የዞን ዋና ከተማ ናት። በከተማዋ ውስጥ አንድ ሜትር አስፋልት የለም። ሙሉ በሙሉ አቧራ ናት፤ ዝናብ ሲዘንብ ደግሞ አላላውስ የሚል ጭቃ ሰቅዞ ይይዛታል። በከተማዋ ውስጥ ከሙዚቃ በላይ የጄኔሬተር ድምጽ ጎልቶ ይሰማል። ይቺ ከተማ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የምትገኘው የሸካ ዞና ዋና ከተማ ማሻ ናት።
የሸካ ዞን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው አገር በቀል የተፈጥሮ ደን የሚገኝበት ነው። በዚህ ደን ውስጥ ብዙ አይነት የቅመማ ቅመም አይነቶች አሉ። የማር ምርት አለ። በዞኑ ውስጥ በዓመት 500 ሺህ ቶል ቡና ይመረታል። ለገበያ የሚቀርበው ግን ከ15 በመቶ አይበልጥም።
አቶ አበራ ገሊቶ የማሻ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የሸካ ዞን እስከ አሁን ድረስ በደርግ ዘመነ መንግስት በተሰራ የጠጠር መንገድ ነው የሚጠቀመው። ይሄ የጠጠር መንገድ ክረምት በገባ ቁጥር ይቋረጣል። በዚህ የመንገድ ችግር ምክንያት የአካባቢው ምርቶች ለገበያ አይቀርቡም። አንድ የጭነት መኪና ቢገኝ እንኳን ምርቱ ከሚሸጥበት ዋጋ በላይ ለማስጫኛ ይጠይቃሉ። ለዚያውም መኪና ከተገኘ ነው። በዚህም ምክንያት የአካባቢው ምርቶች ባክነው ይቀራሉ። ‹‹እንኳንስ የሰው እጅ ገብቶበት ዱር በቀል የሆነው ሀብት ብቻ በቂ ነበር›› የሚሉት አቶ አበራ፤ በመንገድ አለመኖር ምክንያት እንኳንስ ለገበያ ለአካባቢው ማህበረሰብም እንደማይደርስ ይናገራሉ።
‹‹አገራችን ሳተላይት ወደ ሰማይ ማምጠቋን ከሰው ነው የሰማነው›› ያሉት አቶ አበራ፤ በአገሪቱ ውስጥ የሚከናወኑ ነገሮችን በመብራት ችግር ምክንያት መከታተል አይችሉም። እያንዳንዱ ግለሰብ ጄኔሬተር ገዝቶ መኖር አይችልም። መብራት የሚመጣው በአሥራ አምስት ቀን እንደሆነና ለዚያውም ከአሥራ አምስት ደቂቃ በላይ እንደማይቆይ ተናግረዋል። በምን ምክንያት እንደሚጠፋ በግልጽ ባያውቁትም በተደጋጋሚ የሚነገራቸው ዛፍ ወድቆ ነው የሚል ነው። የባንክ አገልግሎት ለረጅም ጊዜ ይቋረጣል። ንጹህ የመጠጥ ውሃ የለም። በዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች ለውሃ ወለድ በሽታዎች በተደጋጋሚ ይጋለጣሉ።
ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ አቶ መኮንን አርጎ ‹‹በአካባቢው ያለው ሀብት ለዓለም ይበቃ ነበር›› ይላሉ። በጥቅጥቅ ደኑ ውስጥ ብዙ የቅመማ ቅመምና ሌሎች ውድ የሆኑ የመድኃኒትና የምግብ አይነቶች ይገኛሉ። መንገድ ግን ምቹ አይደለም። መኪና ቢመጣ እንኳን መንገድ እየተበላሸ ለረጅም ጊዜ ቆሞ ይቆያል።
እንደ አቶ መኮንን ገለጻ፤ በከተማዋ ውስጥ ያለው ነዋሪ መደበኛ መጠቀሚያው ሻማ ነው። አቅም ያለው ጄኔሬተር ይገዛል፤ አብዛኛው ነዋሪ ግን በሻማ ነው። በዚህም ምክንያት የአንድ ሻማ ዋጋ 10 ብር ነው። የፀጉር ቤትና ሌሎች በመብራት የሚሰሩ አገልግሎቶችን ማግኘት አይቻልም። በዚህም ምክንያት ወጣቶች ተስፋ በመቁረጥ ለስደት እየተዳረጉ ነው።
የማሻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጀመረ ተሰማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በከተማዋ ውስጥ ያለው የመብራት ችግር የቆየ ነው። ችግሩን በመሰረታዊነት ለመቅረፍ በከተማዋ አቅራቢያ አዲስ ‹‹ሰብስቲትዩሽን›› እየተሰራ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ሥራውን ቢያንስ በሳምንት ሁለት ጊዜ እየሄደ ይጎበኛል። ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ዋና ማከፋፈያው ከኦሮሚያ ክልል ስለነበር ርቀት አለው። አንድ ቦታ ብልሽት ቢፈጠር ለረጅም ጊዜ ይቆያል። በሌላ በኩል አካባቢው ደን የሚበዛበት ስለሆነ ተደጋጋሚ ብልሽት ይደርስበታል። ያንን ችግር ለመቅረፍ በከተማዋ ዳርቻ የራሱ የሆነ ዋና ማከፋፈያ እየተገነባ ነው።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዘነ አዳፎ እንደገለጹት፤ የሸካ ዞን ለበርካታ ዓመታት የቆየ የመሰረተ ልማት ችግር ነው ያለበት። አሁን ላይ ግን ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው። የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ሥራ ተጀምሯል። የገጠር ተደራሽ መንገዶችም እየተሰሩ ነው።
‹‹መቆራረጥ የሚለው አይገልጸውም›› የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው የዞኑ የመብራት ችግር ከመቆራረጥም በላይ ለረጅም ጊዜ የሚጠፋበት ይበልጣል። እስከ ሦስት ሳምንት ድረስ ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ እንደሚቆይም አስረድተዋል።ችግሩን በመሰረታዊነት ለመቅረፍ በማሻ ከተማ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በማሻ ከተማ እየተሰራ ባለው የመብራት ማከፋፈያ ሳይት ሱፐርቫይዘር የሆኑት አቶ ፍቃዱ ቂጤሳ እንደሚሉት፤ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ግንባታ ከፍተኛ ዝናብ ካላጋጠመ በቀሪዎቹ 15 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
ዋለልኝ አየለ