– ከውጭ ተጽዕኖ ነፃ ያደርጋል
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ይፋ ያደረገችው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በአግባቡ ከተመራ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እና ከውጭ ተጽዕኖ ነፃ እንድትሆን እገዛ እንደሚያደርግ ተገለፀ።
ማሻሻያውን በማስመልከት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሃሳባቸውን የሰጡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች መካከል በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ፍሬዘር ጥላሁን እንደሚናገሩት፤ አገር በቀል ኢኮኖሚ የሚባለው የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ፖሊሲ ሊወጣ ነው። ኢትዮጵያ አገር በቀል ኢኮኖሚ መርህ በመከተል ለውጥ ለማምጣት ማሰቧ ጠንካራና የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለመመስረት እገዛ ያደርግላታል።
‹‹ኢትዮጵያ ካላት ሀብት ውስጥ የሰው ሃይል ተጠቃሽ ነው›› የሚሉት አቶ ፍሬዘር፤ አገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻው የሰው ሀብቱ ላይ እውቀትና ክህሎት በመጨመር ቴክኖሎጂ እንዲመጣ በማድረግ ዕድገት የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል:: በአገሪቱ ያሉትን ሀብቶች ለመጠቀም ቴክኖሎጂ ለማሳደግ እና መሰረተ ልማት ለመገንባት የሰው ሃይሉ መጠናከር እንዳለበት ጠቅሰዋል።
ያሉትን የመሬትና የሰው ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ የኢኮኖሚ ዕድገት ለመፍጠር የአገር በቀል ኢኮኖሚ ከነውስንነቶቹ ተፈፃሚ መሆን እንደሚችል ገልፀዋል።
‹‹በራሳችን እናድጋለን ሲባል መጀመሪያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መታወቅ አለበት።ነባራዊ ሁኔታው ካልታየ ወደ ተሳሳተ መንገድ ይወስዳል::›› በማለት የጠቀሱት አቶ ፍሬዘር፤ የኢኮኖሚው ችግር ሳይለይ መፍትሄ መስጠት እንደማይቻል አመልክተዋል:: የኢኮኖሚውን ድክመት በተለይ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ የአገር ውስጥ ቁጠባ እና የብድር አመላለስ ሁኔታው በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ መላኩ እንደሚናገሩት፤ አገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በአግባቡ መምራት ከተቻለ ያለምንም የውጭ ተጽዕኖ በራስ አቅም ኢኮኖሚውን ማሳደግ ይቻላል::
በማሻሻያው የአገሪቱን ነባራዊ ኢኮኖሚ ተረድቶ ድክመቶችን በማረም እና ጥንካሬዎችን ማስቀጠል ከተቻለ ውጤት ይመጣል።ይህ ሲደረግ የሰውና የመሬት ሀብትን በራስ አቅም መጠቀም ይቻላል።
ማሻሻያው አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ተግባር ላይ መዋል የሚችል ነው።አገሪቱ ያላትን የሰውና የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ የኢኮኖሚ ማሻሻው ሊሳካ ይችላል።ነገር ግን ማሻሻያው ወደ ተግባር ሲገባ ፈታኝ ነገሮች ይኖራሉ።
‹‹ማሻሻያውን በራስ አቅም መሰራት መቻሉ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ፤ በምሳሌነት ታዳጊ አገራት ላይ የበለፀጉ አገሮችን ፍላጎት ማስፈፀሚያ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ በሆነበት ወቅት ከዚህ ነገር ነፃ ሆኖ በራስ አቅም ለመሥራት መንቀሳቀስ መልካም መሆኑን አመልክተዋል።
የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጥናቶችን በአገር ውስጥ ባለሙያዎች መሥራት እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል።ነገር ግን በአገሪቱ ቁጠባ አነስተኛ በሆነበት ሁኔታ ማሻሻያውን በአገር ውስጥ ለመሸፈን መታሰቡ፣ ማሻሻያውን ማስፈፀም የሚችል በየደረጃው የሰው ሃይል መኖሩ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ደካማነት በአግባቡ መታየት እንዳለባቸው አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2012
መርድ ክፍሉ