– የታሪክ ትምህርት የመጨረሻ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ውይይት ይደረጋል
አዲስ አበባ፡- ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ልህቀትን ማዕከል አድርጎ ለማደራጀት የተጠናው ጥናት የፌደራል ሥርዓቱን ያገናዘበ፣ የአገሪቱን ቀጣይ ዕጣ ፋንታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባና ዓለም ነባራዊ ሁኔታም የቃኘ መሆኑን የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የልህቀት ማዕከል አድርገው እንዲደራጁ ጥናት መካሄዱን የገለፁት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ኤባ ሚጀና ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የትምህርትና ስልጠና ለውጥ ስራዎች ትግበራ እና ቀጣይ ሥራዎች›› በሚል ባቀረቡት ጽሁፍ፤ አሁን ባለው ሁኔታ በምሩቃን ዘንድ የሥነ-ምግባር እና የሞራል ውድቀት፣ ስርዓት አልበኝነትና ምክንያታዊ ያለመሆን፣ የሥራ ጠባቂነትና ጥገኝነት፣ የወቅታዊ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ያለማወቅና ያለመረዳት፣ የተግባቦትና የመረዳዳት ችግር አለበት። በመሆኑም በምሩቃን ዘንድ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እና በትምህርትና ስልጠና ስራዎች ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥናት መካሄዱንና በጥናት ሰነዱ ምክረ ሃሳብ መሰረት በከፍተኛ ትምህርት የለውጥ ስራዎች ተለይተው ሲሰሩበት መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
የትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሃዊነት፣ ጥራትና አግባብነት ችግሮች በተገቢውና በሚፈለገው መጠን ሳይፈቱ ቆይተዋል። አገሪቱ የምትፈልገውን ብቁና በአንዳንድ መስኮችም በቂ የሰው ኃይል ማፍራት ሳይቻል ቀርቷል። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለማቃለል የሚያግዝ ስልት አስፈላጊ መሆኑንም አብራርተዋል።
የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው፤ አዲሱ አደረጃጀት ፌዴራል ሥርዓቱን ማዕከል ያደረገና ለሁሉም ክልሎች ተደራሽ በሚሆንበት ብሎም ፍትሀዊ የሆነ ሥርዓትን በመከተል የተደራጀ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸው ልምድ፣ አቅምና ተሞክሮ ከግምት ውስጥ የገባ መሆኑን አስረድተዋል። በቀጣይ መሻሻል ባለባቸው ነገሮች ላይ ምክክርና ማሻሻያ የሚደረግ መሆኑን ፕሮፌሰሩ ጠቁመ ዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2013 ዓ.ም ለሚተገበረው አዲሱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ትግበራ ላይ ተከታታይ ውይይቶችና ምክክሮች ሲደረጉ መቆየታቸውንና በቀጣይም ሰፊ ሃሳብ የሚንሸራሸርበት ይሆናል ሲሉ ሚኒስትሯ ገልጸዋል። ይሁንና ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ አስመስሎ በማህበራዊ ድረ-ገፆችና አንዳንድ አካላት የሚሰራጨው መረጃ ስህተት መሆኑን አብራርተዋል። በተለይም ደግሞ የታሪክ ትምህርት ላይ የመጨረሻ ውሳኔ እንዳልተደረሰና አስፈላጊ ውይይቶች እንደሚደረጉ እና አዲስ የትምህርት ትግበራ የኢትዮጵያ፣ የምስራቅ አፍሪካንና የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።
ከሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በአዲሱ አደረጃጀት 15 የሚሆኑት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአፕላይድ፣ 21 የትምህርት ተቋማት በአጠቃላይ እና ሦስት የሚሆኑት ደግሞ ስፔሻላይዝድ በሚል ዘርፎች ተደልድለዋል።
በዚህም መሰረት አዲስ አበባ፣ አርባ ምንጭ፣ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ሀሮማያ፣ ሀዋሳ፣ ጅማ እና መቀሌ የጥናትና ምርምር፣ አርሲ፣ አሶሳ፣ አክሱም፣ ዲላ፣ ድሬዳዋ፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ኮተቤ፣ ጅግጅጋ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሰመራ፣ አምቦ፣ ወለጋ፣ ወልቂጤ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ አፕላይድ ተብለው ተመድበዋል።
ጋምቤላ፣ መቱ፣ ሚዛን፣ ዋቻሞ እና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች አጠቃላይ ተብለው ከተለዩት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሲካተቱ፤ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ስፔሻላይዝ ተብለው መለየታቸው ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር