አዲስ አበባ፡- በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ ጉዳት የደረሰባቸውን የእምነት ተቋማት ለመገንባት በተደረገ የገንዘብ ማሰባሰብ አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ የተገኘ ሲሆን 725 ሺህ ብር ቃል ተገብቷል። ገንዘቡ የተገኘው ከባለሀብቶች፣ ከግለሰቦች፣ ከመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ከተለያዩ ማህበራት እና ከእምነት ተቋማት ነው።
የሞጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የህዝብና ሚዲያ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መንግስቱ አለማየሁ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ አቶ ወርቁ አይተነው የተባሉት ባለሀብት ቃል የገቡትን አምስት ሚሊዮን ብር በተከፈተው የባንክ ሒሳብ አስገብተዋል። የሞጣ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት 100 ሺህ ብር፣ የሁለት እጁነሴ ወረዳ አስተዳደር 500 ሺህ ብር፣ የማቻከል ወረዳ አስተዳደር 50 ሺህ ብር ቃል የገቡ ሲሆን ከአዋበል ወረዳ የተውጣጡ ዕድሮች 42 ሺህ 200 ብር በጥሬ ገንዘብ ገቢ አድርገዋል።
በሌላ በኩል የአዋበል ወረዳ ቤተ ክህነት 10 ሺህ ብር ለመስጠት ቃል የገባ ሲሆን በሞጣ ከተማ ውስጥ የሚገኝ አንድ ወጣትም 65 ሺህ ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል። በሞጣ ከተማ የሚገኝ የወንጌላዊት ህብረት ሁለት ሺህ ብር ገቢ አድርጓል። ሁለት ማንነታቸው ካልታወቁ ሰዎች 680 እና 250 ብር ገቢ ተደርጓል። አቶ መንግስቱ እንደገለጹት፤ በጥሬ ገንዘብ ከተሰበሰበውና ቃል ከተገባው ውጭም ሌሎች ተቋማትና ባለሀብቶችም አጋርነታቸውን በማሳየት ላይ ይገኛሉ።
በሞጣ ከተማ ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ ሰላማዊ መሆኑን የገለጹት አቶ መንግስቱ፤ መደበኛ እንቅስቃሴዎችና የንግድ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል። የአካባቢው ማህበረሰብ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
ዋለልኝ አየለ