የበዓል ሰሞን መሠረታዊ ምርቶች ከመወደዳቸውም ባሻገር የፍላጎት መጠንም ይጨምራል።ይህን ለመታዘብ ደግሞ የገበያ ቦታዎችንና የሸማች ሕብረት ሠራ ማህበራትን ሱቅ መመልከት በቂ ነው።
ዛሬ በተለያዩ ቦታዎች የበዓል ገበያ ትርምስ የሚበዛበት ወቅት በመሆኑ የምርት እጥረትና የዋጋ ውድነት ብሶት ጎልቶ ይሰማል።ይህንን ቀደም ብሎ ለማረጋጋትና የህዝቡን ብሶት ለመቀነስ የሕብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲዎችና ሸማች ማህበራት በጥምረት እየሠሩ ይገኛሉ።
ወይዘሮ እልፌ ታደሰ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ንዑስ ቀበሌ ዘጠኝ በሸማቾች ሱቅ መዛኝና ንብረት ተረካቢ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ሕብረተሰቡ በተለይም በበዓል ወቅት የሚፈለገው ሳሙና፣ ፓስታ ወይም መኮረኒ አይደለም።የህብረተሰቡ ፍላጎት ስኳር፣ ዱቄት እና ዘይት ነው።
ይሁን እንጂ በድጎማ የሚመጣው ዘይትና ዱቄት እጥረት አለ።ህብረተሰቡ በብዛት የሚፈልገው በድጎማ የሚመጣውን ዘይትና ዱቄት ነው። ምክንያቱም በፈሳሽ መልክ የሚመጣውን ዘይት ለመግዛት አቅም የለም።ስለዚህ መንግሥት የህብረተሰቡን አቅም ከግምት በማስገባት እነዚህን በድጎማ የሚገቡ ዱቄትና ዘይት በስፋት ማቅረብ አለበት።
‹‹ከክልል አምራች ዩኒየኖች ጋር በመተባበር ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎችን አስመጥተናል›› የሚሉት ደግሞ በአራዳ ክፍለ ከተማ ተስፋ ብርሃን የሸማቾች የሕብረት ሥራ ማህበር ሃላፊ አቶ ጌታሁን ደስታ ናቸው። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ቀደም ብሎ ዝግጅት በማድረግ ከስኳር፣ ከዱቄትና ከዘይት በተጨማሪ ሽንኩርት፣ ጤፍ፣ ቂቤ፣ የቁም ከብት፣ በግ፣ ዶሮ እንቁላልና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችም መጥተው ለሕብረተሰቡ በመከፋፈል ላይ ይገኛሉ።
እንደ አቶ ጌታሁን ገለፃ፤ በማህበሩ አቅም የሚሠሩ ሥራዎች በቂ ናቸው ማለት አይቻልም። መንግሥት በድጎማ ከሚያቀርባቸው ምርቶች መካከል ዱቄት ከባለፈው የተሻለ ቢሆንም አጥጋቢ አይደለም። በድጎማ የሚገባው ዘይት መደበኛውም
ሆነ ለበዓል ተብሎ የተሰጠ ባለመኖሩ ከፍተኛ እጥረት አለ። ምክንያቱም አለ በጅምላ የተባለው ተቋም ተገቢውን ሃላፊነት እየተወጣ ባለመሆኑ ነው። ድሃው ህብረተሰብ ደግሞ ፈሳሽ ዘይት የመግዛት አቅም የሌለው በመሆኑ መንግሥት ዘይቱ ላይ ያለውን ችግር ቢቀርፍ መልካም ነው።
በወረዳ ደረጃ የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበሩ በራሱ አቅም ከአምራች ድርጅቶች 340 ካርቶን የተለያየ መጠን ያለው ፈሳሽ ዘይት፣ 200 ኩንታል 1ኛ ደረጃ ዱቄት፣ 200 ኩንታል ጤፍ፣ 200 ኩንታል ሽንኩርት፣ 100 ኪሎ ቅቤ እና በርካታ የኤልፎራ ዶሮዎችና እንቁላሎች ማቅረባቸውን ይናገራሉ።
ከእነዚህ በተጨማሪም አርሶ አደሩንና ከተሜውን ለማገናኘት ለመጀመሪያ ጊዜ በጎችን ማቅረብ የተቻለ ሲሆን፤ ዋጋቸውም ከ2ሺ 500 እስከ 2ሺ 800 ድረስ መሆኑን ይገልፃሉ። እንዲሁም ለሥጋ ቤቶች ማከፋፈል እንዲቻል 42 በሬዎች መቅረባቸውን ይናገራሉ። በአጠቃላይ የህብረተሰቡን ፍላጎት ማርካትና ገበያውን ማረጋጋት እንዲቻል ሕብረት ሥራ ማህበራት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳበት ያስረዳሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ዓሊ፤ የገና በዓልን አስመልክቶ ኤጀንሲው ከክልል አምራች ዩኒየኖች ጋር በመተባበር የተለያዩ ለበዓል የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ይጠቅሳሉ፡፡
በዚህም ከወትሮው በተለየ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት በስፋት ታቅዶ በተመጣጠነ ዋጋ ህብረተሰቡ ሳይጎዳ መሸመት እንዲቻል እየተሠራ መሆኑን ይጠቁማሉ።ለአብነት ብር ሸለቆ አካባቢ ከሚገኘው አግሮ ሴፍ ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር የቁም እንስሳትን እያቀረቡ እንደሆነ ይናገራሉ።
በሕብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ የሚረዱ አረጋውያንና ወላጅ አልባ ከአንድ ሺ በላይ ህፃናት ያሉ ሲሆን፤ እነዚህን አረጋውያንና ህፃናት በዓሉን እንደማንኛወም ህብረተሰብ እኩል ማሳለፍ እንዲችሉ ሸማች ሕብረት ሥራ ማህበራቱ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ ያመላክታሉ።
የተለያዩ ምርቶችን የማቅረብ ሥራ የአንድ ሰሞን ተግባር ብቻ መሆን የለበትም የሚሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አረጋ፤ አሁን በሕብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲዎች በኩል ካለፉት ጊዜያት ልምድ በመውሰድ ለህብረተሰቡ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን ሁል ጊዜ በየአካባቢው ተሟልተው እንዲገኙ ተከታታይነት ያለው ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ይህንን አጠናክሮ በመቀጠል ህብረተሰቡን ከአላስፈላጊ ወጪና ግርግር በመታደግ ገበያውን ማረጋጋት ይገባል።ለዚህም ሕብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ሕብረት ሥራ ማህበራት እንደሚታወቀው ሁሉንም የአቅርቦት አማራጭ የሚያሟሉ ሳይሆኑ የተሻለ አማራጭ ሆነው በመቅረብ ለአባሎቻቸውና ለየወረዳው ማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው።
በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ከ11 ሺህ በላይ የሕብረት ሥራ ማህበራት ያሉ ሲሆን፤ አሁን ገበያው ላይ እየተሳተፉ ያሉት ሸማች የሕብረት ሥራ ማህበራት ናቸው። እነዚህ ሸማች የሕብረት ሥራ ማህበራት በአሥሩም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች ተደራጅተው የሚገኙና 800 ሱቆች እንዳሏቸው ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2012
ፍሬህይወት አወቀ