ለብዙ ሰዎች “ዓላማ” ከቃልነቱ ያለፈ በሕይወት ጉዞአቸው የተገናዘበ ትርጉም የለውም፡፡ የአንዳንዶቻችን የሕይወት ታሪክ ሸለቆ ደርሶ መቆም እንደተገደደ ከተራራ አናት ላይ እንደተፈነቀለ አለት ከዕለት ወደ ዕለት ከማናልፈው ሞት እስከምንደርስ ድረስ እንደመንከባለለ ያለ ሂደት ነው፡፡
ሌሎቻችን ደግሞ ሕይወታችን በዓላማ የምንመራው እንኖርበታለን ያልነውን ዓላማ የሚገዳደሩ ሁኔታዎች እስካልገጠሙንና ኑሮ “አልጋ በአልጋ” እስከሆነልን ድረስ ነው፡፡
ዓላማቸው እና ግባቸው አድሮ መገኘት ከሆነው በየምዕራፉ ተግዳሮት ሲገጥማቸው ጎመን በጤና እያሉ መንገድ ከሚቀያይሩት … ለየት ያለ ለዓላማቸው የጨከነ ማንነት ያላቸው ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የዛሬ የህይወት እንዲህ ናት አምድ እንግዳችን ዶክተር ጥላዬ ጌቴ አንዱ ናቸው፡፡ እንግዳችን ባለፉት 34 ዓመታት በፔዳጎጂ መምህርነት፣ በርዕሰ መምህርነት፣ በዞን አመራርነት፣ በዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነት፣ በክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊነት፣ በትምህርት ሚኒስትር ዴኤታነት እና በትምህርት ሚኒስትርነት ያገለገሉ ናቸው፡፡ ስለሆነም ከእርሳቸው ህይወት ብዙ ቁምነገር ትቀስማላችሁና ልምዶቻቸውን እንድትቋደሱ አቀረብንላችሁ፡፡
ልጅነት
ትውልዳቸው አማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ግሼ አባይ በምትባል የወረዳ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ የተለያዩ ጨዋታዎችን ተጫውተው ያደጉት ናቸው፡፡ ይሁንና ወረዳዋ ከተማ ነክ በመሆኗ ሞፈርና ቀንበር ይዘው አላረሱም፤ ከብትም ቢሆን አልጠበቁም። ስለዚህም በዚያ ውስጥ የሚታዩትን ጨዋታዎች አልተጫወቱም። ነገር ግን ከተሜዎች የሚወዱትን ጨዋታ ማለትም ብይና ኳስ ተጫውተዋል፡፡ ጎበዝ ሯጭና የቅርጫት ኳስ ተጨዋችም እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ከሌሎች ትምህርት ቤቶች ጋር በሚወዳደሩበት ጊዜ ሁሌ አሸናፊ ነበሩ፡፡
ዶክተር ጥላዬ ዝምተኛ፣ አድማጭና ተመልካችም ልጅ ሲሆኑ፤ ከመናገር በፊት ብዙ ማድመጥና ጉዳዩን በትኩረት ማጤንን ቅድሚያ የሚሰጡም ናቸው። ለመምህራንም ሆነ ለጎረቤት ታዛዥ፣ ለቤተሰብም የተባሉትን የሚፈጽሙ እንዲሁም ከጓደኞቻቸው ጋር በፍቅር መጫወት የሚወዱም ናቸው፡፡
በንግድ የሚተዳደሩት ቤተሰቦቻቸው ለስነ ምግባር አትኩሮት ስለሚሰጡ ለዶክተር ጥላዬም ከሁሉም ሰው ጋር ተግባብቶ መኖርን አስተምረዋቸዋል፡፡ በእርግጥ አንድ ነገር አለማወቃቸው ዛሬ ድረስ ይቆጫቸዋል፡፡ ይኸውም የግብርናን ሥራ ሲሆን፤ አያቶቻቸው ጋር እንኳን ሲሄዱ ብዙ መስራት እንዳልቻሉ አጫውተውናል። ሁሉን ነገር ማወቅ እንዳለባቸው ቢረዱም በትንሹ አያቶቻቸው ጋር በቆዩበት ጊዜ ነው ነዶ እንኳን መጫን የለመዱት፡፡
ግብርናውን አውቃለሁ የሚያስብል አንድም ነገር እንዳልነበራቸው ያጫወቱን ዶክተር ጥላዬ፤ ለቤተሰቡ ዘጠነኛ ልጅ በመሆናቸው ብዙም በሥራ የሚያግዙት ነገር እንዳልነበር ይናገራሉ። ነገር ግን በሥራ ወዳድነታቸው በቤተሰብ ትዕዛዝ ሳይሆን በራሳቸው እንጨት በመፍለጥ፣ የተፈለጠውን በማቅረብ፣ ውሃ በመቅዳትና በመላላክ ቤተሰቦቻቸውን ያገለግሏቸው ነበር፡፡
በትምህርት ቤት ድራማ እንደሚሰሩ፣መምህራን የሚጽፉትን ግጥም የተለያዩ በዓላት ላይ ህዝብ በተሰበሰበበት እንደሚያቀርቡ ያጫወቱን እንግዳችን፤ ተመርጠው በአደባባይ ይህንን ማድረጋቸው ደፋር እንዳደረጋቸው ያስረዳሉ፡፡
የስማቸው ስያሜ እንዴት እንደተሰጠ የማያውቁት ዶክተር ጥላዬ፤ ጥላዬ የሚባለው ስም በአካባቢው የሚሰጠው ከለላ፣ መከታ፣ የችግር ጊዜ ደራሽ ለማለት ሲፈለግ የሚጠቀሙበት ነው። ስለዚህም ከዚህ ጋር ተያይዞ ስሙን ያወጡልኝ ይመስለኛል፡፡ ግን ይህንን ስለሆንኩ ነው የምለው የለኝም ይላሉ፡፡
እንግዳችን ሁሌ ህልማቸው ዩኒቨርሲቲ መግባት ነው፡፡ ምክንያቱም ወንድሞቻቸው በሙሉ አዲስ አበባ በመማር ዩኒቨርሲቲን አይተው የተሻሉ እንደሆኑ አስመስክረዋል፡፡ ስለዚህም እርሳቸውም ይህንን ማድረግ ይፈልጉ ነበር፡፡ በእርግጥ ለዚህ ሁሉ መሰረቱ ቤተሰቦቻቸው እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ የትምህርትን አቅም በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ስለሆነ በሚገባ ያውቁታል፡፡ እናም ከሥራ ይልቅ ወደ ትምህርታቸው እንዲያተኩሩ ይገፏፏቸዋል፡፡
ጥር 21 1953 ዓ.ም የተወለዱት ዶክተር ጥላዬ፤ አብዛኛው የእድገት ቦታቸው ባህርዳር እንደነበር ያነሳሉ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንም የያዙት በዚያው በባህርዳር ከቤተሰባቸው ሳይርቁ ነውና የልጅነት ጊዜያቸው አብቅቶም ከቤተሰብ አልተለዩም ነበር፡፡ ሁልጊዜ ልጅ እንደነበሩ አድገዋል፡፡
ከግሼአባይ እስከ ባህርማዶ
በኃይለስላሴ ጊዜ ነበር ትምህርትን ሀ ብለው የጀመሩት፡፡ በዚህም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤታቸውን ደጃዝማች ዘለቀ ደስታ ትምህርት ቤት በመግባት ተማሩ፡፡ እስከስድስተኛ ክፍልም ትምህርትቤቱ ውስጥ ከቆዩ በኋላ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ፍኖተሰላም መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አመሩ፡፡
ሰባትና ስምንተኛ ክፍልን በዚህ ካጠናቀቁ በኋላ ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ባህርዳር አቅንተው አጼ ሰርጸድንግል መላክሰገድ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወይም የዛሬው ጣና ሀይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገቡ፡፡
ትምህርት ቤቱ በወቅቱ አጠቃላይ ትምህርት የሚባል ፕሮግራም ነበረው፡፡ ይህም የሙያና የቀለም ተብሎ በሁለት ተከፍሎ ይሰጥበታል፡፡ በዚህም እርሳቸው የሙያ ትምህርትን በመምረጥ የግብርና ተማሪ ሆኑ፡፡ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ መሆን ባለመውደዳቸውም ነበር ወደሙያው ያዘነበሉት። በዚህም ጎጃም ክፍለአገር ውስጥ ሁለት ቦታ ብቻ ላይ በሚገኘው ትምህርት ቤት ማለትም በአጼሰርጸድንግል መላክሰገድ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን መከታተል እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡
ትምህርቱ የሚሰጠው በክፍለአገሩ ባህርዳርና ደብረማርቆስ ነው፡፡ በዚህም በባህርዳር ጣና ሀይቅ ትምህርት ቤት ገብቻለሁ የሚሉት እንግዳችን፤ አላማቸው ሳይንስ ማጥናት እንጂ የታሪክ ተማሪ መሆን አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በባህሪያቸው የሚሸመደድ ትምህርት ብዙም አይወዱም፡፡ ስለዚህም የቀለሙን በመተው ወደ ሙያ ትምህርቱ ገብተዋል፡፡
ቀጥሎ ያለው የትምህርት መስክ መረጣ ላይ ግን ይህ ፍላጎታቸው መቀጠል አልቻለም ነበር፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ ደረጃ ያለው አንድ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት የተሰጣቸውን የትምህርት መስክ ተቀብለው መማር ብቻ ነው እጣፋንታቸው፡፡
የትምህርት ምርጫ ፔዳጎጂ ላይ እንደጣላቸውና በግዴታም ቢሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር በሚገኘው የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ “ፔዳጎጂ” ትምህርት ክፍል እንዲገቡ እንደሆኑ የሚናገሩት ዶክተር ጥላዬ፤ በፔዳጎጂ ትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ውጤት በመያዝ ትምህርታቸውን ሊያጠናቅቁ ችለዋል፡፡
በወቅቱ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት የሚያመጣው ጥቂት በመሆኑና በተመደቡበት መስክ መማር ግዴታ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ጥላዬ፤ መግባታቸውን ብቻ በማየት ተደስተው እንደነበር አይረሱትም፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪው ካለቀ በኋላ ትምህርት ፍለጋ ከባህር ማዶ የተሸገሩት እንግዳችን፤ በኖርዌይ ኦስሎ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ኢንተርናሽናል ኤንድ ኮንፓራቲቭ ኢዲኩዌሽን ›› በተባለ የትምህርት መስክ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡ ቀጥለው ደግሞ ወደአገራቸው ተመልሰው የተወሰኑ ዓመታትን በዘርፉ ከአገለገሉ በኋላ ለቀጣይ ለትምህርት ወደ ህንድ አገር ተጉዘዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ መሆን እንደሚፈልጉ የሚናገሩት ባለታሪኩ፤ በህንድ ገብተው ‹‹አንድራ›› ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በትምህርት ጥናት እንደያዙም አጫውተውናል፡፡
ከባሌ እስከ አዲስ አበባ
ሥራን የጀመሩት የአንደኛ ደረጃ መምህራንን በማሰልጠንና ለትውልዱ እንዲተርፉ በማድረግ ነው። በዚህም በርካቶች ከእርሳቸው ቀለምን ቀስመዋል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በባሌ ክፍለአገር ሮቤ መምህራን ማሰልጠኛ መምህር ሆነውም ለአምስት ዓመት ያህል በአገለገሉበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ለመሆን በወቅቱ 14 ክፍለ አገር ነበረና ርዕሰ መምህር ለመሆን በቀጥታ አዲስ አበባ ትምህርት ሚኒስቴር በመምጣት መወዳደር ግድ ነው፡፡ እናም እንግዳችንም መጥተው ውድድሩና ተሳተፉ፡፡ ፈተናውንም ወስደው በጥሩ ውጤት አለፉ፡፡ በዚህም ወደ ጎጃም ፈረስ ቤት ናቡሬ የተባለ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሄደው በርዕሰ መምህርነት እንዲያገለግሉ ተደረገ፡፡
በትምህርት ቤቱ ከሶስት ዓመት በላይ እንደሰሩ የሚናገሩት ዶክተር ጥላዬ፤ ይህ የአገልግሎት ጊዜያቸው ሲጠናቀቅ በቀጥታ ወደ ዞን ትምህርት መምሪያ ተሸጋግረው የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት ፕሮግራሞች ቡድን መሪ ሆነው መመደባቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም ስድስት ዓመታትን እንዳገለገሉ ይናገራሉ፡፡
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ጨርሰው ወደአገራቸው ሲመለሱ የአማራ ክልል አቅም ግንባታ ቢሮ የመምሪያ ሀላፊ ሆነው እንደተመደቡት ያጫወቱን ዶክተር ጥላዬ፤ በቦታው ሲደርሱ ቢሮው ገና እየተቋቋመ ስለነበር የትምህርትና ስልጠና መምሪያ ሀላፊ ሆነው እንዲሰሩ መደረጉን፤ በመቀጠል ደግሞ የፖሊሲ ትንተና ሀላፊ ሆነው እንደሰሩ ያነሳሉ፡፡
በእነዚህ ሁለት የሥራ መስኮችም አንድ ዓመት ብቻ ነበር የሰራሁት ብለውናል፡፡ ምክንያቱም የትምህርት ዝግጅታቸው ለተሻለ የስራ ሁኔታ ያሳጫቸው ነበርና የክልሉ መንግስት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አድርጎ ስለሾማቸው ነው፡፡
በክልሉ የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሆነው ለስምንት ዓመት ከአገለገሉ በኋላ ወደ ህንድ ለመማር የሄዱት ዶክተር ጥላዬ፤ በህንድ አገር ዶክትሬታቸውን ከጨረሱ በኋላ በዚያው መቅረትን አልወደዱትም። ብዙ ጓደኞቻቸው ወደተለያዩ አገራት ሲሄዱ እርሳቸው ግን ‹‹አገሬ በለፋችበት እኔነት ለሌላ አገር ብልጽግና አልሰራም›› ሲሉ ወደ አገራቸው መመለሳቸውንና የደብረማርቆስ ዪኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በመሆን መስራታቸውን ይናገራሉ፡፡
በዩኒቨርሲቲው ለሁለት ዓመት ያገለገሉ ሲሆን፤ ለሌሎች አርኣያ ለመሆንም ከፕሬዚዳንትነት ባሻገር የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ያስተምሩ ነበር፡፡ የተለያዩ ችግሮቻቸውን ለመፍታትም ምርምር እያደረጉ የመፍትሄ አቅጣጫም በማስቀመጥ ይታወቃሉ፡፡
በሌላ በኩል በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ተቋሙ የተለያዩ መመሪያዎችና ፖሊሲዎች እንዲኖሩት አድርገዋል፡፡ በተለይም በተለይም በተማሪዎች ስነምግባርና አለባበስ ዙሪያ ህግና ደንብ በማውጣት የማይረሳ አሻራቸውን ያሳረፉ ናቸው፡፡
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ድረስ እንዳይረሳቸው የሚያደርግ የመሰረተ ልማት ሥራም ሰርተዋል።ነገር ግን በእርሳቸው አንደበት ሲገለጽ ‹‹ምንም ከዩኒቨርስቲ አመራሮች የተለየ ነገር ያደረኩት የለም ነው፡፡›› ግን ታሪክን ማንም ሊያጠፋው አይችልምና ስለእርሳቸው ብዙዎች በተለይ ዩኒቨርሲቲው ላይ የሚሰሩ ሰዎች ይህንን ምስክርነታቸውን ከመስጠት ወደኋላ አይሉም፡፡
ዶክተር ጥላዬ፤ ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነታቸው ሲነሱ በአላማ ነበርና በቀጥታ ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ገብተው በሚኒስትር ድኤታነት እንዲሰሩ ተደርገዋል፡፡ ዓመት ከአገለገሉ በኋላ ደግሞ በቀጥታ የሚኒስትር ማዕረጉን ተፈናጠጡና ዛሬ ትምህርት ሚኒስቴር የደረሰበትን ደረጃ እንዲያሳዩ ሆነዋል፡፡ በአራት ዓመት ቆይታቸውም በተለይ በፍኖተካርታው ዙሪያ የሰሩት ሥራ ለስኬታቸው መንደርደሪያ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ዶክተር ጥላዬ ይህንን አደረኩ ማለትን በፍጹም ባይወዱም አንድ ነገር ግን መሸሸግ አልፈለጉም። አይወዱም፡፡ ምክንያቱም ሥራቸው ስኬት ላይ እንዲደርስ ይፈልጋሉና ነው፡፡‹‹ከማንም የተለየ ሥራና ማንነት ባይኖረኝም የፍኖተ ካርታ ሥራው ግን ለእኔ ትልቅ አሻራዬን ያሳረፍኩበት ነው›› ይላሉ፡፡
በሚሰሩት ሥራ አንድም ቀን እረክተው እንደማያውቁ የሚናገሩት እንግዳችን፤ ‹‹ለራስ ብቻ እያሰሉ መንቀሳቀስ ዋጋችንን ዝቅ ያደርገዋል። ምክንያቱም ታሪክ እንዳይኖረንና በስራችን እንዳንታወስ ያደርጋልና ነው፡፡ ስለሆነም የእኔ እምነት መደመርና መቀነስ ከህዝብ አገልግሎት አንጻርም መሆን አለበት›› ይላሉ፡፡ህዝብን በቅንነት ከማገልገል ውጪ የህሊናም ሆነ የመንፈስ እርካታ ሊመጣ አይችልምና ህይወትን በሃላፊነት አምኖ ለሰጠ ህዝብ ማድረግ ይገባልም ባይ ናቸው፡፡
በትምህርት ሥራ ላይ ይህንን ያህል መቆየታቸው የአገር ግንባታ ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ እንዳደረጋቸውና ሰዎችም በተለይ የትምህርት አመራሮች ከዚህ አንጻር ቢጓዙ የቻሉትን እንዳደረጉ ይሰማቸዋል ብለውናል፡፡
‹‹ትምህርት ቤት የሄድኩባቸው ጊዜያት ሲቀነሱ 34 ዓመታትን ከትምህርት ሳርቅ በመስራቴና ህዝብን አገልግሎ በሰላም ሥራን ስላስረከብኩ በጣሙን ተደስቻለሁ፡፡›› የትምህርት ባለሙያ በመሆኔ ዩኔስኮ ውስጥ መመደቤ ለአገራችን የትምህርት ሥራ ተጨማሪ አቅም ሆኜ የበለጠ ለማገልገል የምችልበት እድል ስላገኘሁ አስደስቶኛል፡፡
የኢንተርናሽናል ኢዲኩዌሽን ኮንፓራቲቭ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ጥላዬ፤ የተለያዩ ቦታዎችና የተለያዩ ሥራዎችን መስራት ለእኔ የተለያዩ ትምህርቶችን መማር እንደሆነ አምናለሁ ይላሉ። በዚህም አዲስ እድል አዲስ የትምህርት አጋጣሚ በማግኘቴ እጅግ ተደስቼበታለሁ ብለውናል፡፡
ዶክተር ጥላዬና ፍኖተካርታ
የሥርዓተ ትምህርት ብልሽት እንዳለ የተረዳሁት ገና ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እያለሁ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከዚያ በፊት መምህራን ማሰልጠኛ ስሰራ ጎበዝ፣ መካከለኛና ጥቂት ደከም ያሉ ተማሪዎች ናቸው ያሉት፡፡ ዛሬ ግን ብዙሀኑ እንዴት ዩኒቨርሲቲ እንደገቡ እንኳን ግልጽ ያልሆነበት ነው፡፡ እናም ይህ ነገር መለየት አለበት ስል ጥናት አደረክሁ። በዚህም ትምህርት የሚያጠናቅቁበትና ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡበት ጊዜ ያልተመጣጠነ መሆን፤ የትምህርት አሰጣጡ፣ የመምህራን የአቅም ሁኔታና ወዘተ ችግሮች መሆናቸው አገኘሁ፡፡ በተጨማሪ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በርቀት የተማሩ መሆናቸውም ሌላው ችግር ነበር ይላሉ፡፡
የትምህርት ሥራ የአገር ግንባታ ሥራ ነው፤ትውልድ የሚገነባበትም ነው፤ ታላቅ አገራዊ ሀላፊነትና የሁሉም ሥራ መቋጫ እንደሆነ የሚያስረዱት ዶክተር ጥላዬ፤ ‹‹ ለእኔ መልካም ገጠመኝ በፍኖተ ካርታው ሥራ ላይ መሳተፌና ውሳኔ ሰጪ አካል ሆኜ መመደቤ ነው። ምክንያቱም በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ማህበረሰቡ ትልቅ ሮሮ እንዳለበት ከእኔ በላይ የሚረዳና የሚያውቅ የለም። ስለዚህም መታረም ያለበትን ለማረሙ፣ መቀጠል ያለበት ደግሞ እንዲቀጥል ለማድረጉ የእኔ ድርሻ ትልቅ ይሆናል›› ይላሉ፡፡
ባለሙያዎች ያጠኑትን ሀሳብ በመያዝ ከመንግስት ጋር በመሆን መልክ እንዲይዝ ማድረግ መቻላቸውም ሁልጊዜ እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ፡፡ ፍኖተካርታው በምክንያት የሚያምን፣ የሚደማመጥ፣ አገርን ወደብልጽግና ጎዳና የሚያሸጋግር ትውልድን ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም ለትግበራው የእኔ ድርሻና ሀላፊነት ትልቅ ስለነበር በጥቂቱም ቢሆን አሻግሬዋለሁ ይላሉ፡፡
እንግዳችን፤ ያላስተማርነውን ትውልድ መቼም በተሻለ ሁኔታ ልንጠብቀው አንችልም፡፡ እናም በእኔ ሥራ ጀርባ ሚሊዬን ሰዎች አሉ ብሎ በማመንና ለእነዚያም ሲባል መስራት በመቻሉ ጥሩ ውጤት ይገኛ የሚል እምነት እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡
‹‹መድሃኒትና ትምህርት ተሞክሮ ነው ችግሩ የሚታወቀው›› የሚሉት እንግዳችን፤ ለዚህም ማሳያው አሁን እየወጣ ያለው ትውልድ የአስተሳሰብ ደረጃና የቀደሙት ተማሪዎች የማገናዘብ አቅም በእጅጉ የተለያየ መሆኑ ነው፡፡ ቀደምቶቹ በትንሽ ስልጠና በቀጥታ ሥራ ላይ ገብተው ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ የተመረቁበትን ሙያ አውቀውትም ይሰራሉ፡፡ አሁን እየወጣ ያለው ምሩቅ ግን ብዙ የሚጎሉበት ነገሮች በመኖራቸው የተነሳ ሥራ አጥ ጭምር ሆኖ መንገድ ላይ የሚንከራተት ሆኗል። እናም ይህ ሀላፊነት የትምህርት ባለሙያው በመሆኑ እንደባለሙያነት በጥቂቱም ቢሆን የተንቀሳቀስኩት የነገን የተሻለ ትውልድ ያሳየኛል ብለው እንደሚያምኑ አጫውተውናል፡፡
ለፍኖተ ካርታው እውን መሆን ገና ብዙ ዋጋ ይከፈላል፡፡ 51 ቋንቋ ወደ ትምህርት ቤት ሲወሰድ ብቁ ያልሆኑ መምህራን ተቀጥረዋል፡፡ በዚህም ቋንቋ ተናጋሪ ያልተማረ መምህር ኖሯል፡፡ በሌሎች መልኩም ብዙ ያልበቁ መምህራን ከዩኒቨርሲቲ እስከ ታችኛው ክፍል ድረስ አሉ፡፡ በአመራር ደረጃም ቢሆን እንዲሁ በሙያ ሳይሆን በፖለቲካ አቅም የገቡ አይጠፉም፡፡ እናም ይህንን ሁሉ ሥርዓት ማስተካከልን ይጠይቃል። ከስር ከመሰረቱ ለውጥ ማምጣት ሲቻል ነው የተሻለች ኢትዮጵያን በትምህርቱ ዘርፍ መፍጠርና ማግኘት የምንችለው። በመሆኑም እኔና መሰሎቼ የህይወት መስዋዕትነት እንኳን ቢከፈልበት ከፍለን ይህንን ውጤት ለማየት መትጋት አለብን ብለዋል፡፡
የፍኖተ ካርታው ሥራ የተጀመረ እንጂ ያለቀ አይደለም የሚሉት ዶክተር ጥላዬ፤ ሁሌም ከጀመሩት ሥራ ላይ አለሁበት ብለው እንደሚያስቡና እድሉ ቀንቶአቸው ዩኔስኮ ቢገቡም በዚያም ሆነው ይህንን የሚያጠናክር ሥራ እንደሚያከናውኑ ነግረውናል፡፡ ዩኔስኮ ውስጥ የመጨረሻ ዶክመንቱ እየተጻፈ በመሆኑ ወደዚያ መሄዳቸው ለበለጠ ስራ እንደሚያበረታቸውና አሻራቸውን ማሳረፍ እንዳያቆሙ እንደሚያደርጋቸውም አጫውተውናል። ከዚያም በኋላ ከሥራው ካላራቋቸው በስተቀር የትምህርት ሥራውን እንደሚደግፉም ይናገራሉ፡፡
ቀደም ሲል ሁለት ዓመታት የቦርድ አባል በመሆን የተለያዩ መርሃግብሮችን ይሳተፉበት በነበረው ዩኔስኮ በመግባታቸው ስራውን ስለሚያውቁት አሁን ደግሞ በፓሪስ የኢፌዴሪ ሚሲዮን ባለሙሉ ስልጣን ሚኒስትር የስራ ደረጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሳይንስ፣የትምህርት እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው እንዲሰሩ በመመደባቸው ከአገራችን አንጻር እየቃኙ እንደሚሰሩበት አጫውተውናል፡፡ በዩኔስኮ ከሚሰሩ የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋርም እየተጋገዙ አቅማቸው በፈቀደ አገራቸውን ማገልገል እንደሚቀጥሉበት ነግረውናል፡፡
አበርክቶ
‹‹እኔ ለአገሬ ይህንን ሰራሁ የምለው ነገር የለኝም።አገሬ እኔን እየጠቀመችኝ እንደሆነ ከማሰብ በቀር›› የሚሉት ዶክተር ጥላዬ፤ ተናገር ከተባልኩ የፍኖተ ካርታው ላይ የሰራሁት ሥራ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ከዚያ ውጪ በቅንነት በተመደብኩበት ቦታ ህዝብን ማገልገል መቻሌ አበርክቶዬነው፡፡ የመንግስትን፣ የህዝብንና የራሴን አቅም በመጠቀም የሰራኋቸው የመሰረተ ልማትና ሌሎች የትምህርት ሥራዎችም ለአገሬ ብዬ ያደረኩት በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፡፡
ፍልስፍና
ፍልስፍናዬ አገርንና ህዝብን በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል መቻል የህሊና እርካታን ያስገኛል ብሎ ማመን ነው፡፡ በዚህም በርካታ ሽልማቶችን በየደረጃው አግኝቼበታለሁ፡፡ ግን ከዚህ ሁሉ ዋናው ክፍያዬና ሽልማቴ አገር በትምህርት ሥርዓቱ የተሻለች እየሆነች መምጣቷ ነው፡፡ለዚህ ደግሞ ከ12 ሰዓት በላይ በሥራ ላይ አሳልፋለሁ፡፡ ይህ ደግሞ ለውጥ ለማምጣት የማደርገው ነው፡፡ ግን ስኬቴን በፍልስፍናው የማረጋግጠው ፍኖተካርታው ተተግብሮ ውጤቱን ሳይ ነው ብለውናል፡፡
ፈተና
በቤት ውስጥ ለቤተሰብ ብዙ ጊዜ ያለመስጠትና በማህበራዊ ህይወት ደካማ መሆናቸው በጣም ችግራቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከዚያ ባሻገር ደግሞ በሚሰሩት ሥራ መርካት አለመቻላቸው ያበሳጫቸዋል፡፡ በእርግጥ ይህ ምክንያት አለው ይላሉ፡፡ የአቀድኩት ነገር ሙሉ ለሙሉ ተፈጽሞ አለማየታቸውና በጥቂት ነገር የሚረካ ሰው ባለመሆናቸው እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ስለዚህም በእኔ መደሰት ሌሎች እንዲደሰቱ ለማድረግ አለመቻሌ ፈተና ሆኖብኝ ቆይቷል ይላሉ፡፡
በተሰጣቸው ሀላፊነት ሁሉ የሚይዝዩት እቅድና የሚያገኙት ውጤት ባለመጣጣሙ አንድም ቀን እረክተው ባለማወቃቸው ሰዎችም በትንሽ ነገር እንዳይረኩ አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ ጥሩም መጥፎም ጎን አለውና ጥሩውን ማስፋት ላይ መጥፎውን መቀነስ ላይ መስራት እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡
በትምህርት ስርዓቱ ብዙ ተማሪ እየወደቀ፣ ብዙ ችግር ያለበት መምህር ተይዞ፣ የትምህር ባለሙያው የሚፈለገውን ስትራቴጂካዊ አመራር በማይሰጥበት አገር ተቀምጠን፣ የምሩቃን ሁኔታ በአቅም የተሻለ ባልሆነበትና ህብረተሰቡ በትምህርቱ ስርዓት እየተማረረና እያለቀሰ እየታየ በጥቃቅን ነገር የምሻሻም ከሆነ በጣም ደስ እንደማይል ይናገራሉ፡፡ ተረክቷል ተብሎ ምስጋና ማቅረቡም ሹፈት ይሆንብኛል ባይ ናቸው፡፡ እናም በጥቂት ሳይሆን በብዙ ለመርካት የሚታትር ሰውን መፍጠር የመጀመሪያ ሥራቸው እንደሚያደርጉት አጫውተውናል፡፡
ቤተሰብ
በስራ አጋጣሚ ነው ያገኟት የዛሬ የሁለት ልጆች እናትና ባለቤታቸውን ዶክተር አዳም መኮንን። የምትሰራው በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህርት በመሆን ሲሆን፤ ልጆቿን በሚገባ የምትንከባከብ፤ ለእርሳቸውም ጭምር ልዩ ትኩረት የምትሰጥ፤ የእርሳቸውን ድክመት በእርሷ ሥራ የምትሸፍን ነች፡፡ በተለይ ማህበራዊ ተሳትፎ ላይ እርሳቸውንም ወክላ የምትገኝበት ቦታ ብዙ ነው፡፡
የዶክተር ጥላዬ ልጆች ሁለቱም ሴቶች ሲሆኑ፤ የመጀመሪያ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሦስተኛ ዓመት የህክምና ትምህርት ተማሪ ነች፡፡ ሁለተኛዋ ደግሞ ናዝሪት እስኩል አስረኛ ክፍል ትምራለች፡፡ ስለዚህም እርሳቸው ልጆቻቸውን ማስጠናት ባይችሉም እናታቸው ጎበዝ ተማሪ እንዲሆኑ አድርጋቸዋለችና በዚህ ያመሰግኗታል፡፡
ለትምህርት በሄዱበት እንኳን እገዛዋ እንዳልተለያቸው የሚናገሩላት ባለቤታቸው፤ ልጆቹን ብቻዋን እንዳሳደገች ይሰማቸዋል። ግን አጠቃላይ የእርሷም ሆነ የእርሳቸው ቤተሰብ መተጋገዝ የሚወዱ በመሆናቸው ሁለቱም ዲግሪያቸውን ውጪ አገር ሄደው ሲማሩ እንዳልተቸገሩ አይረሱትም። ስለዚህም በቤተሰባቸው ደስተኛ እንደሆኑም ይናገራሉ፡፡
መልዕክት
በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያሉትን ደረጃዎች አንድ በአንድ እየሰራሁባቸው በመምጣቴ ትምህርት ምን እንደሆነ ተረድቻለሁ የሚሉት ባለታሪኩ፤ በእርሳቸው ምልከታ ትምህርት ትውልድ የመቅረጽና ቀጣይ አገርን የመስራት ጉዳይ ነው፡፡ ትውልድ ማፍሪያና አገር ማንነቷ ሳይደፈር ማቆያ ነው፡፡ አገር በየዘርፉ ምን ደረጃ ላይ እንዳለች ማሳወቂያም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህም ሰዎች ይህንን አስበው ሊማሩም ሊያስተምሩም ሊሰሩም ይገባል የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው፡፡
‹‹ሰዎች ከእኔ ቢማሩ የምለው የአላማ ጽናትን ነው፡፡ እኔ ለያዝኩት ነገር አቅሜ በፈቀደ መጠን አይቻልም ሳይሆን ይቻላል ብዬ እሰራለሁ፡፡ ይህ ደግሞ የምፈልገውን ሁሉ በስኬት እያጠናቀቅሁ እንድጓዝ አድርጎኛል፡፡ አሁንም ለበለጠ ስኬት እንድሰራ መሰረቴ እርሱ ነው፡፡ ስለሆነም ሰዎችም ይቻላልን ይዘው አቅማቸውን አሟጠው ቢሰሩ ይጠቀማሉ›› ይላሉ፡፡
ከሰዎች ሲማሩ በንጽህ ልብ መሆን አለበት። በዚህች ምድር ላይ አንድ ጊዜ ነው ኖረንባት የምናልፈው፡፡ ስለሆነም በበጎነት ለአገርና ለህዝብ ማገልገልንም ልምድ ማድረግ ይገባል፡፡ በተሰማራበት ሙያ፣ ለተሰጠው ሀላፊነት ታማኝ ሆኖ ማገልገልም ያስፈልጋል፡፡
አገር ለማገልገል የእውቀት ችግር ችግር አይሆንም። ችግሩ ከሰዎች ለመማር ያለው ዝግጁነት ነው፡፡ ቅንነት፣ ታማኝነት፣ በመልካም መንፈስ በአቅም ልክ መንቀሳቀስ አለመቻል ነው። ስለዚህም ከላይ የተዘረዘሩትን ገንዘብ አድርጎ መንቀሳቀስ ከተቻለ አገርን መለወጥ አያዳግትም ሌላው ምክራቸው ነው። እኛም መልዕክታቸውን በመተግበር ለአገራችን እንቁም እያልን ለዛሬ አበቃን።ሰላም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው