ኢትዮጵያዊነት እንደ አባ መላዕከ ህይወት አክሊለማርያም ያሉ መስኪዶችን የሚገነቡ ፤እንደ ሀጂ ቱሬ አይነት ቤተክርስቲያን የሚያሰሩ ድንቅ አባቶች ያፈራች ሀገር ነች፡፡ የሃይማኖት አጥር ሳይገድባቸው የአንዱ ሃይማኖት ተከታይ ለሌላው ዘብ የሚቆምና መስዋዕትነትን የሚከፍል ህዝብ ያፈራች ሀገር ነች፡፡ በዘመናት ሂደትም አንዱ ከአንዱ ጋር ተጋብቶና ተዋልዶ በመኖር ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ነባር ባህልና ታሪክም ዘመናትን የተሻገረና በውጭው ዓለም ዘንድም ዕውቅና የተቸረው ነው፡፡
ለዚህም ነው በእምነት ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ለበርካታ ኢትዮጵያውያን አስገራሚና ለመቀበልም የሚቸግር ድርጊት የሚሆነው፡፡ ለዘመናት አብረው የኖሩት ኢትዮጵያውያን አማኞች መስኪድ የሚያቃጥሉበት ቤተክርስቲያን የሚያወድሙበት ምንም አይነት መነሻ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን አማኞች በአንዱ የእምነት ተቋም ላይ የተቃጣ ጥቃት በሁሉም የእምነት ተቋማት ላይ እንደ ተቃጣ ጥቃት አድርገው የሚወስዱት፡፡
ይህን ለዘመናት አብሮ የቆየውን የአብሮነትና የመቻቻል ባህል ለማጥፋትና የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ የሚፈልጉ ወገኖች ግን ሁሉጊዜም የሃይማኖት ተቋማትን በማቃጠልና በማውደም ሀገሪቱን ወደ ለየለት ጥፋትና ብጥብጥ እንድታመራ ዘወትር ሲታትሩ ይስተዋላሉ፡፡ በተለይም በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያንን በብሄር በመከፋፈል ለማበጣበጥና ለማዋጋት የተሸረበው ሴራ ባለመሳካቱ ፊታቸውን ወደ እምነት ተቋማት አዙረዋል፡፡ ሰሞኑንም በሞጣ ከተማ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰውም ጥቃት የዚሁ አንድ ማሳያ ነው፡፡
በሞጣ ከተማ የተደረገው አጸያፊ ተግባር የሁለቱንም ሃይማኖት ተከታዮች የማይወክልና ለዘመናት በአካባቢው ሰፍኖ የቆየውን ፍቅርና መተሳሰብ የማይመጥን አሳፋሪ ድርጊት በመሆኑ በክርስቲያንና በሙስሊም ማኅበረሰቦች እየተወገዘ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ጉልላት ላይ ጭስ በመታየቱ የአካባቢው ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በፍጥነት ተረባርበው የከፋ ጉዳት ሳይደርስ እሳቱን መቆጣጠር መቻሉ አስደሳች ቢሆንም፣ ስሜትን አስቀድመው ይሁን ወይም ሌላ ተልዕኮ ተቀብለው በማይታወቅ ሁኔታ መስጊዶችንና ሱቆችን ያቃጠሉና የዘረፉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ውለው ለሕግ እንዲቀርቡ የሁለቱም እምነት ተከታዮች እየጠየቁ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም የተቃጠሉትን መስኪዶች መልሶ ለመገንባት ክርስቲያን ባለሀብቶች ጭምር በሚሊዮኖች የሚገመት ብር በማዋጣት አንድነታቸውንና አብሮነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ፡፡
ለበርካታ አመታት አብሮ የኖረው የሞጣ ሙስሊምና ክርስቲያን በሴረኞች ተንኮል ሥራ የሚፈታ እንዳልሆነ ማሳያው ሰሞኑን በሁለቱም በኩል እየተደረገ ያለው የእርስ በርስ መደጋገፍ ማሳያ ነው፡፡ ሙስሊሙ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ክርስቲያኑ መስጊዶችን ላለፉት ሺህ ዓመታት እየገነቡና እየተጋገዙ እንደኖሩት ሁሉ፣ ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ራሳቸውና የክልሉ መንግሥት የተቃጠሉትን እንደሚገነቡም እየተገለጸ ነው፡፡
ይህ የሞጣ ህዝብ እያደረገ ያለው የአንድነትና አብሮነት ጉዞ የሴረኞችን ተንኮል ያከሸፈ ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያውያን እኩይ መንፈስ ባላቸው የሴራ መልዕክተኞች ደባ እንደማይተላለቁ ማሳያ በመሆኑ አሁንም መሰል የትብብርና የአንድነት ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012