ሐዋሳ፡- ‹‹በጥቃቅን ምክንያት እርስበእርስ የሚለያየንን አጀንዳ ትተን ስንደመር አቅማችን ይጎለብታል›› ሲሉ በደቡብ ህዝቦችና ብሄር ብሄረሰቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ተናገሩ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ መደመር ማለት ደቡብ ማለት ነው። መደመር አንዱን የሚያቀርብ ሌላውን ደግሞ የሚያገል ሳይሆን ሁላችንም የምናስፈልግ በመሆናችን በጋራ አገር እንገንባ የሚል እሳቤ የያዘ ሰነድ ነው። ይህ ሲስተዋል ደግሞ ለመደመር ማዕቀፈ እሳቤ ደቡብ በማሳያነት ሊቀርብ የሚችል ነው፤ ከዚህም አኳያ በጥቃቅን ምክንያት የሚያለያይን አጀንዳ በመተው በመደመር አቅማችንን ማጎልበቱ በየትኛውም እይታ የተሻለ ነው።
አቶ ርስቱ፣ ‹‹እንደ ደቡብ ያለንን ነገር ማስተዋል ከቻልን በርካታ ነገር በእጃችን ላይ አለ። ስንሰባሰብ አቅማችን ይጠናከራል። ለአብነትም ከዚህ በፊት ደቡብ ሲቋቋም ካሉት ማህበረሰቦቹ መካከል 12ኛ ክፍል ያልጨረሱ በርካታ ነዋሪዎች ይገኙበት ነበር። በተቃራኒው ደግሞ በጣም በርካታ ምሁራን ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎችም ነበሩ። ነገር ግን ወደ አንድ በመምጣታችን የአንዱ አቅም ለሌላው ጉልበት መሆን ቻለ። እርስ በእርስም ተደጋገፍን። ዛሬ ላይ በሁሉም ኮሪደሮቻችን የተማረ የሰው ኃይል አለ፤ ይህ ትልቅ ነገር ነው›› ሲሉ አመልክተዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ በክልሉ ብዝሃነት አለ፤ ይህ ብዝሃነት ደግሞ ሀብት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በመደመር ያለውን የሰው ኃይል፣ ሀብትና ሐሳብንም በሙሉ በማጠናከርና አንድ በመሆን ክልል ብሎም አገርን መገንባት ይቻላል። ስለዚህ እንደመር የሚለውን እሳቤ ደቡብ ቀድሞ ተደምሮ ማሳየት ችሏል። ይህንኑ የደቡብን ሐሳብ ሌላውም ወስዶት የበለጠ በመቀራረብና አንድ በመሆን ለሁሉም በምትበቃ አገር መኖርና በጋራም በማልማት መጠቀም ይቻላል። መደመር የያዘውም ፅንሰ ሐሳብ ይኸው ነው።
የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ወደ 56 ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚኖሩ ሲሆን፣ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን እንዲሁም ታሪካቸውንም በማሳደግ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
አስቴር ኤልያስ