አዲስ አበባ፡-የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በተፋጠነ ሁኔታ ለማጠናቀቅ አስፈላጊው ርብርብ እየተደረገ ሲሆን፤ ባለፉት አራት ወራት ብቻ 340 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ገለፀ፡፡
የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብረሃም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ለግድቡ ግንባታ መፋጠን ሲደረግ የነበረው ድጋፍ መቀጠሉንና ከነሐሴ 2010 ዓ.ም እስከ ህዳር 2011 ዓ.ም ድረስ ብቻ ከ340 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ግንባታው ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ከህዝቡ የተሰበሰበው ከ12.3 ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ በያዝነው የበጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 13 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ታቅዷል።
ለግድቡ ግንባታ ይካሄድ የነበረው ህዝባዊ ንቅናቄ በመቀዛቀዙ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራው ተዳክሞ እንደነበር አስታውሰው ሆኖም ግን መንግሥት ስለ ግድቡ ግልጽ መረጃ ለህዝብ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ አስፈላጊ እርምጃዎች እየተወሰዱ በመሆናቸው የግድቡን ግንባታ የማፋጠን ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በቅርቡ የመገናኛ ብዙኃን ቡድን ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑና ህዝባዊ ተሳትፎውም ከመቼውም በላቀ ሁኔታ እንደሚከናወን አቶ ኃይሉ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አብረሃም በላይ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ይሠራው የነበረው የግድቡ አካል መዘገየትን አስታውሰው፣ የግድቡ ግንባታ ለማፋጠን ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን ለማቃለል በጥናት ላይ የተደገፈ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ዶክተር አብረሃም ገለጻ፤ የሃይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር ግንባታ ለማከናወን ሲጂጂሲ ከተባለው የቻይና ተቋራጭ ጋር የውል ስምምነት ተፈርሟል፡፡ የመካኒክል ሥራዎችን ለማከናወን ደግሞ ሲኖ ከተባለ ተቋራጭ ጋር ውል ታስሯል፡፡ የግድቡን ግንባታና ውሳኔ አሰጣጡ የተፋጠነ እንዲሆንም ዓለም አቀፍና ልምድ ካላቸው ተቋሟት ጋር ሥራ መጀመሩንም አረጋግጠዋል፡፡
መንግሥት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ኃይል ማመንጨት ሥራውን በ2013 ዓ.ም የሚጀምር ሲሆን፤ በ2015 ዓ.ም ደግሞ የግድቡ ሥራ መቶ በመቶ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት የግድቡ የሲቪል ሥራ 82 ከመቶ፣ መካኒካል ሥራው 25 ከመቶ የደረሰ ሲሆን፤ አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ 65 ከመቶ ደርሷል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር