ማህጸን ቁልቁል የተደፋ ቅርጽ ያለው የሴት እህቶቻችን ውስጠ አካል ነው። ይህ ውስጠ አካል ብዙ ክፍሎች ሲኖሩት የማህጸን አንገት/በር (Cervix) አንዱ ነው። ይህ አካል ከሌላው የማህጸን አካል በተለየ የደደረ ሲሆን የመውለጃ ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ያለጊዜው ሊከሰት የሚችልን የጽንስ ሹልከት ይከላከላል። በተጨማሪም የሴቶችን ወርሃዊ ዑደት ተከትሎ በሚያመነጫቸው ፈሳሾች ሥር ዓተ ጽንሰትን ያግዛል። እንደ ማንኛውም የሰውነታችን ክፍል የማህጸን አንገትም በተለያዩ ደዌዎች ሊጠቃ ይችላል። የከፋው ደዌ ደግሞ የማህጸን አንገት ካንሰር (Cervical Cancer) ነው። የማህጸን ካንሰር ገዳይ ነው። የማህጸን አንገት ካንሰር በተለይ እንደኛ አገር ባሉ የህብረተሰብ ጤና ተደራሽነት ውስንነትና የማህበረሰቡ የጤና አገልግሎት ተጠቃ ሚነት አናሳ የሆኑ ቦታዎች ውስጥ ከቁንጮ ገዳዮች መካከል አንዱ ነው።
የማህጸን አንገት ካንሰር ልክ እንደ ማንኛውም ካንሰር ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ሊያስነሱት ይችላሉ። ሁዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ የካንሰሩ አማጭ ህዋስ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ቫይረስ ከ150 በላይ ዝርያዎች ሲኖሩት 42 የሚሆኑት ከማህጸን አንገት ደዌ ጋር ቁርኝት አላቸው። ከነዚህ ውስጥ 14ቱ ከማህጸን አንገት ካንሰር ጋር የጠበቀ ዝምድና አላቸው (High risk):: HPV16 እና HPV18 የሚባሉ ዝርያዎች 70 በመቶ ለሚሆነው የማህጸን አንገት ካንሰር አማጭ እንደሆኑ ይነገራል። ለማህጸን አንገት ካንሰር መከሰት የተለያዩ አጋላጭ ሁኔታዎች አሉ። ከበርካታ ሰዎች ጋር ሩካቤ ስጋ መፈጸም ወይም ብዙ የፍቅር አጋር ከነበረው ሰው ጋር ሩካቤ ስጋ መፈጸም፤ የሩካቤ ስጋ ግንኙነትን በልጅነት መጀመር፤ ማጨስ፤ በሌሎች የአባላዘር በሽታዎች ተጠቂ መሆንና የተዳከመ በሽታን የመካላከል አቅም መኖር (ኤች አይ ቪ፤ የምግብ እጥረት፤ ከፍተኛ ውጥረት ወዘተ) ጥቂቶች ናቸው። ከላይ የተጠቀሱ አጋላጭ ምክንያቶች ከሌሉ በፓፒሎማ ቫይረስ መያዝ ብቻ ለማህጸን አንገት ካንሰር መከሰት በቂ አይደለም።
የማህጸን አንገት ካንሰር ብዙ መገለጫዎች አሉት። ዋነኛ መገለጫው የማህጸን አንገት ሲነካ መድማት ነው። ይህ ሁኔታ በወር አበባ መካከል የመድማት ክስተትን ሊያስከስት ይችላል። በኛ አገር የጤና አጠባበቅ ሁኔታ አብዛኛው የማህጸን አንገት ካንሰር ስር ከሰደደና ከተሰራጨ በኋላ ስለሚታወቅ የመዳን ዕድሉ አነስተኛ ነው።
የማህጸን አንገት ቅድመ ምርመራ
የሰለጠኑ አገራት በማህጸን አንገት ካንሰር ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ችለዋል። ይህ የሆነበት ትልቁ ምክንያት ደግሞ የማህጸን አንገት ካንሰር ቅድመ ምርመራን (Pap smear) ትግበራ ላይ በደንብ ስለሰሩበት ነው። ይህ ቅድመ ምርመራ ከማህጸን በር አራቱም አቅጣጫ ናሙና ተወስዶ የሚደረግ ምርመራ ነው። ምርመራው ቅድመ ካንሰርነትን የሚያሳይ ከሆነ ማህጸን ሳይጎዳ በቀላሉ ማከም ይቻላል። የዚህ ምርመራ ናሙና አወሳደድ እጅግ ቀላል ሲሆን በዝቅተኛና በመካከለኛ እርከን ባሉ የጤና ባለሙያዎች ሊከወን ይችላል። ናሙናው የስነ ደዌ ስፔሻሊስት ያለበት ቦታ ተጓጉዞ ምርመራው ይጠናቀቃል። ይህን አሰራር የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር ለዓመታት ይተገብር ነበር። በተለያዩ የግልና የመንግስት ተቋማት ላይም አገልግሎቱ በመስፋፋት ላይ ይገኛል። የማህጸን አንገት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ለሚከተሉት ሴቶች ሊደረግ ይገባል።
ሀ) 21 ዓመት የሞላቸው ሴቶች እስከ 29 ዓመታቸው ድረስ በየሶስት ዓመቱ ይህን ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራል
ለ) የግብረ ሥጋ ግንኙነት ቀድመው የጀመሩ ሴቶች በጀመሩ በሶስተኛው ዓመት ይህን ምርመራ መጀመር ይኖርባቸዋል። (ለምሳሌ በ17 ዓመቷ የጀመረች ምርመራውን በ20 ዓመቷ መጀመር አለባት)
ሐ) ከ20-29 ዓመት የተደረጉት ሶስቱም ምርመራዎች ምንም ችግር ከሌለባቸው ከ30-65 ዓመት ድረስ ምርመራው በየ 5 ዓመቱ ይቀጥላል።
መ) ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶችና ባለፉት 10 ዓመታት መደበኛ ምርመራውን ሲያደርጉ የቆዩ ቅድመ ካንሰር ምርመራውን ማድረግ አይጠበቅባቸውም።
የጋርዳሲል ክትባት (Gardasil Vaccine)
አብዛኞቹ ክትባቶች የሚሰሩት የበሽታ አማጭ ህዋሳትን በማኮላሸት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የዘረመል አስመስሎ ግንባታ ጥበብን (Recombinant DNA Technology) በመጠቀም ከቫይረሱ ጋር በቅርብ ርቀት የሚመሳሰል ሰው ሰራሽ ህዋስ በማዘጋጀት የሚከወን ነው።ጋርዳሲል መጀመሪያ ሲፈጠር ከሁለቱ የHPV ቫይረሶች (HPV 16 and 18) ተመሳሳይ የሆነ ሰው ሰራሽ ህዋሳትን በዘረመል ጥበብ በመቀመር ነበር።ሰውነታችን ለነዚህ ተመሳስለው የተሰሩ ቫይረሶች የበሽታ መከላከያ ንጥረ ነገሮችን በማመንጨት ለወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ በቫይረሱ መጠቃት ለመከላከል በሚል እሳቤ። ሁለቱን ቫይረሶች ብቻ መከላከል ግን ሁሉንም የማህጸን አንገት ካንሰር ሊከላከል እንደማይችል እየታወቀ ሲመጣ ክትባቱን ማሻሻል እንደሚገባ የክትባቱ አምራቾች ተገነዘቡ። አሁን እንደ አዲስ ወጣ የሚባለው ጋርዳሲል 9 (Gardasil 9) ዘጠኙን ዝርያዎች ሊከላከል ይችላል የሚል እሳቤ አለ። ይህኛው ግን ገና በመላው ዓለም አልተሰራጨም። በመላው ዓለም በተፈቀደባቸው አገራት እየተሰጠ ያለው አራቱን ዝርያዎች ይከላከላል የተባለው ነው።
ከጋርዳሲል ጋር የተያያዙ የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሳሉ። የመጀመሪያውና አንገብጋቢው ጥያቄ “እውን ጋርዳሲል የማህጸን አንገት ካንሰርን ሙሉ በሙሉ ይከላከላል ወይ?” የሚለው ነው። መልሱ አይከላከልም ነው። ጋርዳሲል ይከላከላል ከተባለላቸው ከ4ቱ ዝርያዎች ውጭ በሆኑ ዝርያዎች የምትጠቃና ተጋላጭነት ያላት እናት አሁንም ከማህጸን አንገት ካንሰር ተጠቂነት አትድንም። ክትባቱ ይከላከላል የተባለላቸውን ዝርያዎች ይከላከላል ወይ የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ። እንዴውም የተወሰኑ የፓፒሎማ ቫይረሶችን ለይቶ ማጥቃት ሌሎች ዝርያቸውን በፍጥነት እንዲራቡ በር ይከፍትላቸዋል የሚሉ አሉ።ፖሊዮ እየጠፋ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ፖሊዮን የሚያመጣው ቫይረስ ዝርያው አንድ ስለሆነና ለሱ ፍቱን የሆነ ክትባት ስለተገኘለት። በታሪክ እንደጠፋ የሚነገርለት small poxም በተመሳሳይ ሁኔታ ነው የጠፋው። የተለያየ ዝርያ ያላቸው ቫይረሶችን በክትባት የመከላከል ሙከራ ብዙ ጊዜ አጥጋቢ አይደለም። ለእያንዳንዱ ዝርያ ክትባት መስራት አስቸጋሪ ስለሆነ። ሌላው የሚነሳው ጥያቄ ደግሞ ከጋርዳሲል ጋር የተያያዘ የሚከሰቱ የጎንዮሽ ጉዳቶች ናቸው።
በርግጥ የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው መድሃኒት የለም። ጥቅሙ ከጉዳቱ ሲያመዝን ግን መድሃኒቱን እንወስዳለን። የክትባቱ አዘጋጅ የጎንዮሽ ጉዳት ብሎ ካስቀመጣቸው ውጭ ሌሎች ያልተጠበቁ የጎንዮሽ ጉዳቶችን እየጠቀሱና የክትባቱን ጎጂ ጎኖች እያነሱ የሚከራከሩ ሙያተኞችና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች እየተበራከቱ ናቸው።አንዳንዶቹ እንዴውም አንድ የማህጸን አንገት ካንሰርን ለመከላከል መከተብ ያለበትን የሰው ቁጥሩ (Number to treat-NTT) እና ከዚሁ ቁጥር ውስጥ ሊከሰት ከሚችለው የጎንዮሽ ጉዳቶች ጋር በማነጻጸር ጉዳቱ ከውጤታማነቱ ያመዝናል የሚል ድምዳሜ የደረሱ አሉ።
ጋርዳሲል በአሜሪካ የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር አስተዳደርን መስፈርት አልፎ የተመዘገበ ክትባት ነው።ያ ማለት ክትባቱ ፈጽሞ አይጎዳም ማለት አይደለም። ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል መድሃኒቶች መስፈርቱን አሟልተው ከተመዘገቡ በኋላ በድህረ ግብይት የዳሰሳ ጥናት (Post marketing surveillance) ወቅት በተመዘገቡ ለጤና አስጊ የጎንዮሽ ጉዳቶች ምክንያት ከገበያ እንዲወገዱ ተደርገዋል።ከጋርዳሲል ጋር የሚያያዙ የጎንዮሽ ጉዳቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ (94%) ለክፉ የሚሰጡ አይደሉም።6% ደግሞ አስጊ የሚባሉ ናቸው (በጣም ትልቅ ቁጥር ነው)
የሚከተሉት የሚጠበቁ እና ቶሎ ቶሎ ሊከሰቱ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ናቸው።
- የተወጋበት ቦታ የህመም የእብጠት እና የመቅላት መከሰት
- ጠንከር ያለ ራስ ምታት
- የድካም ስሜትና የጡንቻ መቆራረጥ
- ትኩሳት
- የሐኪምን ክትትል የሚሹ እና ጠንከር ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች
- ደምን በፍጥነት የሚያ ወርድ ከፍተኛ የሆነ የሰውነት መቆጣት (anaphylaxis)
- ራስን መሳት
- የሚጥል በሽታ አይነት ማንቀጥቀጥ
- ከነርቭ መላላጥ የተነሳ የሚመጣ የሁለቱም እግሮች መስለል (Gullian Barre Syndrome)
- የህብለ ሰረሰር የመቆጣትና የማበጥ ችግር ( ካበጠበት ወደ ስር ያለው ሰውነታችን ላይታዘዝልን ይችላል)
- የቆሽት ማረር (Pancreatitis- ይሄ ገዳይ ነው በነገራችን ላይ)
የደም መርጋትና የረጋው ደም ሳንባና አንጎል አይነት ወሳኝ የሰውነታችን ክፍሎች ሄዶ ደም ስሮቹን መዝጋት (venous thromboembolic events)
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012 ዓ.ም