ብዙዎች ከዛሬ 20 አመታት በፊት በሆነውና እንደዋዛ ሊዘነጉት ባልቻሉት አሳዛኝ ዕለት ዙሪያ በትዝታ ሲመላለሱ ውለዋል። ይህ ጊዜ ለአገሪቱ ብቻ ሳይሆን ድንገቴውን የአደጋ ዜና ለሰማው የዓለም ክፍል ሁሉ እጅግ አሳዛኝ ቀን ነበር።
ህዳር 14 ቀን 1989 ዓም። በክፉ አሳቢዎቹ ጠላፊዎች ውጥን በኮሞሮስ ደሴት ዳርቻ የወደቀውና ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሆነው የበረራ ቁጥር ኢቲ 961 ቦይንግ 767 የመንገደኞች አይሮፕላን ላይ በደረሰው አደጋ የበረራ ሰራተኞችን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ዜጎች ህይወት ስለማለፉ ተሰማ ።
በወቅቱ በኢትዮጵያዊው ፓይለት ካፒቴን ልዑል ጥረትና በተአምር ከተረፉት ጥቂት ተሳፋሪዎች ባሻገር የአደጋው ክብደት ለብዙሀኑ አይረሴ ሆኖ አልፏል። ይህን ክፉ አጋጣሚ በየአመቱ ከመዘከር ባሻገር በኢትዮጵያ የበረራ ታሪክ ጥቁር አሻራቸውን ጥለው ካለፉት አደጋዎች መካከል አንደኛው ሆኖ ተመዝግቧል።
የበርካቶች ህይወት በኮሞሮሱ የአይሮፕላን አደጋ ያለፈበትን የቀን ክፉ ሲያስቡ የዋሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ማምሻው የሰሙት ሌላ የትራፊክ አደጋ ዜና ደግሞ ከክፉ ቀን ትውስታቸው ፈጥነው እንዳይወጡ ምክንያት ሆነ።
ህዳር 14 ቀን 2012 ዓም። በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች በተመሳሳይ ጊዜና ሰዓት የደረሱ የመኪና አደጋዎች የ49 ሰዎችን ህይወት ቀጥፈው በርካቶችን ለከፋ የአካል ጉዳት ማጋለጣቸው ተነገረ። ዕለቱም የክፉ ቀናት ግጥጥሞሽ ሆነና በየቀኑ የትራፊክ አደጋዎችን ወሬ እየሰማ ለሚያድረው ሁሉ እጅግ የከፋ ዜና ሆኖ ሊያመሽ ግድ አለ።
ነፍሰጡሯ ወይዘሮ ዘጠኝ ወራትን እየቆጠረች የመውለጃ ጊዜዋን ስታሰላ ከርማለች። ያሳለፈችው የእርግዝና ጊዜ ፈታኝ ቢሆንም ከቀናት በኋላ ወልዳ የምትስመውን ፍሬዋን እያሰበች ጭንቀቷን ሁሉ ትረሳለች። ለአራስነት ቆይታዋ ቤት ጓዳዋን አሟልታ ‹‹ለእንኳን ማርያም ማረችሽ››ወግ መቃረቧን ስታስብ ደግሞ የድካም ጎኗን አሳርፋ እፎይታዋን አሻግራ ትናፍቃለች። ይሄኔ ወደ አዲሱ ዓለም ለመምጣት ‹‹ልቀቁኝ››የሚለው ጽንስ ከውስጧ ሲፈራገጥ ይሰማታል። ይህ እውነትም የእናትና ልጁን ቁርኝት አጥብቆ ዓይን ለዓይን የሚተያዩበትን ዕለት እያስጠጋ ቀናት ማፋጠኑን ቀጥሏል።
እነሆ! ህዳር 14 ቀን 2012 ዓም የቁርጡ ቀን የቀረበ ይመስላል።ዘጠኝ ወራትን በእርግዝና የቆየችው ወይዘሮ የናፈቀቸውን ልጇን ታቅፍ ታጠባው ዘንድ ጊዜው ደርሷልና ህመም ቢጤ ይሰማት ይዟል። ምልክቱ የምጥ እንደሆነ የገመቱ ቤተሰቦች የልጃቸውን በሰላም መገላገል ናፍቀው ምጡ ሳይፋፋም ወደ ጤና ተቋም ሊያደርሷት ተሰባስበዋል። ባጃጅ ቀርቦ ወላዷ ወደውስጥ እንደገባችም ከጎኗ ሆነው በጭንቀቷ ሊገኙ የወደዱ ቤተሰቦቿ አጅበዋት ጉዞ ጀምረዋል።
መንገዱ ወደ ጤና ጣቢያ ሲያመራ ሁሉም ከቆይታ በኋላ ስለሚቀበሉት አዲስ እንግዳ እያሰቡ ነበር። ይህ ሕልም ግን ከዳር አልደረሰም። በድንገት ትንሽዋ ባጃጅ ባጋጠማት ከባድ የመኪና ግጭት ከመንገድ ተስፈንጥራ ወደቀች። ወዲያውም ነፍሰጡሯን ጨምሮ የስድስት ቤተሰብ አባላት ህይወት ተቀጠፈ።
ይህ ብቻ አይደለም። በዚሁ ቀን ጉዞውን ወደ አምቦ ከተማ ያደረገው የሕዝብ ማመላለሻ ሀይሩፍ ሚኒባስ ከአንድ ቱርቦ ከባድ መኪና ጋር ተጋጭቶ በውስጡ የነበሩ 17 ተሳፋሪዎች ህይወት ወዲያውኑ ተቀጥፏል። በሚኒባሱ ውስጥ ከነበሩት መካከል ሰባት ያህሉ የአምቦ ዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች ናቸው። አብዛኞቹም ለመመረቅ ጥቂት ጊዜያት የቀራቸው፣ ስለነገ መልካም ተስፋን የሰነቁና ሀገራቸውም በጥብቅ የምትሻቸው ዜጎች ነበሩ።
አደጋው በደረሰበት ቀን መሰማት የጀመሩ የትራፊክ አደጋ ዜናዎች በዚህ ብቻ አልተቋጩም። በአገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎች በመኪና መገጨት፣ መገልበጥና መጋጨት በደረሱ ክስተቶች 49 ሰዎች ስለመሞታቸው ተመዝግቧል።ከተጠቀሰው ዕለት በፊትም ሆነ በኋላ ለጆሮ የሚከብዱ አደጋዎችን እየሰማን ስለነገ በስጋት ማደራችንን ቀጥለናል። አሁን ላይ የትራፊክ አደጋ ጉዳይ እጅግ ከባድና አሳሳቢ እየሆነብን ይገኛል።
በአደጋው የበርካቶች ህይወት ጠፍቶ ብዙሀኑን ለከፋ የአካል ጉዳት ዳርጓል። ጠዋት ወጥተን ማታን በሰላም ለመመለስ ተስፋ በሆነበት አጋጣሚም ልጆች ያለ አሳደጊ ቀርተዋል። ጥቂት የማይባሉ ቤተሰቦች ጎጆ ተዘግቶ አረጋውያን ያለጧሪና ሰብሳቢ በሀዘን እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል።
በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት ወድሞም በርካቶች ያለፉበትን ጥሪት አጥተዋል።ዛሬም በየቀኑ የምናይና የምንሰማቸው አደጋዎች አልተቋረጡም ። ማመን ከምንችለው በላይ ቁጥራቸው እያሻቀበ በየሰከንዱ ከስጋት ጋር እንድንራመድ ምክንያት ሆነውናል።
ብዙዎች የአገሪቱ ስም በክፉ ለሚያስጠራው የትራፊክ አደጋ መበራከት ከአሽከርካሪውና ከተገልጋዩ ጋር በማያያዝ የራሳቸውን ምክንያትና ሰበብ ያስቀምጣሉ። ከ33 አመታት በላይ በሹፍርና ሙያ የቆዩት የባስ ካፒቴን ታምራት ወልደ ጊዮርጊስ ግን ‹‹ሁሉም ለስነምግባር ደንቦች ተገዢ ቢሆን ለአደጋ የተጋለጠ አይሆንም ነበር›› በሚል ያምናሉ።
በቀድሞ ሰራዊት የፈንጂ አምካኝ ባለሙያ እንደነበሩ የሚጠቅሱት አቶ ታምራት ይህ ጥንቃቄ የተሞላበት ልምድም ዕድሜያቸውን ለገፉበት የሹፍርና ሙያ መሰረት ሆኖ አብሯቸው መዝለቁን ያመለክታሉ። ስራ ጀምረው እጃቸው ከመሪ ጋር ሲገናኙም ከመንገዳቸው በቀር ስለምንም አያስቡም። «የፈንጂ ማምከን ስራ ስህተቱ ሞት ብቻ ነው። ማሽከርከርም ቢሆን ስህተት ከተገኘበት ውጤቱ በሞት ይደመደማል» ይላሉ።
ዛሬ አንጋፋው ሾፌር ተቀጥረው በሚሰሩበት የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በጠንቃቃ አሽከርካሪነታቸው በየአመቱ አመስግኖ ከሚያከብራቸው ሰራተኞች መካከል አንዱ ሆነዋል። አቶ ታምራት ለአምስት ተከታታይ አመታት ያለምንም አደጋ በመጓዛቸው የወርቅ ሜዳሊያና የዋንጫ ተሸላሚ ናቸው።
የባስ ካፒቴን ሰለሞን ዋሴም ለሶስት ተከታታይ አመታት አደጋን ተከላክሎ በማሽከርከር የገንዘብና የብር ሜዳሊያ ከተሸለሙ ሾፌሮች መካከል አንደኛው ነው። ሰለሞን ጎንደር በነበረበት ጊዜ ለአመታት የህጻናት ማመላለሻ ሾፌር በመሆን አገልግሏል። በወቅቱ ለህጻናቱ የሚያደርገው ጥንቃቄና ትኩረትም አመታትን ለተሻገረበት ሙያ መነሻ እንደሆነው አይሸሽግም።
ሰለሞን ብዙዎች ለሚያደርሱትና ለሚደርስባቸው የትራፊክ አደጋ መንስኤው ያለመረጋጋት ችግር መሆኑን እንደምክንያት ያስቀምጣል። ‹‹የአንድ ወገን ጥንቃቄ ብቻውን ውጤት አያመጣም›› የሚለው ባስ ካፒቴኑ ‹‹አንዱ ለሌላው ሰበብ ሳይሆን መንገድን ከስጋት በራቀ ጉዞ ማጠናቀቅ ለሁሉም ይበጃል›› ሲል መልዕክቱን ያደርሳል።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012
መልካምስራ አፈወርቅ