በምግብ እንሽርሽሪት መዋቅር ላይ ከሚያጋጥሙ በሽታዎች መካከል አብዛኞቹ በተዛባ አመጋገብና አኗኗር ዘይቤ አማካኝነት የሚከሰቱ ናቸው። እነኝህ ሕውክታዎች፣ ከጊዜያዊ ምቾት ማጣት ስሜቶች እስከ ተወሳሰቡ የካንሰር በሽታዎች ሊሆኑ ይችላሉ። አብዛኛው ሕዝብም በነዚህ በሽታዎች ይጠቃል። በተለይ የጨጓራ ሕመም የብዙ ሰዎች የጤና ችግር ሲሆን የሆድ ድርቀትና ተቅማጥ የሚያስከትሉ የውስጥ ደዌ የጤና ችግሮችም በስፋት ይታያሉ። አብዛኛውን ጊዜ የምግብ እንሽርሽሪት ስርዓት ላይ የሚያጋጥሙንን የጤና ችግሮች አመጋገብንና የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል መቆጣጠር የሚቻል ሲሆን በዚህ ዘዴ መቆጣጠር የማይቻሉትን ደግሞ ሕክምና በመከታተል መፍትሔ ሊገኝላቸው ይችላል።
የምግብ እንሽርሽሪት ስርዓት ስንል አብዛኛውን ጊዜ ስሙ የሚነሳው ጨጓራ ቢሆንም ስርዓቱ የሚያቅፋቸው ብዙ የሰውነት ክፍሎች ናቸው። ይኽውም ከአፍ(Mouth) ጀምሮ ምራቅ ዕጢ(Salivary glands)፣ ድህረ አፍ(Pharynx)፣ ጉሮሮ (Oesophagus)፣ ከርስ(Stomach)፣ ጉበት (Liver)፣ የሃሞት ከረጢት (Gallbladder)፣ ቆሽት/ፓንክሪስ(Pancreas)፣ ትንሹ አንጀት (Small intestine)፣ ትልቁ አንጀት (Large intestine)፣ ሽለላ አንጀት(Rectum) እና ፊንጢጣ(Anus) ናቸው። እንግዲህ ምግብ ተበልቶ፣ ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ተመጠው በአንፃሩ ደግሞ ሰውነት የማይፈልጋቸው ውጋጆች ከሰውነት እንዲወገዱ እነኝህ የአካል ክፍሎች በትስስርና በመናበብ ያለእንከን መስራት ይጠበቅባቸዋል። ከነኝህ አካላት አንዳቸው ላይ የሚያጋጥም የጤና እክል በሰንሰለታማ ግንኙነት ሌሎችም ላይ ይንፀባረቃል። ለምሳሌ ቅባት የበዛቸውን ምግቦች ስንመገብ ቅባቱ እንዲፈጭ በሃሞት ከረጢት ውስጥ የሚገኘው ሃሞት መረጨት መቻል አለበት፤ የሃሞት ከረጢት ከሌለ ወይም አንድ እክል ገጥሞት የማይሰራ ከሆነ፣ የቅባት ምግቡ ስለማይፈጭልን የመታወክ ሁኔታ ያጋጥመናል። ሌሎቹም እንዲሁ ናቸው።
ሕውከተ ጨጓንጀት (gastroenteritis)
ጨጓራና ከጨጓራ ጋር በትስስር በምግብ ልመት፣ ድቀት እንዲሁም የጠቃሚ ንጥረ ነገሮች ምጠት እና የማይጠቅሙ ነገሮች ውጋጅ ላይ የሚሰሩ ውስጠ አካላት አብዛኛውን ጊዜ ሕውከት ይገጥማቸዋል፤ ይህ ሕውከት ጊዜያዊና ለክፉ የማይሰጥ ወይም ስር የሰደደ ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም በነኝህ አካላት ላይ የሚያጋጥም የጤና ችግር በአንድ ላይ ሕውከተ ጨጓንጀት (gastroenteritis) ይባላል። በስርዓቱ ላይ ከሚያገጥሙ በሽታዎች መካከል በስፋት የሚታየው የጨጓራ በሽታ ነው።
የጨጓራ በሽታ ምልክቶች
አብዛኛውን ጊዜ የጨጓራ በሽታ ሲያጋጥም፣ ምልክቶች ከእንብርት በላይ በሆድ አካባቢ መታየት ይጀምራሉ፤ ለማሳሌ የማቃጠል፣ የመጐርበጥ እንዲሁም የቁርጠት ስሜት ሊሰማን ይችላል። ምግብ ከተመገብን በኋላም ምቾት ማጣት በብዛት ያጋጥማል፤ ተያይዞም የምግብ አለመፈጨት፣ የሆድ መነፋት እና የማቅለሽለሽ ስሜት ይኖራል። ችግሩ እየባሰ ሲሄድ ደግሞ ግሳት፣ ቃርና ማስመለስ ሊኖር ይችላል። እነዚህ የጨጓራ ህመም ምልክቶች ሲሆኑ፤ ከፍ እያለ ሲመጣ እና በሽታው ስር ሲሰድ በተከታታይ ደም ማስታወክ፣ የሰውነት ክብደት መቀነስ እንዲሁም ሰውነት የመዛልና የመድከም ስሜት ሊከተል ይችላል።
አብዛኛውን ጊዜ የጨጓራ በሽታ ሲያጋጥም፣ ምልክቶች ከእንብርት በላይ በሆድ አካባቢ መታየት ይጀምራሉ
አያይዘን ማወቅ ያለብን የጠቀስናቸው ምልክቶች ሙሉ ለሙሉ የጨጓራ ህመም ብቻ የሚያመጣቸው ላይሆኑ ይችላሉ። ቀድመን እንዳየነው ከጨጓራ በተጨማሪም በዙሪያው የሚገኙ የጉበት፣ የቆሽት፣ የሐሞት ከረጢት እንደዚሁም የአንጀት ህመም ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። አልፎ አልፎ ደግሞ በእድሜ መግፋት የሚመጣ የስኳር ህመም ያለባቸው፣ የልብ ህመም ተጠቂዎች እንዲሁም የምግብ መፍጫ ቱቦ ህመም ያለባቸው ሰዎች እነዚህን ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ። ስለዚህ የሚታዩ ምልክቶች ሐኪም ዘንድ በመቅረብ ከየትኛው እንደሆኑ መለየት አለበት። ለዚህ ተግባር በተለያዩ መሳሪያዎች የተለያዩ ምርመራዎች ሊያስፈልጉ ይችላሉ።
የጨጓራ በሽታ መንስኤዎች
የጨጓራ በሽታ በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ደረጃ ተንሰራፍቶ የሚገኝ በሽታ ነው። በሽታው ብዙዎችን የሚጐዳና መነሻዎቹም በርከት ያሉ ናቸው። ነገር ግን በብዛት የሚታወቀው በባክቴሪያ አማከኝነት የሚከሰተው ኢንፌክሽን ነው። ይህ በሽታ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ከንፅህና ጉድለት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ነው። አብዛኛውን ጊዜ ምግብና ውኃ በባክቴሪያው በመበከሉ ምክንያት በጨጓራ ላይ ኢንፌክሽን ይፈጠራል። ኢንፍክሽን ደግሞ ቁስለት የሚያስከትል ነገር ነው። ቁስለት ደግሞ እስከ ደም መፍሰስ ሊያስከትል የሚችል ነው። በዚህ መንገድ የሚፈጠር ደም መፍሰስ በሰገራ ላይ ጭምር መታየት የሚችል ነው። ሌሎች እንደምክንያት ሊጠቀሱ የሚችሉት በምግብ፣ በመድኃኒት እና በሌላ መልኩ ወደ ከርስ የሚገቡ በርካታ ነገሮች ጨጓራን ሊያስቆጡ ይችላሉ። የተለያዩ የፀረ-ተዋሲያን፣ የሳንባ እንዲሁም የካንሰር ሕክምና መድኃኒቶች እንደጎንየሽ ችግር ጨጓራን የሚያስቆጡ ናቸው። አልኮልም ሌላው ጨጓራን የሚያስቆጣ ነገር ነው። የሚጠጡ የባሕል መድኃኒቶች፣ ጫት እና ሲጋራም የጨጓራ ህመም መንስኤዎች ናቸው። ከነዚህ በተጨማሪ ካንሰር ሊሆኑም ላይሆኑም የሚችሉ በጨጓራ ላይ የሚበቅሉ ዕጢዎች አሉ። እነዚህ ዕጢዎችም ለጨጓራ ህመም መንስኤ ናቸው። በሌሎች በሽታዎች የተነሳም ጨጓራ ሊታመም ይችላል። ለምሳሌ የጉበት በሽታ፣ የሳንባ፣ የልብ እንዲሁም የኩላሊት በሽታ እና ሌሎች የሰውነት በሽታዎች የጨጓራ በሽታን በተዘዋዋሪ ሊያመጡ ይችላሉ።
በሰውነት ውስጥ አሲድ ከመብዛቱ የተነሳ አንጀትና ጨጓራ ላይ የመቁሰል ችግር ሊያጋጥም ይችላል። ከዚህም አልፎ አሲዱ ወደላይ ደጋግሞ በመመለስ የምግብ ቱቦን የሚያቆስልበት ሁኔታም ሊኖር ይችላል። በጣም በሰፊው በወጣቶች ላይ የሚከሰተው የጨጓራ ሕመም ደግሞ ከጭንቀት ጋር ተያይዞ በአሲድ መብዛት የሚከሰተው ሊሆን ይችላል። ይሄ ዓይነቱ ችግር ጨጓራው ሲታይ የመላጥ እና የመቁሰል ሁኔታ ሳይኖረው ሕመሙ ግን ሊኖር ይችላል። ሕመሙ ብዙ ጊዜ ከስራ ጋር ተያይዞ የኑሮ ጭንቀትና ውጥረት የሚያመጣው ነው። ችግሩ በወጣትነት እድሜ ላይ በሰፊው የሚታይ እና ለረጅም ጊዜ እየተመላለሰ የሚያስቸግር ሊሆን ይችላል።
ምርመራ
የጨጓራ ሕመምን ለመለየት የተለያዩ ምርመራዎች ይደረጋሉ፤ አብዛኛውን ጊዜ መጀመሪያ የሚታየው የጨጓራ ባክቴሪያ መኖር አለመኖሩን የመለየት ስራ ነው። ይህም በደም፣ በሰገራ ወይም በትንፋሽ ምርመራ ሊለይ ይችላል፤ ከባክቴሪያው ኢንፌክሽን የተነሳ በትንፋሻችን የሚወጣ ኬሚካል አለ፤ በመሆኑም ትንፋሽ በመመርመር ማወቅ ይቻላል። አንድ ሰው ላይ የጨጓራ ባክቴሪያ መኖሩ ታውቆ ከታከመ በኋላ ባክቴሪያው መጥፋት አለመጥፋቱን መመርመር አለበት፤ ምርመራውም መካሄድ ያለበት በሰገራ ወይም በትንፋሽ ብቻ ነው። ምክንያቱም ሰውነታችን የሚያመርተው ፀረ እንግዳ አካል(አንቲ ቦዲ) ለረጅም ዓመታት በደም ውስጥ ሊኖር ይችላል፤ በመሆኑም በተደጋጋሚ በደም ምርመራ ባክቴሪያው መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ አይቻልም። ብዙ ጊዜ በህክምናው ላይ የሚታየው የተሳሳተ አካሄድ ይሄ ነው። አንድ ሰው ተደጋጋሚ የደም ምርመራ እያደረገ የጨጓራ መድኃኒቶችን ዝም ብሎ መውሰዱ ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም አላስፈላጊ ወጪ ከማስወጣቱ እና ከመድኃኒት ጉዳቱም በተጨማሪ በሽታው መድኃኒቱን በመልመድ ለወደፊቱ በምን እንደሚታከም ሊቸግር ይችላል።
ከበድ ያሉ ምርመራዎችና መፍትሔዎች
በሌላ በኩል ህመሙ ስር እየሰደደ ሄዶ መቁሰል፣ የጨጓራና አንጀት መጣመም እና መጥበብን ከዚህም አልፎ በጨጓራ ላይ ካንሰር የሚያመጡ ዕጢዎችን የመሳሰሉ ጠንቆችን የማስከተል ደረጃ ላይ ከደረሰ የቪዲዮ ምርመራ (ኢንዶስኮፒ) በማድረግ ደረጃውን ማወቅ፣ የሚደማ ነገርም ካለ በመርፌ መድኃኒት በመስጠት ማቆም እና ማዳን ይቻላል። ዕጢዎች ከተከሰቱም ናሙና ወስዶ በማረጋገጥ ትንሽ ከሆነ ያቺን ቦታ ቆርጦ ማውጣት ይቻላል። በተጨማሪም በህመሙ ስር መስደድ የተነሳ የጨጓራ እና የአንጀት መተላለፊያ ከጠበበ በኢንዶስኮፒ ማስፋት ይቻላል። ከአቅም በላይ ሆኖ ከፍተኛ የመድማት ሁኔታ ካለው፣ ትልቅ ዕጢ ካስከተለ እስከ ቀዶ ህክምና የሚደርስ ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል።
የበሽታ ጠንቆችን የማስከተል ደረጃ ላይ ከደረሰ የቪዲዮ ምርመራ (ኢንዶስኮፒ) በማድረግ ደረጃውን ማወቅ ይቻላል
አመጋገብና መውሰድ ያሉብን የጥንቃቄ እርምጃዎች
ምግብና አመጋገብን በተመለከተ ለሁሉም ሰው የተሻለ ወይም ምርጥ የሚባል አካሄድ አለ ብሎ መናገር ያስቸግራል። በተፈጥሯችን የተለያየ የምግብ ፍላጐትና ልምድ ስላለን ለሁሉም የሚስማማ የሚባል ምግብ የለም። በመሆኑም በአጠቃላይ የሚመከረው ቡና፣ ሻይ፣ ቅመማ ቅመም እና በርበሬ የበዛባቸው ምግቦችን እንዲሁም አልኮል እና ሲጋራን አለመጠቀም ነው።
ምግብና አመጋገብን በተመለከተ ለሁሉም ሰው የተሻለ ወይም ምርጥ የሚባል አካሄድ አለ ብሎ መናገር ያስቸግራል ሰውነትን የሚያቃጥሉና የሚያስቆጡ እንደ አልኮል፣ ሚጥሚጣ እና ቃሪያ ያሉ የሚወሰዱ ነገሮች አብዛኛውን ጊዜ ለጊዜው የማደንዘዝ ባህሪይ ስላላቸው ያሻሉን ይመስላሉ፤ ብዙ ሰዎችም እነኝህ ነገሮች እንደሚያሽሉአቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ። ውስጠ አካለችን ስስ ስለሆነ ለጊዜው እንደማደንዘዣ ቢያግዙም ውጤቱ ግን ቁስለት ካለ ማባባስ ነው የሚሆነው።
ሌላኛው ችግር ደግሞ ጥግብ ብሎ መብላት ነው፤ እስከ ቁንጣን የደረሰ ጥጋብ ጨጓራ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል፤ በመሆኑም ከፋፍሎ መመገብ ያስፈልጋል። ጨጓራ መፍጨት ሲያቅተው ምግቡ ተከማችቶ የጨጓራ ሕመም ስሜቶች የሆኑት የመነፋት፣ የማበጥ፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስና የመሳሰሉት ይፈጠራሉ። በታመመ ጨጓራ ላይ ደጋግመን ብዙ ነገር ብንጭንበት የባሰ እየደከመ ይመጣል።
ማጠቃለያ
ስንወለድ የሁላችንም ተፈጥሮ ተመሳሳይ ቢሆንም፤ የአመጋገብ ልምድ ከባህላችን ጋር ይያያዛል። ከልጅነት ጀምሮ ቅመማ ቅመሞችን ተመግቦ ያደረገ ሰው በምግቡ የተነሳ ጨጓራው አይታመምም። ነገር ግን የሌላ ሀገር ምግብ የሚመገቡ ሰዎች መጀመሪያ ሊታመሙ ይችላሉ። የውጭ ሀገር ዜጐችም የእኛን ሀገር ምግብ ሲላመዱት ምንም አይላቸውም። ችግሩ የሚፈጠረው በታመመ ጨጓራ ላይ እነዚህን ኮስተር ያሉ ምግቦች ስንጨምርበት ነው ህመሙን የሚያባብሱት።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012