የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ በፖሊሲና ስትራቴጂዎች ደረጃ ትኩረት የተሰጠው ቢመስልም የታለመለትን ማሳካት አልቻለም፡፡ በሌሎች አለማት በተለይም በታዳጊ አገራት ዘንድ የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን እንቁ ባለሙያዎች እንደሆኑ በጥናቶች ተመላክቷል። የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ያሉበትን ችግሮች በመዳሰስ በፍኖተ ካርታው መዳረሻው ምን ይሆን? የሚሉትን ጉዳዮች ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡
ምን ችግሮች ነበሩበት?
የ1994 ዓ.ም የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በግንባታ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ ጥበብ፣ በንግድ ክህሎት እና በመሰል ዘርፎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዲችሉ አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡ ተስፋ ያለው ለውጥ መታየት ባለመቻሉ የተነሳ ለበርካታ ጊዜ ከተለያዩ ተቋማት ስትራቴጂዎች ጋር በማጣመር ይዳሰስ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ፡-(በከተሞች ኢንዱስትሪ ልማት ፓኬጅ 1996 ፣በትምህርት ዘርፍ ልማት ፕሮግራም 1996 ፤በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ 1994 ዓ.ም…ወዘተ) እንደተጣመሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ራሱን የቻለ ፖሊሲ ነበረው ለማለት ባያስደፍርም ከ13 አመታት በፊት ተሞክሮ ነበር፡ ከ10 ዓመታት በፊት ፓኬጅ እንደተዘጋጀለትም የሰነድ መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡
ችግሮች የሚጀምሩት ከምልመላ ነበር፡፡ ፍላጎትን መሰረት አድርጎ የሚገባበት ሳይሆን ተወዳዳሪ ያልሆኑ(10ኛ ብሔራዊ ፈተና ማለፍ ያልቻሉ) ተማሪዎች የሚገቡበት ነበር፡፡በዚህ የተነሳ የሚጠቅም ተደርጎ በማህበረሰቡም ሆነ በተማሪዎች ዘንድ የሚታይ አልነበረም፡፡ 35 ሚሊዮን የሚጠጋው የአገሪቱ ሰራተኛ ሀይል በአማካኝ በትምህርት ደረጃውና በምርታማነቱ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድሎች የሚፈጥሩ የግል ተቋማት ባለመኖራቸው በከተማም ሆነ በገጠር የሥራ አጦች ቁጥር ጨመረ፡፡ በመሆኑም ይሄን ችግር ሙያ ነክ ክህሎትና እውቀት በማስጨበጥ በራሳቸው ሥራ መፍጠር ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በፋብሪካ ሰራተኛ ተቀጣሪነት ተሰማርተው ብቁ ባለሙያ መሆን ይችላሉ የሚል እሳቤ የተሰነቀ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን በሰለጠኑበት ብቁ ሆነው ችግር መፍታት አልቻሉም፡፡ ተምሮ የሚመረቀውና የብቃት ማረጋገጫውን ተፈትኖ በማለፍ በስራ ላይ የሚሰማራው የሚጣጣም አልሆነም፡፡ በሌሎችም በርካታ ችግሮች የተተበተበ ዘርፍ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በሥልጠና ፣በብቃት ምዘና፣ በምልመላ፣በትምህርት ማሻሻል እና በሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮችም ሰፊ ችግሮች መስተዋላቸው መፍትሄ መሻት አስገዳጅ እየሆነ መጥቷል። አሁን ላይ በዘርፉ ምን ለውጦች ተፈጠሩ?
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ እንደገለጹት፤ የአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት አዲስ ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናም በራሱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ነቅሶ በመለየት መፍትሄ እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለው እንዳሉት፤ አለም ያደገው በተሟላ ሁኔታ የቴክኒክና ሙያ የትምህርትና ሥልጠና አሰጣጥን በመተግበር እንደሆነ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ በእውቀት የታጨቀ እንጂ በክህሎት የተገነባ አልነበረም፡፡ በመሆኑም እውቀትም ክህሎትም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ እያደጉ የሚሄዱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርቶች ይሰጣሉ። ተማሪዎቹ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ፍላጎታቸው ላይ ተመስርቶ ተቀዳሚ ምርጫቸው መሆን አለበት፤በሙያቸውም እስከሚፈልጉት ደረጃ ድረስ ማደግና ራሳቸውን ማሻሻል አለባቸው።
በመሆኑም ከ12ኛ ክፍል አገራዊ ፈተና እንዳጠናቀቁ በፍላጎታቸው መርጠውት የሚገቡበት እንደሚሆን ገልጸዋል። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ክብረት በበኩላቸው፤ በቴክኒክና ሙያ የተደረጉት ለውጦች በዋናነት በአራት የሚከፈሉ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው መሰረታዊ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት በተመረጡና በተደራጁ ውስን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ራሱን ችሎ ይሰጣል፡፡ ተማሪዎች ግንዛቤውን ይዘው 12ኛ ክፍል ሲያጠናቅቁ ወደፈለጉት መግባት ይችላሉ፡፡ ሁለተኛው መደበኛ የሙያ ሥልጠና የሚጀምረው 12ኛ ክፍል አጠናቀው የሚገቡበት ነው፡፡ መደበኛ ያልሆነው ስልጠና አሁን ባለበት እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
አቶ ሀብታሙ እንዳብራሩት፤ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ደረጃዎችን በሚመለከት ከደረጃ አምስት በላይ ዝግ የነበረው አሰራር አሁን ባለው ሁኔታ እስከ ፒኤችዲ ማሳደግ ችሏል። እስከ ሙሉ ፕሮፌሰርነት /ደረጃ ስምንት/ ድረስ አድጓል፡፡
ደረጃ አንድ ጀማሪ ሙያተኛ፣ ደረጃ ሁለት ረዳት ሙያተኛ፣ደረጃ ሶስት ሙያተኛ፣ደረጃ አራት ከፍተኛ ሙያተኛ፣ ደረጃ አምስት መሪ ሙያተኛ ፣ደረጃ ሥድስት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ደረጃ ሰባት የማስተርስ ዲግሪ እና ደረጃ ስምንት የፒኤች ዲግሪ ሆኗል፡፡
የመምህራንን ሁኔታ በሚመለከት፡- ደረጃ አንድ እና ደረጃ ሁለት የሚያስተምሩት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ናቸው። ከዚያ በላይ ያሉት ደረጃዎች ማስተርስና በላይ ይጠይቃሉ። በተጨማሪም የሙያ ብቃት ምዘና ያላቸው አሰልጣኞች እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ በዚህ የተነሳ እስከአሁን የነበሩት አሰልጣኞች ፕሮፋይል ይቀየራል፡፡ በ‹‹ሲ›› ደረጃ የነበሩ አሰልጣኞች ሥልጠናው በ2013 ዓ.ም እስኪጀመር ድረስ መማር(ማሻሻል) ይኖርባቸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲ ትምህርትን በተመለከተ፡- ቅድመ ምረቃ አራት አመት ይሆናል፡፡ የመጀመሪያ አመት ትምህርትም የ21ኛውን ክፍለ ዘመን ክህሎትና አስተሳሰብ በሚመጥን መልክ መሆን አለበት፡፡
የዩኒቨርሲቲዎችን አደረጃጀቶችን በሚመለከት ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ተልዕኮዎች ላይ እንዲያተኩሩ ይደረጋል፡፡ በተለያዩ መስኮች የልህቀት ማዕከል ይሆናሉ። የሪሰርች ፣የመምህርነት፣ ‹‹አፕላይድ››፣ ዩኒቨርሲቲዎች ተብለው በተልዕኳቸው መሰረት ይወሰናሉ፡፡
ሀገር አቀፍ የጥራት ማዕቀፍ የሚሰራ ሲሆን ጎን ለጎንም የቴክኒክና ሙያ የብቃት ማረጋገጫ ማዕከላት ይደራጃሉ። ቴክኒክና ሙያዎች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተቀናጅተው የሚሰሩት ይሆናል፡፡
ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ትምህርት ደረጃ አንድና ሁለት ክልሎች በሚመርጡት ቋንቋ ይሰጣል። ሌሎች የውጪ ቋንቋዎች በፍላጎቶቻቸው ላይ ተመስርቶ በአማራጭነት ይሰጣል፡፡
የጎልማሶች ትምህርት ስልጠና ራሱን ችሎ በሚዘጋጅ ስትራቴጂ የሚመራ ሲሆን ቴክኒክና ሙያ ተቋማትንም የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የአርሶ አደር ስልጠና በቴክኒክና ሙያ በኩል የሚሰጥ በመሆኑ ነው፡፡
የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ጉዳዮች ትኩረት ይሰጣቸዋል፡፡ በፍኖተ ካርታው በተመለከተው መሰረት በትምህርቱ ማጠናቀቂያ ወቅት የተቀመጠውን መስፈርት ማሟላት ግዴታ ይሆናል፡፡
የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲን በተመለከተም በአዲስ የተሻሻለ ሲሆን የቴክኒክና ሙያም አብሮ የሚለወጥ ይሆናል፡፡
አለም አቀፍ የምዘናና ውድድር ሥርዓትን በተመለከተ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ምዘናዎችና ውድድሮች መሳተፍ ይኖርባታል፡፡ ተሳታፊም ትሆናለች፡፡ ቴክኒክና ሙያን ጨምሮ በየዘርፉ እንዲጠናከርና አለም አቀፍ ስታንዳርድን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ይደረጋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በቀጣይ ምን ይስሩ?
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንደተናገሩት፤ በ2013 ዓ.ም በአዲሱ አሰራር ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሰልጣኞችን እስኪቀበሉ ድረስ በትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው ፍኖተ ካርታ የተጠቀሱ ዋና ዋና ጉዳዮች ከቴክኒክና ሙያ አንጻር መተግበር የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ማዕቀፎች ያዘጋጃሉ፤ ለባለድርሻዎቻቸው ያስተዋውቃሉ፡፡ በየደረጃው የሚፈለጉ የሰው ሀይሎችን ደረጃ በትምህርት ፖሊሲው ትይዩ ማብቃት የሚያስችሉ ይዘቶች እንዲካተቱ ከአገራዊ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጋር ተናበው ይሰራሉ። በተለይም ከደረጃ ማደግ ጋር ተያይዞ አሁን ያለው ገበያ የሚፈልገውን የሰው ሀይል ለይቶ ማሰልጠን ተገቢነት ስለሚኖረው በትኩረት ይሰራሉ። በሌላ በኩል ምሩቃን ምዘናን የማይፈልጉት(የሚጠሉት) ለምን እንደሆነ ለይቶ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚሰሩም አብራርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 1/2012
ሙሐመድ ሁሴን