• 26 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ተመዝግቧል
አዲስ አበባ፡- ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ያለ በቂ ምክንያት ወደ ሥራ ያልገቡ 1ሺ178 ፕሮጀክቶች ፈቃድ መሰረዙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ። በግማሽ ዓመት 26 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት መመዝገቡ ተጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳብራሩት፤ በግማሽ በጀት ዓመቱ ዘርፈ ብዙ የኢንቨትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ ለመስጠት ታሳቢ ተደርጎ ሰፊ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን ለ1ሺ500 ኢንቨስትመንቶች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ከእቅዱ በላይ ልቆ 1ሺ598 ፈቃድ ለመስጠት ተችሏል። የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በተገቢው ጊዜ ወደ ሥራ ባልገቡት ላይ እርምጃ ተወስዷል። የኢንቨስትመንት አዋጁ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደ ሥራ ካልገቡ ፈቃድ የሚሰረዝ መሆኑን ያስቀመጠ ሲሆን፤ በግማሽ ዓመቱ 1ሺ178 ፕሮጀክቶች ፈቃድ ተሰርዟል።
ኮሚሽነሩ እንዳሉት፤ በግማሽ ዓመቱ 26 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት የተመዘገበ ሲሆን፤ ለ10ሺ ዜጎች የሥራ ዕድልም ይፈጥራሉ ። በ2012 በጀት ዓመት ደግሞ 40 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ታሳቢ ተደርጎ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል። የኢንቨስትመንት ስብጥሩም በአገልግሎት ዘርፍ፤ በማኑፋክቸሪንግ እና በማህበራዊ ዘርፎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በኮንስትራክሽን ላይ ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ መኖሩንም አብራርተዋል።
በስድስት ወራት ውስጥ 2ነጥብ9 ቢሊዮን ብር ካፒታል ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፤ 959 ፕሮጀክቶች የካፒታል እቃ እንዲያስገቡ፣ 47 ፕሮጀክቶች ደግሞ መለዋወጫዎች እና 166 ተሽከርካሪዎች ግዥ ከቀረጥ ነፃ ተፈፅመዋል። ለ19 ፕሮጀክቶች ደግሞ መሬት እንዲያገኙ ድጋፍ መደረጉን አብራርተዋል።
ቀደም ሲል ፈቃድ የወሰዱ 51 ፕሮጀክቶች ደግሞ ወደ ሥራ መግባታቸውን አብራርተዋል። በአምስት ዓመቱ የዕድገት ትራንስፎርሜሽን ውስጥ በአገልግሎት ዘርፍ ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ ከታሰበው ውስጥ 40 ከመቶ ስኬታማ መሆኑን አስገንዝበዋል። በአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ 60 ከመቶ ታሳቢ የተደረገ ሲሆን 40 ከመቶ ስኬታማ ሆኗል።
እንደኮሚሽሩ ገለፃ፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፤ ኢንቨስተሮች ፈቃድ ባገኙበት ዘርፍ በፍጥነት ወደ ሥራ አለመግባት፤ ከፍተኛ የሆነ የመሬት አቅርቦት እጥረት፣ የውጭ ምንዛሪና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት መኖሩ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሯል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር