ወይዘሮ ሀይርያ መሀመድ በቡታጀራ ከተማ ቀበሌ 02 ነዋሪ ናቸው። ውልደታቸውና እድገታችው አዲስ አበባ ቢሆንም በትዳር ምክንያት ቡታጀራ ላይ ከከተሙ 41 ዓመታትን እንዳስቆጠሩ ይጠቅሳሉ። በዚያን ወቅት ታዲያ ቡታጀራ ከገጠር መንደር ብዙም ያልተሻለችና መሰረተ ልማቶች ያልተዘረጉባት እንደነበረች ያስታውሳሉ። በተለይም ደግሞ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በከተማዋ መኖር ፈታኝ እንደነበር ያነሳሉ።
የመጠጥ ውሃ የሚያመጡት በከተማዋ ከሚገኙ ሁለት ተፋሰሶች እንደነበር የሚናገሩት ወይዘሮ ሃይርያ፤ ይህም እንደእርሳቸው ላሉ እናቶችማ ችግራቸውን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎባቸው መቆየቱን ይጠቅሳሉ።« ከተፋሰሶቹ ውሃ የምናስመጣው በትንሹ 40 ደቂቃ በእግራችን ተጉዘን አልያም ደግሞ አህያ ያላቸውን ሰዎች ፈልገንና ተማፅነን ነበር፤ ብዙውን ጊዜ ደግሞ ወረፋ ለመጠበቅ እንገደድ ነበር» ይላሉ። አህያው ተገኝቶ ውሃውን ቢያስመጡም የከተማዋ ነዋሪዎች ተፋሰሱን የሚጋሩት ከከብቶቻቸው ጋር በመሆኑ የሚደፈርስበትና የሚበከልበት አጋጣሚ ብዙ እንደነበር ያስረዳሉ።
ይህም ታዲያ በተለይ እንደእርሳቸው ላሉ እናቶችና ህፃናት ለውሃ ወለድ በሽታዎች ሲያጋልጣቸው ኖሯል። «ብዙዎቻችን በንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር በጃርዲያ አሜባና ኮሬላ ለተባሉ በሽታዎች እንዳረግ ነበር» የሚሉት ወይዘሮ ሃይርያ፤ ለተጨማሪ ወጪና እንግልት ይዳረጉ እንደነበርም ያነሳሉ። ከተማዋ በከርሰ ምድር ውሃ የታደለች ሆና ሳለ ነዋሪዎቿ በችግር መኖራቸው ሁልጊዜም ያሳስባቸውና ያሳዝናቸው እንደነበርም ነው የተናገሩት።
ይሁንና ካለፈው አስር ዓመት ወዲህ የከተማዋ አስተዳደር ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር ንፁህ የመጠጥ ውሃ መስመር ዝርጋታ በማከናወኑ ያ ሁሉ ስቃይ መቃለሉን ይናገራሉ። «አሁን ያለው የቡታጀራ ውሃ አገልግሎት ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አለው» ይላሉ። የውሃ እና የሌሎች መሰረተ ልማቶች መዘርጋታቸውን ተከትሎ ግን ከገጠር ወደ ከተማዋ የሚፈልሰው ህዝብ ቁጥር በጊዜ ሂደት መጨመሩን፤ ከተማዋም እየሰፋችና እያደገች መምጣቷን ይገልፃሉ።
ይህን ተከትሎም በተለይም በከተማዋ የገጠር ወረዳዎች ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ውሃውን ማዳረስ ለከተማዋ አስተዳደር ፈታኝ እንደሆነበት ይገልፃሉ።ምንም እንኳን እርሳቸውና ሌሎች በመሃል ከተማዋ ያሉ ነዋሪዎች ውሃ አንገብጋቢ ችግራቸው ባይሆንም ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ግን አሁንም እነሱ ከ40 ዓመት በፊት ይጋፈጡት የነበረውን መከራ ተካፋይ መሆናቸው እንደሚያስዝናቸው ይገልፃሉ።
«እኔ አካባቢ ችግር ባይኖርም አዳዲስ በተመሰረቱ ሰፈሮች አካበቢ ያሉ ሰዎች በጣም በውሃ ችግር እንደሚሰቃዩ አያለሁ።በተለይም ደግሞ ከተማዋ በከርሰ ምድር ውሃ የታደለች በመሆንዋ የውሃ መስመር ዝርጋታው እነዚህን አካቢዎች ቢያዳርስ ጥሩ ነው» በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የቡታጀራ ከተማ የውሃ አገልግሎት ድርጅት የሰው ሀብት የስራ ሂደት አስተባባሪ ከማል ከድርም የወይዘሮ ሀይርያን ሃሳብ ይጋራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ ከአለም ባንክ በተገኘ ብድር ከተማ አስታደደሩ ያስገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጅክት ከጥቂት ዓመታት በፊት የከተማዋን የውሃ ሽፋን 100 በ100 አድርሶት ነበር። ይሁንና ከተማዋ ፈጣን እድገት እያስመዘገበችና ነዋሪዎቿም እየጨመሩ በመምጣታቸው ምክንያት ሽፋኑን ወደ 94 በመቶ አውርዶታል።
በተለይም ደግሞ በአካባቢው ያሉ ወረዳዎችና ቀበሌዎችም ሳይቀሩ ከከተማዋ ውሃ እያስጫኑ የሚወስዱበት ሁኔታ በመኖሩ ለሁሉም የከተማዋ ነዋሪ ያለምንም መቆራረጥ ማዳረስ አዳጋች እየሆነ መምጣቱን ይገልፃሉ። አቶ ከድር አሁን ላይ ምንም እንኳ በፈረቃ ውሃ የሚሰራጭበት ሁኔታ ባይኖርም የህዝቡ ቁጥር ከዚህ በላይ ማደጉ ስለማይቀር ወደፊት ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ የሆኑ አካባቢዎች ሳይቀሩ የችግሩ ተካፋይ እንዳይሆኑ ስጋት አላቸው።
በአሁኑ ወቅት ይህንን ችግር በዘላቂነት መፍታት ያስችል ዘንድ በድርጅታቸው የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ይገልፃሉ፡ከዚህ ቀደም የነበረውን መልካም አፈፃፀም መሰረት በማድረግም የከተማ አስተዳደሩና የዞን አስተዳደሩ ከፍታ ባለባቸው አካባቢዎች የንፁህ መጠጥ ውሃውን ተደራሽ ለማድረግ ጉድጓድ የመቆፈር ስራ ማከናወናቸውን ያስረዳሉ። ቁፋሮው ከተጠናቀቀ በኋላ ግን ባለፈው አመት በነበረው አገራዊ አለመረጋጋት ችግር ምክንያት የግብዓቶች ግዢ ሳይፈፀም መቅረቱን ይናገራሉ። ይሁንና የችግሩን አንገብጋቢነት በመረዳት ፅህፈት ቤቱ በራሱ አቅም ግዢውን ፈፅሞ የመስመር ዝርጋታ መከናወኑን ያብራራሉ።
«ይህም ሆኖ ግን በትራንስፎርመር ችግር ምክንያት ውሃውን ለተጠቃሚዎቹ ማድረስ አልተቻለም። ይህንንም ጉዳይ እስከ ክልል ምክርቤት አቅርበው እስከሚቀጥለው ወር ድረስ ችግሩ እንደሚፈታ ተገልጾልናል» በማለት ያለውን ችግር አብራርተዋል።ድርጅታቸው በአካባቢው ያለውን ሰፊ የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ጥቅም ላይ ማዋል ያስችል ዘንድ ተጨማሪ የጉድጓድ ቁፋሮዎችን ለማከናወን ማቀዱንና ፕሮጀክት መቅረፁን ይናገራሉ።
ይሁንና ጉድጓድ የማስቆፈሪያው ገንዘብ የአንድ አመቱ በእጥፍ በማሻቀቡ ምክንያት በራሱ አቅም ፕሮጀክቱን እውን ማድረግ አዳጋች እንደሆነበት ያስረዳሉ።« የእኛ ከተማ ከዚህ ቀደምም በውሃ ፈንድ አማካኝነት ከአለም ባንክ ለውሃ ፕሮጀክት የተበደርነውን ገንዘብ በመክፈል ረገድ ከግንባር ቀደሞቹ መካከል የሚጠቀስ ነው፤ ስለሆነም አሁንም ለፕሮጀክቱ ማስፋፊያ የሚያስፈልገንን ገንዘብ በብድር ብናገኝ በታማኝነት ለመክፈል ዝግጁ ነን» በማለት የድጋፍ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በደቡብ ብሄር ብሄረሰብ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ከመጡ ከተሞች መካከል ሆሳእና ከተማ አንዷ ነች። ልክ እንደቡታጀራ ሁሉ የውሃ አቅርቦቱ እያደገ ከመጣው ፍላጎት ጋር የማይመጣጠን መሆኑን የከተማዋ ውሃ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ያረጋግጣሉ። በአሁኑ ወቅት ከ185ሺ ሰዎች በከተማዋ ይኖራል ተብሎ እንደሚገመት የሚናገሩት ኋላፊው፤ ይህንን የህዝብ ቁጥር የሚመጥን የውሃ መሰረተ ልማት መዘርጋት ላይ ግን አስተዳደሩም ሆነ ድርጅታቸው የፋይናንስ እጥረት እንደተገዳደራቸው ያስረዳሉ።
እንደአቶ ጥላሁን ገለፃ፤ ድርጅቱ ከ2003 በፊት አራት ጥልቅ ጉድጓዶች እና ከወንዝና ግድብ ውሃ በማጣራት ነበር አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው። ከ2003 ዓ.ም በኋላ ግን በአለም ባንክ ብድርና በህብረተሰብ ተሳትፎ ወደ ዘላቂ ውሃ መስመር ዝርጋታ ተገብቷል።በዚህም ከ6ሺ ሜትሪክ ኪዩብ በላይ ውሃ በማምረት የውሃ ሽፋኑን ከ45 በመቶ ወደ 94 በመቶ ማሳደግ ተችሏል። ይህም ሆኖ ህብረተሰቡ አሁንም ውሃ እያገኘ ያለው በፈረቃ ነው። በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት ኢንቨስትመንት በከተማዋ እያደገ በመምጣቱ የውሃ ፍላጎቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ እያደገ ይገኛል።
የውሃ ልማት ፈንድ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ዋና ዋቄ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ድርጅታቸው ከተቋቋመበት አላማዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ጉዳይ በሚያገኘው የመንግስት ድጎማ፣ የውጭ ብድርና እርዳታ የከተሞችን የውሃና የሳኒቴሽን ተደራሽ ማድረግ አንደኛው ነው። ከእነዚህ ምንጮች የሚያገኘውን ገንዘብ በብድር የሚያስተላልፍ ሲሆን እስካሁን 114 የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን 104 ከተሞችን ተደራሽ አድርጓል። በእነዚህ ከተሞች ላይ ያወጣው ወጪም አንድ ቢሊዮን ይደርሳል።
«በአሁኑ ወቅት41 ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁ ሲሆን ከእነዚህ ከተሞች ውስጥ 27 የሚሆኑት ብድራቸውን ወደ መመለስ ገብተዋል» ያሉት አቶ ዋና፤ ከወሰዱት ውስጥ ወደ 600ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ያመለክታሉ። በአሁኑ ወቅትም በርካታ ፕሮጀክቶች ተጠንተው ብድር እየተጠበቁ መሆኑን ይገልፃሉ። በተጨማሪም የፕሮጀክቱን ጣዕም የቀመሱት ከተሞችም ተጨማሪ ብድር በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ከእነዚህም መካከል ቡታጅራና ሆሳእና ከተማ ተጠቃሽ እንደሆኑ ያስረዳሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
ማህሌት አብዱል