አዳማ፡- የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ በመጪው የገና በዓል ከህብረተሰቡ አቅም በላይ የገበያ ዋጋ ንረት እንዳይከሰት በሥሩ ባሉት ማህበራት አማካኝነት እየሠራ መሆኑን ገለፀ። ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የግንዛቤ መፍጠሪያ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
የምክክር መድረኩ ትናንት በአዳማ ከተማ በተካሄደበት ወቅት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ከኤጀንሲው ዋና ተግባራት ውስጥ አንዱ የኑሮ ውድነትንና ድህነትን መቀነስ ሲሆን፤ ይህንን ለማረጋገጥም በዓላት ሲመጡ የምርቶች እጥረት እንዳይኖርና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ ማህበራትን በከተሞች ባሉ ዋና ዋና የመሸጫ አካባቢዎች ከሸማች ማህበራቱ ጋር የማስተሳሰር ሥራዎች ይከናወናሉ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ለመጪው የገና በዓል በኤጀንሲው ሥር ያሉ ማህበራት የእርድ እንስሳት፣ እንቁላል፣ አትክልት፣ ፍራፍሬና መሰል ምርቶችን በማቅረብ የገበያው ዋጋ የተረጋጋና ጤናማ እንዲሆን በመሥራት ላይ ሲሆን ይህ ተግባር በሁሉም በዓላት በተመሳሳይ ሁኔታ የሚከናወን ነው።
የሕብረት ሥራ ማህበራት የገበያ እሴት ሰንሰለቱን በማሳጠር አምራቹ ከሸማቹ ጋር በቀጥታ እንዲገናኝ በማድረግ መሆኑን፤ ይህም አምራቹ ተመጣጣኝና ፍትሐዊ ግብይት እንዲያደርግ እንደሚያግዘው፤ በሌላ መልኩ ሸማቹ ህብረተሰብ ጥራት ያለው ምርት በፈለገው ጊዜና ቦታ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንደሚያስችለውና ይህ ተግባር ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ስኬታማ እየሆነ መምጣቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
አጠቃላይ አገራዊ የፖለቲካ ቀውስ ወደ ኢኮኖሚ ቀውስ እንዳይሄድ የህብረት ሥራ ማህበር የማይተካ ሚና መጫወቱን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህ ሚና ወደ ፊትም እንደሚቀጥልና በተለይ የበዓላት ወቅትን ተከትለው በሚመጡ የገበያ ትርምስና አለመረጋጋት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ፤ የህብረት ሥራ ማህበራት የህዝቡን የልማት ፍላጎት ማሳካት የሚያስችሉ የመንግሥት የልማት ውጥኖችን ወደ መላው ህብረተሰብ የሚያደርሱ መሆናቸውን በመጠቆም፤ በግብይት ወቅት የአቅርቦት ችግር እንዳይፈጠር ከምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ጋር በጥምረት እየሠራ መሆኑን ጠ ቁመዋል።
ኤጀንሲው የህብረት ሥራ ማኅበራት ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻልና በተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ፓርክ ለሚሠሩ ህብረት ሥራ ማህበራት ግንዛቤ ለመፍጠር ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ያካሄደ ሲሆን፤ በመድረኩ የህብረት ሥራ ማህበራት እሴት ከመጨመር አኳያ ያላቸው አገራዊ አፈፃፀምና ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲሠሩ ምክረ ሐሳቦች ተነስተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
አዲሱ ገረመው