- በ170 ተማሪዎች ላይ የአንድ ዓመት ቅጣትና እስከ መጨረሻው ከዩኒቨርሲቲዎች የማባረር እርምጃ ተወስደ
አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል እንዲሁም በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች እየተከሰተ ያለውን ረብሻ ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም እና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራን ለማከናወን ለመላው የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብና ለወላጆች ጥሪ ቀርቧል፡፡
170 ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲዎች የረብሻ ድርጊት ላይ በመሳተፋቸው ለአንድ ዓመት በትምህርት ገበታ ላይ እንዳይሳተፉ ከመቅጣት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ከዩኒቨርሲቲዎች የማባረር እርምጃ መወሰዱም ተጠቁሟል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጋራ ትናንት መግለጫ በሰጡበት ወቅት፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ድኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንደተናገሩት፤ 99 በመቶ የሚሆነው ተማሪ የመማር ፍላጎት አለው።ነገር ግን በማያውቀው ጉዳይ ትምህርቱ እየተስተጓጎለበት ይገኛል።ከሌሎች በሚደርሰው ማስፈራሪያ ዩኒቨርሲቲዎችን ለቆ እየወጣ መሆኑ ታውቋል።
ይህን ችግር በመቅረፍ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ለማከናወን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ያለ የከተማ ህብረተሰብ፤ የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብም ሆነ ወላጆች መንግሥትን በመደገፍ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
‹‹ከሌሎች አካላት ገንዘብ እየተከፈላቸው በባንክና በእጃቸው የውጭ ምንዛሬ ሳይቀር የሚያንቀሳቅሱ ተማሪዎች ተገኝተዋል›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በደረቅ ወንጀል የተሳተፉ የሰው ህይወት ያጠፉና አካል ያጎደሉት ላይ ምርመራ ከማካሄድ ባሻገር ባለፉት 15 ቀናት ብቻ በዩኒቨርሲቲዎች የረብሻ ድርጊት ላይ በመሳተፋቸው ለአንድ ዓመት በትምህርት ገበታ ላይ እንዳይሳተፉ ከመቅጣት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ከዩኒቨርሲቲዎቹ የማባረር እርምጃ የተወሰደባቸው 170 ተማሪዎች መኖራቸውንም አመልክተዋል።280 ተማሪዎች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን፤ በቀጣይ ቁጥራቸው ከዚህም በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል ተናግረዋል።
ረብሻውን በመቀስቃስም ሆነ በማባባስ በኩል ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞችም ጭምር መሳተፋቸው በመታወቁ ከ10 በላይ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የሥራ ውላቸው ተቋርጧል።የደሞዝ ቅጣትን ጨምሮ የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎች የተሰጣቸው መኖራቸውንም ዶክተር ሳሙኤል ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹን በ3ት በመክፈል 8 ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ወደ ትምህርት የተመለሱ መሆኑን፤ ሌሎች 8ት ተቋማት ደግሞ በከፊል ትምህርት ተቋርጦባቸው እንደሚገኝ እና 4ቱ ተጨማሪ ሥራ የሚፈልጉ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የትምህርት ፕሮግራሙን በመከለስ የመማር ማስተማር ሥራው የሚካሄድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ጨምረውም መማር ማስተማሩ በሰላም እንዲካሄድ ፍላጎት ያላቸው የዩኒቨርሲቲ አካባቢ የከተማ ወጣቶች እና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ለሰጠው ጥቆማ አመስግነው፤ ወጥተው የነበሩ ተማሪዎችን የመመለስ ሥራ እንደሚሰራ እና በዚህ ላይም መንግሥት የመምህራንን እና በተለይም የወላጆችን ድጋፍ የሚፈልግ መሆኑን አመልክተዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፋንታ በበኩላቸው፤ ከ50 በላይ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ገንዘብ ተከፍሏቸው ረብሻ በማስነሳት ላይ ተሰማርተው የነበሩ ተማሪዎች መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም ከውስጥ ጥበቃ ጀምሮ መምህራን እና የተለያዩ የአስተዳደር ሠራተኞች ተማሪ ከተማሪ ጋር እንዲጋጭ ሲሰሩ እንደነበር መታወቁን አብራርተዋል።በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የካፌ ሥራን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ አካላት ረብሻ በማስነሳት በኩል ሚና የነበራቸው ሲሆን፤ አብዛኞቹ በውጭ ማህበረሰብ እና በተማሪዎች ጥቆማ የተያዘ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ችግሩ እየተፈጠረ ያለው ለውጡን የማይፈልጉ አካላት ዩኒቨርሲቲ የሚፈጠር ችግር መላውን ህዝብ ይነካል፤ ወሬው ለዓለም ይደርሳል በሚል አቅደው የሚሰሩት መሆኑን አመልክተው፤ በተማሪዎች መካከል ያለው የሃይማኖትና የብሔር ብዝሃነትን እንደመሣሪያ የተጠቀሙበት መሆኑንም አብራርተዋል።
ግጭቱን ለማስቆም የዩኒቨርሲቲው አካባቢ ነዋሪዎች፤ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ቤተሰብ ሃላፊነቱን በመወጣት ከመንግሥትና ከፖሊስ ጎን እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2012
ምህረት ሞገስ