አዲስ አበባ፡- በዳኝነት ሂደት ውስጥ ያለው ጣልቃ ገብነት ዳኞችን ነፃነት እያሳጣቸውና ለፍትህ መዛባት እየዳረገ በመሆኑ ዳኞች፣ የፍትህ አካላትና ህብረተሰቡ ችግሩን ለማስቆም መሥራት እንዳለባቸው ተጠየቀ።
በዳኝነት አሰራርና አስተዳደር ሥራ ላይ የሚመክር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው፣ የፌዴራልም ሆነ የክልል የዳኝነት አካላት የህግ የበላይነትን በማስከበር የህገ መንግሥት የበላይነትን ለማረጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ነገር ግን በተለያዩ አካላት የሚደረገው ጣልቃ ገብነት የህግ የበላይነት እንዳይከበርና ዜጎችም በፍትህ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲያጡ አድርጓል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ እንደገለጹት፣ በቅርቡ የዳኝነት ነጻነትና ጣልቃ ገብነትን በተመለከተ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል። በዚህም ቃለ መጠይቁን ከሞሉት 87 በመቶ በሥራቸው ጣልቃ ገብነት መኖሩንና ከዳኞች በነጻነት መወሰን ጋር በተያያዘ ችግር መኖሩን አረጋግጠዋል። ይህ ችግር ደረጃው ቢለያይም በክልል ፍርድ ቤቶችም የሚታይ ሲሆን በተለይ በሶማሊያ፣ አፋር፣ ጋምቤላና ኦሮሚያ በስፋት ይስተዋላል።
አንዳንዶቹ ጋር ጣልቃ ገብነቱ በግልጽ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዳኞች ላይ የስነ ልቦና ጫና ማድረስ፣ ማስፈራራትና እስከ ማሳሰርም የሚደርስበት ግዜ እንዳለ አቶ አመልክተዋል፡፡
ጣልቃ ገብነቱ የሚፈጸመው ከመንግስት አስፈጻሚ አካላት ብቻ ሳይሆን ከተደራጁ ቡድኖችና ግለሰቦችም ጭምር መሆኑን ጠቁመው፣ ዳኖቹም ሆኑ አስፈጻሚ አካላትና ህዝቡ ነፃና ገለልተኛ የዳኝነት ሥርዓት እንዲፈጠር መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልልም ችግሩ ሰፊ ነው የሚሉት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኦባንግ ጁሉ፣ በቀጥታ በህግ ስር ያለ መዝገብ ውስጥ ጣልቃ በመግባት «እኔ ያሰርኳቸውን ሰዎች ለምን ትፈታለህ፣ ከሥራ እናስለቅቅሃለን›› እስከማለት የተደረሰበት ጊዜ እንዳለ ተናግረዋል።
ጣልቃ ገብነት በተደጋጋሚ ይስተዋላሉ የሚሉት አቶ ኦባንግ፣ በሥራ አስፈጻሚው በኩል ያለውንም ችግርም ገልጸዋል፡፡ ይኸውም ‹‹በ2010 የክልሉ ፓርላማ ለሥራ ማስኬጃ በጀት 3 ሚሊዮን ብር ያጸደቀ ቢሆንም የተሰጠው ግን 300 ሺ ብር ብቻ ነበር። ለምን ይቀነሳል ብለን ብንጠይቅ ምላሽ አልተሰጠንም፡፡ እነዚህ ጣልቃ ገብነቶች የማይስተካከሉ ከሆነ አጠቃለይ የፍትህ ሥርዓቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል›› ሲሉ አመልክተዋል።
የሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አብዱላሂ ሰይድ «የክልሉ ፕሬዚዳንት ካለሥልጣናቸው የክልሉን የዳኞች ጉባኤ ይሰበስቡ ነበር» ሲሉ አስታውሰው፣ የጉባኤው አመሰራረትም ሆነ አካሄድ ከዳኝነት ሥራ ጋር የማይስማማ በመሆኑና በርካታ ችግሮች ተፈጥረው ስለነበር ለውጡን ተከትሎ እንደ አዲስ እንዲዋቀር ለማድረግ ተገደናል ብለዋል።
እንደ አዲስ በተዋቀረው የዳኞች ጉባኤ አራት ዳኞች፣ ሁለት የፓርላማ አባላት፣ ሁለት ጠበቃዎችና አንድ ከህዝብ ተወካይ አሉት ብለዋል። ጉባኤውም በክልሉ ያለው አጠቃለይ የፍርድ ቤት ሥርዓት የተስተካከል ስላልነበር በአስራ አንዱ ዞኖችና በ93ቱ ወረዳዎች እንደ አዲስ ምደባ ለማድረግ መገደዱን ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ