አዲስ አበባ፡- ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቡና ኮንፍረንስ፣ ኤግዚቢሽንና ፌስቲቫል የኢትዮጵያ ቡናን በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ለማስተዋወቅ የሚያገለግል ብራንድ ሎጎ ይፋ የሚደረግ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ። የወጪ ቡና አስተዳደር መመሪያም ከጥር 1 ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑም ተመልክቷል።
የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ የቡና ኮንፍረንስ፣ ኤግዚቢሽንና ፌስቲቫሉን አስመልክተው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ቡና ብራንድ ሎጎ ይፋ መደረጉ አገሪቱ የምታመርተውን ልዩ መለያ ከማስተዋወቅ ባሻገር ከምርቷ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ ያግዛታል።
«ኢትዮጵያ የቡና መገኛና በርካታ ዝርያ ያላቸውን ቡናዎች ለአለም እንደማበርከቷና ከሚታወቁ የአለም የቡና አምራቾችና ቡናን በቀዳሚነት ከሚያበቅሉት የአፍሪካ አገራት አንዷ ብትሆንም ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ግን ማግኘት አልቻለችም» ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም ዋነኛ ምክንያት የሚገባውን ያህል ማስተዋወቅ አለመቻሉ መሆኑን አስገንዝበዋል። እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ ሁሉንም ቡና የሚወክል መለያ ብራንድ በውል አለመኖሩ በምክንያትነት የሚጠቀስ መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም የብራንድና ሎጎው በዚህ አለም አቀፍ መድረክ ላይ ይፋ መደረጉ አገሪቱ ያላትን በርካታ ባለልዩ ጣዕም የቡና ዝርያዎችን ለማስተዋወቅ የሚያግዛት መሆኑን ተናግረዋል።
እንደዶክተር አዱኛ ገለፃ፤ የመድረኩ መዘጋጀት አምራቾችን፣ ላኪዎችና ገዢዎችን በቀጥታ ለማገናኘት እድል ይፈጥራል። ዱካው የታወቀን ቡና ለገዢዎች ለማስተዋወቅና በቀጥታ በሚመረትባቸው አካባቢዎችም በመገኘት ገበያ ተዓማኒነት እንዲኖር ያግዛል። ፍትሃዊ የቡና ንግድ ተጠቃሚነትን ለማጥራት የራሱን አስተዋፅኦ የሚያበረክት ሲሆን፤ የተለያዩ የቡና አምራች አገራት ያላቸውን የአመራረት ተሞክሮ እና በግብይቱም ረገድ ያላቸውን እውቀት ለማካፈል ያስችላል። በተጨማሪ አገሪቱ ያላትን የቡና አፈላል ስነስርዓት በማስተዋወቅና ለቱሪዝም መስህብነት ለማዋል ሚና ይኖረዋል።
በሌላ በኩልም የወጪ ቡና ውል አስተዳደር መመሪያ ከጥር 1ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። መመሪያው አገሪቱ ልታገኝ ይገባት የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ግኝት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ሲያደርግ የቆየው እና ለኤክስፖርት ገቢ ትልቅ ፈተና የነበረው በሻጮችና ገዢዎች መካከል ይፈጠር የነበረውን የኮንትራትና ውል(under invoice and contract default) ማፍረስ ችግር ይፈታል ተብሎ እንደሚታመን አስገንዝበዋል።
«coffee from land of origin» በሚል መሪ ሃሳብ ከጥር 28 እስከ30 በሚከበረው በዚሁ ኹነት ከመላው አለም በሚመጡ 500 በላይ ቡና ገዢዎች፣ አልሚዎች፣ ቡና ቆይዎችና ምሁራን ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። እንዲሁም ከአንድ ሺ በላይ የአገር ውስጥ ተሳታፊዎች ፣ 56 ምርቶቻቸውን የሚያሳዩ ድርጅቶች ይታደማሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
ማህሌት አብዱል