- የጅቡቲ መንግስት ለግንባታው በኢትዮጵያ ተለዋጭ ቦታ ጠይቋል
አዲስ አበባ፡- የትራንስፖርት ባለስልጣን ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ግብዓቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ በፍጥነት እንዲገቡና አሠራሩን ለማዘመን ታስቦ 245 ሚሊዮን 751ሺ ብር የተገነባው የደረቅ ጭነት መናኸሪያ ቢጠናቀቅም አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመረ ተገለፀ። ኢትዮጵያ በጅቡቲ ለመገንባት ላቀደችው የፈሳሽ ጭነት መናኸሪያ የጅቡቲ መንግስት በኢትዮጵያ ተለዋጭ ቦታ ጠይቋል።
የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አልማዝ በየሮ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደ አገር ውስጥ የምታስገባቸውን ምርቶች በወቅቱ አገር ውስጥ እንዲደርስ ታስቦ ለተሽከርካሪዎች ማቆሚያ በጅቡቲ የደረቅ መናኸሪያ ግንባታ ቢካሄድም አገልግሎት መስጠት አልጀመረም።
ይህም ሊሆን የቻለው በመናኸሪያው ውስጥ የሚያልፍ የኤሌክትሪክ ምሰሶ ቀደም ሲል ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጠውና መፍትሄ ሳይበጅለት ግንባታው በመከናወኑ ነው መሆኑን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። ይህም ለአሽከርካሪዎችም ሆነ ለተሽከርካሪዎች እክል የሚፈጥርና አደጋ የሚጋብዝ መሆኑን ጠቁመዋል።
መናኸሪያውን መሃል ለመሃል ሰንጥቆ የሚያልፈውን የኤሌክትሪክ ምሰሶ ለማንሳት ከፍተኛ ወጪ ተጠይቋል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ከዚህም በተጨማሪ ምሰሶዎቹ አደጋ ሊያደርሱ እንደሚችሉና የከተማዋ የመብራት ሥርጭት ላይም ጫና እንደሚፈጥሩ ጠቁመዋል። በመሆኑም ይህ እልባት ሲሰጠው ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት ይችላል ብለዋል።
አሁን ያለው ችግር አሳሳቢ በመሆኑም በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፍተኛ ክትትል እያደረገ መሆኑንና መናኸሪያው ሥራ ሲጀምር ግን ወደ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ የሚገቡ ከባድ ተሽርካሪዎችን በሙሉ የማስተናገድ አቅም እንዳለው አብራርተዋል።
በተመሣሣይ በጅቡቲ ለመገንባት ለታሰበው የፈሳሽ ጭነት መናኸሪያ የኢትዮጵያ መንግስት የጅቡቲ መንግስትን የግንባታ ቦታ የጠየቀ ሲሆን፤ የጅቡቲ መንግስት በተራው አገሪቱ ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ የምትወስዳቸውን ምርቶች ለማከማቸትና ለማጓጓዝ ያመቻት ዘንድ ግንባታ የማከናወን እቅድ እንዳላት አስገንዝበው በኢትዮጵያ አቻ ቦታ መጠየቃቸውን ገልፀዋል። በዚህም የተነሳ እስካሁን ርክክብ አለመከናወኑንና በእንጥልጥል ላይ ያለ ጉዳይ መሆኑን ወይዘሮ አልማዝ አብራርተዋል።
በፌደራል ትራንስፖርት የከተማና ገጠር ትራንስፖርት ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ባዩ ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ በጅቡቲ ተርሚናል የተገነባው ደረቅ ጭነት መናኸሪያ 86ሺ ካሬ የሚሆነው የመጀመሪያው ዙር በኮንክሪት 75ሺ ካሬ ደግሞ በአስፋልት እንዲሰራ የታቀደና ፕሮጀክቱ ከ10 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነው።
ይሁንና እስካሁን ድረስ በቂ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም። በተለይም በወቅቱ በፕሮጀክቱ ውስጥ መካተት የነበረባቸው የውሃ ፍሳሽ ማስወገጃ፣ አጥር፣ ማማ፣ መፀዳጃ ቤትና ሙሉ ለሙሉ ተርሚናል ለማስገንባት መካተት የነበረባቸው መስፈርቶችና ግንባታዎች አልተካተቱም።
እንደ አቶ ሙሉጌታ ባዩ ገለፃ፤ የመናኸሪያው ኮንክሪት ግንባታ ተጠናቆ ሥራ እንዲጀምር የተደረገ ቢሆንም በቂ አገልግሎት መስጠት አልቻለም። በአሠራር ደረጃው በጅቡቲ ያለውን ከፍተኛ የሆነውን ሙቀት መቋቋም የማይችል ነው።
በተጨማሪም መናኸሪያውን አቋርጦ የሚያልፍ ኤሌክትሪክ ምሰሶ ከሥራው በፊት በዲዛይን ሥራ ተካቶ መነሳት ነበረበት። በመናኸሪያው አጠገብ ባለው አስፋልት ውስጥም የሚያልፍ ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ገመድ የተቀበረ ሲሆን ይህም በሥራው ላይ ሌላ ጫና ፈጥሯል። ለዚህ ሁሉ ችግር መጀመሪያ በዲዛይን መመለስ የነበረበትና ግንባታው ሳይጀመር ቀድሞ መጠናቀቅ እንደነበረበት ገልፀዋል። ይህ ባለመሆኑም እስካሁን ችግር ሆኖ መቀጠሉንና መናኸሪያው በቂ አገልግሎት እንዳይሰጥ ሆኗል።
ከፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የደረቅ የጭነት መናኸሪያው ውስጥ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን ለማንሳት 73ሺ ዶላር መጠየቁ ታውቋል። የግንባታው ዋነኛ ችግር ሊከሰት የቻለውም በዲዛይን መጠናቀቅ የነበረበት የመጀመሪያ ደረጃ ሥራ በሚገባ ባለመከናወኑ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር