ቅኔ ትርጉመ ብዙ ቃል ነው። ብዙ ጊዜ የምንሰማው ግን በቤተ ክህነትና በአብነት ተማሪዎች ዘንድ ነው። ቅኔ ሲባልም ለብዙዎቻችን ቀድሞ ትዝ የሚለን የአብነት ተማሪዎች የሚሉት የግዕዝ ቅኔ ነው። ይህ ደግሞ ለብዙዎቻችን አይገባንም። ለብዙዎቻችን የሚገባን በስነ ጽሑፍ ውስጥ ያለው ቅኔ ነው። ለምሳሌ ግጥም ቅኔ ነው። ዳሩ ግን ብዙ የሚባልለት የዘመናዊ ገጣሚዎች እንጂ የሕዝብ ግጥም አይደለም። ለዘመናዊ ገጣሚዎች መነሻ የሆነው የሕዝብ ግጥም የቅኔ መሰረት ነው። ግልጽ የሆነ ሰምና ወርቅ የምናገኘውም በሕዝብ ግጥሞች ውስጥ ነው። ወደ ሕዝብ ግጥሞች ሰምና ወርቅ ከመግባታችን በፊት ግን ቅኔ (ሰምና ወርቅ) ምንድነው የሚለውን እንመልከት።
የአማርኛ ቅኔ (ሰምናወርቅ) አጭር የአማርኛ ንግግር ክፍል ሲሆን፤ በውስን ቃላት፣ ሐረጋት፣ ስንኝና ስድ ጽሑፍ ወዘተ ከባድና ስውር መልዕክት የምናስተላልፍበት ልዩ አገላለጽ ነው ።
ሰምና ወርቅ ሲባል በእማሬያዊ (የተለመደው) ትርጉም፤ ሰም ማለት ሰምአ ሰማ (ሰምነከረ ሰራ) ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ሲሆን ጥሬ ትርጉሙ በአማርኛ ሰም ማለት ከማር ምጣጭ (ጭማቂ) ተነጥሮ የሚዘጋጅ ለመጻፍና ጡዋፍን ለመስራት የምንጠቀምበት ጥሩ ሽታ ያለው ቁስ ማለት ነው። ወርቅ ማለት ደግሞ በማዕድን በቁፋሮ ከመሬት ውስጥ የሚገኝ ልፋት፣ጥረትና ድካምን የሚጠይቅ አንጸባራቂ አጥበርባሪ የሚያምርና ውብ ማራኪ መልክ ያለው ውድ የሆነ ቁስ ነው። ሰምና ወርቅ ሲባል በአማርኛ አገባቡ ግን ይለያል።
ወርቅ ወርቅነቱ የሚታወቀው በእሳት ሲፈተን እንደሆነው ሁሉ በአማርኛ ንግግርም ወርቅን ለማወቅና ለመገንዘብ ጊዜና ጥረትን፣ የማገናዘብ አቅምን፣ ብልህነትን፣ ማሰብን፣ክህሎትን እና ፍላጎትን የሚጠይቅ ነው። ከታወቀ በኋላም ልዩ አቅምን የሚፈጥርና ሰውን የዕውቀት ማህደር ማድረግ የሚችል ነው።
ሰምና ወርቅ የአገሪቱን ወግ፣ ባህል፣ ልማድ፣ ጀግንነት፣ ሐዘን፣ ደስታ፣ ታሪክና የት መጣሽነት በግጥም እና በስድ ንባብ ሲያወሳና ሲዘክር ይኖራል። ይህ የአማርኛ ትምህርት ክፍል ለምርምር፣ ለመድኃኒት ቅመማ፣ ለፈጠራና ስነ ጽሑፍ እንዲሁም ለዜማና ድርሰት ሙያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ነው።
ሰምና ወርቅ የግዕዝ እና የአማርኛ ተብሎ በሁለት ይከፈላል። ሰም በአማርኛ ጥሬ ትርጉሙ በቀጥታ የምናገኘው የቃሉ እማሬያዊ (አውዳዊ) ፍች ማለት ሲሆን ወርቅ ማለት ደግሞ ህቡዕ (ስውር)፣ ድብቅ ሆኖ በፍለጋና በማሰብ የሚደረስበት የቃሉ ሁለተኛ ትርጉም (ልዩ መልእክት) ወይም የቃሉ ፍካሬያዊ ፍች ማለት ነው ። ሰምና ወርቅን አጣምሮ የያዘው ቃል ደግሞ ሕብረ ቃል ይባላል። አንድን ቅኔ (ሰምና ወርቅ) ለመፍታት የመጀመሪያው ሥራ ሕብረ ቃሉን ማወቅ ነው። ሕብረ ቃሉ ውስጥ ሰምና ወርቅ ይገኛል።
የአማርኛ ቅኔን ለመፍታት የተለያዩ ዘዴዎች አሉት። ይሄውም ሆሄያትን ከሳድስ ወደ ራብዕ ወይም ከራብዕ ወደ ሳድስ በመቀየር፣ ላልቶና አጥብቆ በማንበብ፣ ሁለት ትርጉም ያላቸውን ቃላት ጠንቅቆ በማወቅ፣ ታሪክን በማወቅ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከቁራንና ከሌሎች ድርሳናት ትርጉሙን በማወቅ ነው። መልዕክታቸውም፤ የሀዘን ወይም የደስታ፣ የታሪክ ወይም የቀልድ፣ የወቀሳ ወይም የአድናቆት… ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ።
መቅደላ አፋፉ ላይጩኸት በረከተ
የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ
የቅኔው አይነት የሀዘን ሲሆን አፈታቱ ደግሞ ታሪክን በማወቅ ነው። በዚህ ቅኔ ውስጥ ሕብረ ቃሉ ‹‹ወንድ አንድ ሰው›› የሚለው ነው ። ታሪኩ ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ የሞቱበት መሆኑ ነው። የቅኔው ሰም መቅደላ አፋፍ ላይ ከፍተኛ ለቅሶና ጩኸት የተሰማ ሲሆን በቁጥር አንድ ወንድ ሞቷል፤ ምን ያህል ሴት እንደሞተ ግን አልታወቀም የሚል ነው ።
የቅኔው ወርቅ ጀግናው አጼ ቴዎድሮስ ሞተ የሚል ነው። ይሄውም በድሮው ጊዜ (በእርግጥ አሁንም ይባላል) ‹‹ወንድ›› የሚለው ቃል በእማሬያዊ ትርጉሙ ፆታን አመልካች ቢሆንም በፍካሬያዊ ትርጉሙ ጀግንነትንም አመልካች ነበር። ከቅኔ አፈታት ዘዴዎች አንዱ ደግሞ እማሬያዊና ፍካሬያዊ ትርጉም ያላቸውን ቃላት መለየት ነው።
እነዚህ የሕዝብ ቅኔዎች በብዛት የሚያተኩሩት በወቅቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ ነው። ለዚህም ነው የመሪዎችን ስም እየጠቀሱ ነው የሚቀኙት። በወቅቱ እንደ ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን ወይም ማህበራዊ ድረ ገጽ የመሳሰሉ መገናኛ ብዙኃን ስለሌሉ ሀሳብን መግለጽ የሚቻለው በለቅሶ፣ በሰርግና በሥራ ቦታዎች ላይ በሚደረጉ እንጉርጉሮዎች ነው። አድናቆትም ይሁን ትችት የሚነገረው ደግሞ በቀጥታ ሳይሆን በቅኔ ነው። ምናልባት በወቅቱ የነበረው ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት ስለማይፈቅድ ይሆናል፤ ይህ ሀሳብን በቅኔ የመግለጽ ነገር ግን አሁንም አለ። ምክንያቱ ሁለት ነው። በአንድ በኩል መንግስት እንዳይቆጣ ለመሸወድ ሲሆን በሌላ በኩል ግን የኪነ ጥበብ ውበት እንዲኖረው ነው። አንድ ነገር በቀጥታ ሲነገር ውበት አይኖረውም፤ ኪነ ጥበብ የሚሆነው ሰዎች ፈልገው የሚያገኙት ትርጉም ሲኖር ነው። እንዲህ ለማለት ፈልጎ ነው ሲባል ነው። በቀጥታ ከተነገረ ቅኔ ሳይሆን ዜና ነው የሚሆነው።
ወደ ቀድሞ የሕዝብ ቅኔዎች እንመለስ።
አጼ ዮሐንስ ይዋሻሉ
መጠጥ አልጠጣም እያሉ
ሲጠጡ አይተናል በእርግጥ
ራስ የሚያዞር መጠጥ
ሕብረ ቃሉ ‹‹ራስ የሚያዞር›› የሚለው ነው። የዚህ ቅኔ ሰም (በግልጽ የሚታወቀው ትርጉም) አጼ ዮሐንስ መጠጥ አልጠጣም (አልወድም) ቢሉም ተደብቀው ሲጠጡ አይተናል እንደማለት ነው። የቅኔው ሰም (በሥውር መንገር የተፈለገው መልዕክት) አጼ ዮሐንስ ከሱዳኖች ጋር ሲዋጉ አንገታቸው ተቆርጦ ተወስዶ ነበርና እሱን ለመግለጽ ነው። ከመጠጥ ጋር የተገለጸም ይህኛውን ትርጉም ለመሸፈን እንጂ አጼ ዮሐንስ የሚያሰክር መጠጥ ሲጠጡ ታይተው ላይሆን ይችላል።
ልብ በሉ! በዚያን ወቅት እንኳን አጼዎችንም መተቸት ይቻል ነበር ማለት ነው። በዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ላይም፣ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ላይም እንዲህ አይነት አጼዎችን ወጋ የሚያደርጉ ቅኔዎች ተነግረዋል።
አንጥረኛው ብዙ ከንጉሱ ቤት
ባልአልቦ አደረጉት ያንን ሁሉ ሴት
ሕብረ ቃሉ ‹‹ባልአልቦ›› የሚለው ነው። አሁንም አንድ ነገር ልብ በሉ! በወቅቱ ቅኔዎች የሚገለጹት ከጽሑፍ ይልቅ በቃል ነበር፤ እናም ተደራቢ ትርጉማቸውን ለመደበቅ ምቹ ነበር። በጽሑፍ ሲሆን ግን ቶሎ የመታወቅ ዕድሉ ሰፊ ነው። ለምሳሌ ይሄ ሕብረ ቃል በጽሑፍ ሲጻፍ ‹‹ባል አልቦ›› ወይም ባለ አልቦ›› ተብሎ ሊሆን ይችላል፤ ሰዎች በቀላሉ አወቁት ማለት ነው። በድምጽ (በቃል) ሲነገር ግን ቅኔነቱ ይጨምራል። ለማንኛውም ወደ ትርጉሙ እንሂድ።
የዚህ ቅኔ ሰም፤ በንጉሳዊያኑ ዘመን ብዙ ጥበበኞች ነበሩ። አንጥረኛ ማለት የእጅ ሙያ ያለው ማለት ነው። እነዚህ የእጅ ሙያ ያላቸው ሰዎች የሚኖሩት በንጉሶች አካባቢ ነው። እነዚህ አንጥረኞች ‹‹አልቦ›› የሚባል የሴቶች የእግር ጌጥ ይሰራሉ። በህብረ ቃሉ ውስጥ ‹‹ባለ አልቦ›› አደረጉት ማለት ለሴቶች አልቦ ሰጧቸው ማለት ነው። ‹‹ባል አልቦ›› ሲሆን ደግሞ ባል (የትዳር ጓደኛ) አሳጧቸው ማለት ነው። አልቦ ማለት በግዕዝ ምንም ወይም የሌለ ማለት ነው። ባሎቻቸው በጦርነት ይሞቱ ስለነበር ባል የሌላቸው ይሆናሉ ማለት ነው። ሌላኛው ቅኔው ደግሞ ወታደሮች የሰው ሚስት ይቀሙ ስለነበር ባሎቻቸውን አሳጧቸው እንደማለትም ነው።
ከታሪክና ፖለቲካ ውጭ ያሉ ሌሎች ማህበራዊና የፍቅር ቅኔዎች እንሂድ።
ምን ያደርጋል ጠላ ምን ያርጋል ጠጅ
ጠላትን መጋበዝ ቡናአርጎ ነው እንጂ
በቅኔ አፈታት ሂደት ውስጥ ቃልን ከቃል መሰንጠቅ፤ ራብዕን ወደ ሳድስ መቀየር የተለመደ ነው። የዚህ ቅኔ ሕብረ ቃል ‹‹ቡናአርጎ›› የሚለው ነው። ራብዕን ወደ ሳድስ ወይም ሳድስን ወደ ራብዕ በመቀየር ‹‹ና››ን ወደ ‹‹ን›› ወይም ‹‹ን››ን ወደ ‹‹ና›› መቀየር እንችላለን። በዚህ አካሄድ የቅኔው ሰም ጠላትን ጠላ እና ጠጅ መጋበዝ ሳይሆን ቡና አፍልቶ መጋበዝ ነው ጥሩ ማለት ነው። የቅኔው ወርቅ ግን ጠላትን ጠላ ጠጅ መጋበዝ ሳይሆን ቡን(ደህና አድርጎ) አድርጎ መደብደብ ነው ማለት ነው።
ቃላትን መሰንጠቅ አንዱ የቅኔ አፈታት ዘዴ እንደሆነው ሁሉ ቃላትን መገጣጠምም እንደዚሁ የቅኔ አፈታት ዘዴ ነው። ተከታዩን ምሳሌ እንመልከት።
ይሄው ደረትሽ ነው ያጣለው ሰውን
እስኪ ሸፈን አርጊው ያጡት እንደሆን
ሕብረ ቃሉ ‹‹ያጡት›› የሚለው ነው። ሰሙ ደረትሽ ያምራል፤ የደረትሽ ማማር ሰዎችን እያጣላ ነውና እስኪ ሸፍኝውና ይጡት (አያግኙት) ማለት ነው። ወርቁ ደግሞ ያ ጡትሽ ነው ነውና ሸፍኝው ማለት ነው።
አንዳንድ ቅኔዎች የሚፈቱት ሁለት ትርጉም ያላቸውን ቃላት ጠንቅቆ በማወቅ ነው። ሳይጠብቅም ሳይላላም፤ ቃሉን ሳይገጣጠምም ሳይሰነጣጠቅም ሁለት ትርጉም የሚይዙ ይኖራሉ። ተከታዩን ቅኔ እንመልከት።
አላህ ካደረሰን ለሮመዳን ቀን
መልበስ ይገባሃል የሱፍ ኮትህን
ሕብረ ቃሉ ‹‹የሱፍ ኮትህን›› የሚለው ነው። የዚህ ቅኔ ሰም ሱፍህን (የኮት አይነት) መልበስ አለብህ ማለት ነው። ቅኔው ደግሞ የሱፍ የተባልከው ሰው ኮት የሮመዳን በዓል ነውና ኮት ልበስ ማለት ነው። በነገራችን ላይ የዚህ ቅኔ ሰምና ወርቅ በጣም ተቀራራቢ ነው። ብናቀያይረውም ብዙም ልዩነት የሚያመጣ አይደለም። እንደሚታወቀው ሮመዳን የሙስሊም በዓል ነው፤ የሱፍ የሚባል ስም ደግሞ የሙስሊም ነው። ስለዚህ የወርቁ ትርጉም ብዙም ሩቅ አይደለም። እርግጥ ነው አንዳንድ ቦታ ላይ ሰምና ወርቅ እኩል የሚሆኑበት አጋጣሚም አለ።
አንዳንድ ቅኔዎች በጣም ረቂቅ ይሆኑና ብዙ ግራ ያጋባሉ። በተለይም ቃልን በመሰንጠቅ የሚፈቱ ቅኔዎች ረጋ ብሎ ማሰብንና ማሰላሰልን ይጠይቃሉ። ልብ ብለን ካላስተዋልን ቶሎ አይመጣልንም። የሚከተለውን ግጥም ልብ በሉ።
ቀለምና ቀለም ተጣልተው በቦታ
ጊዜ ተሰጥቷቸው የቀጠሮ ተርታ
ነገሩን ብናየው አግድሞ ካለፈ
ብለው ገለጹልን ወገን አሸነፈ።
ይሄን ቅኔ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰማው ሰው እንደሚቸገር ነው። ምናልባት ግን በቀላሉ የሚያገኘው ሰውም ሊኖር ይችላል። የዚህ ቅኔ ሕብረ ቃል ‹‹ወገን›› የሚለው ነው። የቅኔው ሰም ‹‹ወ›› የተባለው ፊደል (ሆሄ) ‹‹ገ›› የተባለውን ፊደል አሸነፈ ማለት ነው። በአማርኛ የፊደል ገበታ አቀማመጥ ‹‹ወ›› ከ››ገ›› ቀድሞ ነው የሚገኘው። ወርቁ ወገን (ዘመድ) አሸነፈ እንደማለት ነው።
ከድሮ ቅኔዎች ወደ ቅርብ ዘመን ስንመጣ ደግሞ አሁንም በዘፈኖች ውስጥ እናገኛለን። በተለይም የአራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች መገኛ በሆነችው ወሎ ውስጥ ብዙ ዘፈኖች ሰምና ወርቅ ያላቸው ናቸው። እነዚህ ዘፈኖች ግጥሞቻቸው የሕዝብ ስለሆነ ከአንድ ዘፋኝ በላይ ሊጠቀማቸው ይችላል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ምናልባትም ዘፋኙ ራሱ የፈጠራቸውም ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ የአበበ ፈቃዱ ‹‹አንቺን ብሎ›› የሚለው ዘፈን ውስጥ ይህን ሰምና ወርቅ እናገኛለን።
ራያ ሰቆጣ ኮረም ተወልደሽ
ማን ይሆን መለኛው የጁ ሚያረግሽ
የተጠቀሱት ቦታዎች በአንድ አካባቢ የሚገኙ ናቸው። ተፈቃሪዋ ራያ ወይም ሰቆጣ ወይም ኮረም ተወልዳ ይሆናል። ወይም ደግሞ አንዱ ቦታ ተወልዳ ሌላኛው ቦታ አድጋ ይሆናል። የዘፋኙ ጥያቄ እነዚህን አካባቢዎች ካዳረስሽ አይቀር የጁ (ወሎ ውስጥ የሚገኝ ነው) የተባለው ቦታስ ማን ያመጣልኝ ይሆን እያለ ነው። በቅኔው ደግሞ አንቺን የመሰልሽ ቆንጆ የሚያገኝሽ (በእጁ የሚያስገባሽ) ማን ይሆን መለኛ ብሎ እየጠየቀ ነው።
በድምጻዊት የዝና ነጋሽ ዘፈን ውስጥ ደግሞ ተከታዩን ቅኔ እናገኛለን። ይህ የየዝና ነጋሽ ቅኔ ግን በሕዝብ እንጉርጉሮዎች ውስጥም ይገኛል።
እሾህ ብቻ ሆኗል እግሬን ብዳስሰው
እንዴት መራመጃ መሄጃ ያጣል ሰው
ሕብረ ቃሉ ‹‹መሄጃ መራመጃ›› የሚለው ነው። የዚህ ቅኔ ሰም እግሯን እሾህ ስለወጋው መሄድ (መራመድ) አልቻለችም። ወርቁ ደግሞ በፍቅር ስለተጎዳች የት አገር ብሄድ ነው የሚለቀኝ፤ እንዴት የምሄድበት (አገር) አጣላሁ እያለች ነው። በነገራችን ላይ ይሄ ቅኔ ለፍቅር ብቻ አይደለም። በኑሮ ወይም በሌላ ነገር የተማረረ ሰውም የሚለው ነው። መሄጃ አጣሁ እያለ ሲያማርር ማለት ነው።
ቅኔ በፍቅር፣ በታሪክ፣ በእምነት የሚፈጠር ነው። ከእምነት ደግሞ አንድ እንጥቀስና መደምደሚያችን ይሁን። እምነት ሲባል እንግዲህ ግንኙነት ከፈጣሪ ጋር ነው። ዘለሰኛ የሚጫወቱ አዝማሪዎች እንዲህ ይላሉ።
ተጣልቻለሁ ከእግዜር ጋራ
አይደል በብዙ በአንድ እንጀራ
እሱ ሆድ የለው አይበላ
ለሰው እያደላ
ሕብረ ቃሉ ‹‹በአንድ እንጀራ›› የሚለው ነው። ሰሙ በእግዚአብሔር ጋር ምግብ እየበላን በብዙ ሳይሆን በአንድ እንጀራ ብቻ ተጣላን ማለት ነው። ወርቁ ግን ጠለቅ ያለ ትርጉም አለው። እንጀራ (ሀብት) መመኘት ብዙም የሃይማኖተኛ ባህሪ አይደለም። ሀብት ለማካባት የሚደረግ ሩጫ ከፈጣሪ ያርቃል ተብሎም ይታሰባል። በሌላ በኩል እንጀራ ብቻ የሚያስብ ሰው ስለማይጾም ከፈጣሪው ይጣላል። እናም የዚህ ቅኔ ወርቅ ሌላ ወንጀል ሳልሰራ ጾም ባለመጾሜ ብቻ (እንጀራ ስለበላሁ) ከእግዜር ጋር ተጣላሁ እያለ ነው። ‹‹ለሰው እያዳላ›› የተባለው አንዱን ሀብታም አንዱን ድሃ ታደርጋለህ ለማለት ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012 ዓ.ም
ዋለልኝ አየለ