የገጠር ልጅ ነው። እንደ እኩዮቹ ላለመማሩ ምክንያት የቤተሰቦቹ ድህነት ነበር። መሀል ደብረብርሀን ቢወለድም በአያቶቹ እጅ ለማደግ በሚል ወደ ገጠር ተላከ። የህጻንነት ዕድሜውን እምብዛም ሳያጣጥም በጎችን እንዲጠብቅ ተወስኖበት ከሜዳ ወሎ መግባትን ለመደ።
አንዳንዴ ከተማ ያሉ ወላጆቹን የማየት ዕድሉ ይገጥመዋል። እንዲህ በሆነ ጊዜ ደስታው ወሰን ያጣል። እንደ ልጅነቱ አይቦርቅም ስሜቱን ይገልጻል። እነሱ ሲያገኙት ግን ለአያቶቹ መሰጠቱን እንዲያውቅ አድርገው ማንነቱን ያስታውሱታል።በሀይሉ ከወላጆቹ ይበልጥ አያቶቹን ቢወድም ከተማ ለመሄድ ልቡ እንደተነሳ ውሎ ያድራል።
አልፎ አልፎ ለጥየቃ ወደ ገጠር የሚመጡ ዘመዶቻቸው ስለከተማ ሲያወሩ ጆሮውን የሚጥለው ህጻን ሁሌም ስለማያውቀው ህይወት እየተመኘ በጉጉት መኖሩ አልቀረም።ልጅነቱን ተሻግሮ በዕድሜው ሲጎለብት ደግሞ ይህ ፍላጎቱ ይበልጥ ጨምሮ ደጅ ደጁን ማየት ልምዱ አደረገ።
ከዕለታት በአንዱ ቀን ወደስፍራው የዘለቀችው አክስቱ ይህን ፍላጎቱን አውቃ ልታስከትለው ብታስብ የገጠሩ ልጅ በሀይሉ በእጅጉ ጓጉቶ በፍጥነት እንድትወስደው ይማጸናት ጀመር። ይህን ጊዜ ወደ ጉርምስናው ያለፈበት ዕድሜ በመሆኑ በራሱ ውሳኔ እንዲመራ ዕድሉን ሰጠው። አክስቱም የወጣቱን የተለየ ፍላጎትና ከተማ የመግባት ምኞት አስተውላ አብሯት እንዲሄድ ፈቀደችለት።
አዲስ ህይወት በአዲስ አበባ
በዕድሜው መጎልበት የያዘው በሀይሉ በአክስቱ ቤት እንግድነቱን እንደጨረሰ አዲስ አበባን ለመላመድ ጊዜ አልፈጀበትም። ወጣ ገባ ባለ ጊዜም እንደሌሎቹ ጉልበቱ የፈቀደውን ሰርቶ ማደር እንደሚችል ገባው። ይህኔ ራሱን አዘጋጅቶ የመረጠውን ለመስራት ወሰነ።
በአካባቢው ባገኘው የቀን ስራ እየዋለ እያደረ ገንዘብ መቁጠር ሲጀምርም ራሱን ማስተዳደር እንደሚችል ተማመነ። ማደሪያውን አክስቱ ቤት ያደረገው ወጣት በስራው አጋጣሚ ያገኛቸውን ሲግባባ ከብዙዎች ተላመደ። እንዲህ መሆኑም አርቆ እንዲያስብና ልቡ እንዲሸፍት ሰበብ ፈጠረ። ካለበት ርቆ ቤት ተከራይቶ መኖር እንዳለበት በወሰነ ጊዜ የአክስቱ ቤት ቆይታ ሰባት ወራትን አስቆጥሮ ነበር።
በሀይሉ በቀን ስራ ውሎው ሲቀጥል በከባድ ድካም መዛሉ አልቀረም።ወጪና ገቢው ሊመጣጠን ያለመቻሉ ደግሞ ያበሳጨው ጀምሯል። ሁሌም ከድካም መልስ በእጁ ያለውን ገንዘብ ሲቆጥር ይናደዳል። በዚህ መንገድ ህይወቱን እንዴት እንደሚቀጥል ሲያስብ ደግሞ ደጋግሞ ተስፋ ይቆርጣል።
እሱ ድካምና ልፋቱ ከእለት ወጪው ጋር ያለመደራረሱ ጉዳይ አሁንም እያሳሰበው ነው። በከተማ ኑሮ የሳሳ ህይወትን መከተል እንደሌለበት ለራሱ ደጋግሞ ነግሮታል። አሁን ካለበት መንገድ ፈቀቅ ለማለትም ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንዳለበት እያሰበ ነው። ከቀናት በኋላ ‹‹ይበጀኛል›› ባለው የቻይና ተቋራጮች ዘንድ ስራ ጀመረ። አሁንም ግን ብዙ ለሚያስበው በሀይሉ የስራው አይነትና የክፍያው መጠን የሚያስደስተው አልሆነም።
በሀይሉ የከተማን ህይወት ካወቀ ወዲህ በአንዳንዶች ዘንድ የሚያስተውለው የህይወት ለውጥ የፈጠነ መሆኑን ተረድቷል። በቅርብ የሚያውቃቸው ባልንጀሮቹ ሳይቀሩ ኑሯቸው ተሻሽሎ ረብጣ ገንዘብ የሚቆጥሩበት እውነትም ሌላ ሚስጥር እንደሚኖረው ከጠረጠረ ቆይቷል። በተለይ ትዳር ይዞ ጎጆ ከወጣ በኋላ እጅ እያጠረው የተቸገረበት ጊዜ የበረከተ ነው። ይህን ሲያስብም ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል ባለው ውሳኔ ላይ ከራሱ ተስማምቶ ጨርሷል።
አቅጣጫን መቀየር
አሁን በሀይሉ ሲያስብበት በከረመው ጉዳይ ከውሳኔ ደርሶ መንገዱን ጀምሮታል። ይህን የመከረው ከራሱ ጋር ስለነበር ሚስጥሩ የግሉ መሆን እንደሚገባው አምኖበታል። ሁሌም ከስራ መልስና በእረፍቱ ቀናት የሚመላለስባቸው ጎዳናዎች ለዓላማው ስኬት መነሻ ሆነውታል። እነዚህ መንገዶች የሚሻውን ለዓይኖቹ አቀብለው ለእጆቹ ሲሳይ ያደርሱለታል። በነዚህ ጭር ያሉ ሰፈሮች ብቅ ባለ ጊዜ ተነጥቆ ኪስ የሚገባ ገንዘብና ሞባይል አያጣም።
በሀይሉ የወጣበትን ጉዳይ አጠናቆ ወደቤቱ ሲገባ ደግሞ ምን ሰርቶ እንደተመለሰ የሚጠረጥር የለም። በሌላም ቀን ተመላልሶ ድርጊቱን ሲደግመው ያለአንዳች መረጃ ነውና ለሌሎቹ ታምኖ መኖሩን አውቆበታል። የሌብነቱን ጉዳይ ያለአንዳች እማኝ የቀጠለበት በሀይሉ ንጥቂያውን ከመጀሩ በፊት የአካባቢውን መውጫና መግቢያ ማጥናትን አይዘነጋም። ይህን ማድረጉ ፈጣን እግሮቹ ተፈትልከው እንዲያመልጡና መደበቂያዎችን ጭምር እንዲያመቻች አግዞታል።
ሚስጥር ጠባቂው መንታፊ ሁሌም ለስራ ሲዘጋጅ ከጎኑ የሚሽጠው የሰላ ቢላዋ አብሮት ነው። ድርጊቱን ለመከላከል የሚሞክርና የሚታገለው ካገኘም ስለቱን ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይል ያውቃል። በየቀኑ ዓይኖቹን እንደንስር ከወዲያ ወዲህ የሚያንቀዠቅዠው በሀይሉ አሳቻ ሰአትና ስፍራን እየለየ ያሰበውን መፈጸሙን ቀጥሏል።
በሀይሉን የሚያውቁ በርካቶች በቀን ስራ ደክሞ የመግባቱን እውነት ይመሰክራሉ። እሱም ቢሆን የሚተባበረው ያለማበጀቱ ስሙን ጠብቆ ከነሚስጥሩ እንዲጓዝ ረድቶታል።ሰፈር በዋለ ቀን ሌላ መንደር ተሻግሮ የመሄድ ልምዱ ተመልሶ ለሚፈጽመው ድርጊት እንዳገዘው ነው።
አንዳንዴ በሀይሉ በመንደሮች መሀል እየዞረ የቤቶቹን ሁኔታ ሲቃኝ ይውላል። በአሳቻ ሰአት ተመልሶ ለመምጣት የሚያመቸው ከሆነም መለያ ምልክትን ይተዋል። ሲመለስም ከአይኖቹ የገባውን አመቻችቶ ይሰርቃል። በማግስቱ ስራው ላይ የሚያዩት ሁሉ የሚያደርገውን አይጠረጥሩም። እሱም በስርቆት የሚያገኘውን ሲሳይ ከሌሎች አርቆ ለገዢዎች እያስማማ ባሻው ዋጋ ይሸጣል።
ታህሳስ 14 ቀን 2010 ዓ.ም
በሀይሉ በዚህ ቀን ስራ ላይ ውሎ በጊዜ ከቤቱ ገብቷል። ሌቱ ሲጋመስ ሊፈጽመው ያሰበውን ድርጊት ግን ከማሰላሰል አልቦዘነም። ያቀደውን ከማድረጉ በፊት በአንድ ሰፈር ደርሶ ሲዘዋወር ቆይቷል። እንዲህ ለመሆኑ ዋነኛ ምክንያት እንደተለመደው መውጫ መግቢያውን ለማጥናትና ማምለጫውን ጭምር ለማመቻቸት ነው።
ዕለቱን ደምቃ የዋለችው ጸሀይ ጊዜውን ለምሽቱ እንዳስረከበች ከቂሊንጦ ሰፈር የታችኛው መንደር ነዋሪዎች በጊዜ ወደየቤታቸው መግባት ጀምረዋል። አካባቢው ከዋና መንገዱ ወጣ ስለሚል መንደርተኛው እንዳሻው አምሽቶ መግባትን አለመደም። አጋጣሚ የሚያስመሻቸው ቢኖሩ እንኳን እርስ በርስ ተጠባብቀው ሊሄዱ ግድ ነው።
ገና በጊዜ ጭር ማለት የጀመረው ሰፈር ምሽቱ ላይ ብሶበታል። በስፍራው ያሉ አብዛኞቹ ግቢዎች በአጥር የተከበቡ ናቸው። ከነዚህ መሀል ጥቂቶቹ በአሮጌ ቆርቆሮና በሰንሰል ተከልለዋል። ከአጥሮቹ አልፈው የሚታዩ መኖሪያዎች አዲስ ቢሆኑም ዘመናዊ የሚባሉ አይደሉም።አፈራማው መንገድ ግራናቀኝ በሚተያዩ መልከ ብዙ ቤቶች ተከፋፍሎ ነዋሪዎችን ሲያመላልስ ይውላል።
መንደሩን ለኑሮ ከመረጡት በርካቶቹ ለቤት ኪራይ ቅናሽ ሲሉ የገቡ ናቸው። ከነዚህ መሀል በቀን ስራ የሚውሉ፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸውና አቅማቸው ዝቅተኛ የሚባሉ ይገኙበታል። ወጣት ተስፋዬ መኮንንም በዚህ ሰፈር ጊዚያትን ካስቆጠሩ ነዋሪዎች መካከል አንደኛው ነው።
ተስፋዬ የቀን ሰራተኛ ቢሆንም ከሚያገኘው ገቢ እያብቃቃ የማታ ይማራል። በዚህ ሰፈር የሚኖረው እንደሌሎች የቤት ኪራይ ስለቀነሰለትና አቅሙን ስለሚመጥን ነው።ያለበት ቤት አነስተኛ ክፍል ቢሆንም ራሱን ለማሳደር በቂው ሆኖለታል።በቤቱ የበዛ ዕቃ የለውም። ለዕለት መጠቀሚያ የሚሆኑትን ብቻ ገዝቶ ራሱ እያበሰለ ይጠቀማል።
የዛን ቀን በጊዜ በመግባቱ ራቱን በልቶና በሩን ዘግቶ ጋደም ብሏል።ድካም ሲጫነው ግን ዕንቅልፍ እያታለለው ቆይቶ በመጨረሻ የምሩን ተኝቷል።ተስፋዬ ለረዥም ሰአታት ያለመንቀሳቀስ መተኛቱ ያለበትን እስኪረሳ አድርጎታል። ባልተለመደ ሁኔታ እንዲህ መዳከሙም የቤቱን መብራት ሳያጠፋ ለሊቱ እንዲጋመስ ግድ ብሏል።
ለሊት 8፡00 ሰዓት
ቀኑን በመንደሩ ተገኝቶ ሲዞር የዋለው በሀይሉ አሁን ካሰበው ስፍራ ደርሶ ዙሪያ ገባውን መቃኘት ጀምሯል።የአካባቢው ጨለማነት ከለበሰው ጥቁር ጃኬት ጋር ተዳምሮ ማንነቱን ደብቆታል።ኮቴውን አጥፍቶ ከቂሊንጦ የታችኛው ሰፈር ሲቃረብም ከሌሊቱ ሰምንት ሰዓት ሆኖ ነበር።በቆርቆሮ ከታጠሩት ግቢዎች አንደኛው አጠገብ ሲደርሰ እርምጃውን ቀነስ አድርጎ ወደ ውስጥ አንጋጠጠ።
ግቢው በጨለማ ተውጦ ጭርታ ነግሶበታል።በአካባቢው የውሾች ድምጽም ሆነ የሌላ ነገር ኮሽታ አይሰማም። እንዲህ መሆኑ ለበሀይሉ አመቺ ነበር።በጎኑ የሻጠውን ስል ጩቤ እየዳሰሰ አጥሩን ዘሎ ሲገባ የነበረው ዝምታ አልተቀየረም።እግሮቹ መሬት እንደረገጡ ጎን ለጎን ተደጋግፈው የቆሙትን ቤቶች አሻግሮ ቃኛቸው።ከአንደኛው በቀር የሁሉም መብራቶች ጠፍተዋል።
በሀይሉ ዙሪያቸውን በላስቲክ ከተሸፈኑት ትንንሽ ቤቶች አለፍ ብሎ መብራት ወደሚታይበት መኖሪያ አመራ።የተስፋዬ ቤት ነበር።የቤቱ ግድግዳ በበቂ የጭቃ ምርግ የተሸፈነ አለመሆኑ በእንጨቶቹ መሀል ባለ ቀዳዳ ወደውስጥ እንዲያጮልቅ አገዘው።ይህኔ ባለአበባ ደማቅ አልጋ ልብስ ደርቦ ከአልጋው ላይ የተኛውን ተስፋዬን ቁልጭ ብሎ ታየው።
አሁንም ካለበት ሆኖ ወደውስጥ መቃኘቱን ቀጠለ።ዓይኖቹ በጠባቧ ክፍል ደርሰው ሲመለሱ ከአንዲት አነስተኛ ወንበር የተቀመጠና ቻርጅ የሚደረግ ነጭ ሞባይል መኖሩን አረጋገጠ።ከዚህ በኋላ ብዙ መቆየት እንደሌለበት ያመነው በሀይሉ እጁን ወደውስጥ አሾልኮ በሩን ከፈተና ከቤቱ መሀል ደረሰ።ይህ ሁሉ ሲሆን በከባድ ዕንቅልፍ ውስጥ የነበረው ተስፋዬ ካለበት አልተነቃነቀም።
በሀይሉ ኮቴውን አጥፍቶ ወደ ሞባይሉ ተጠጋና ቆመ።የተኛውን ሰው ትንፋሽ በድጋሚ አረጋግጦም ሞባይሉን ከቻርጀሩ ሲያላቅቅ በቤቱ የተለየ ድምጽ ተሰማ።ይህኔ ተስፋዬ ከዕንቅልፉ ባነነና ከበሀይሉ ጋር ተፋጠጠ።ወዲያውም በድንጋጤ አንገቱን ይዞ ‹‹ሌባ፣ሌባ፣ሌባ… እያለ መጮህ ጀመረ።ያላሰበው የገጠመው በሀይሉ ልብሱን ለማስለቀቅ እየሞከረ ከጎኑ የሻጠውን ስለት መዳሰስ ያዘ።
የተስፋዬ ጩሀት ሲበረታ ግን ሌሎች ደርሰው ከመያዙ በፊት ጩቤውን መዞ በደረቱ ላይ ሰካበት።ተስፋዬ እጆቹን ሲያነሳለት ሊተወው አልፈለገም።በድጋሚ ጀርባው ላይ ወግቶት ሲወድቅ ሞባይሉን ነቅሎ ያገኘውን ልብሶች ሰበሰበና አስቀድሞ በከፈተው የውጭ በር እየሮጠ አመለጠ።ሰፈሩን አቋርጦ አስፓልቱን እንደታሸገረም የወጋበትን ጩቤ ከመንገድ ወርውሮ ወደ ቤቱ ገብቶ ተኛ።
የፖሊስ ምርመራ
በማለዳው ከሰፈሩ የደረሰው ፖሊስ የወጣቱን አስከሬን መርምሮ በሰው እጅ ስለመገደሉ አረጋገጠ።በስፍራው ካሉት ጎረቤቶች መረጃ ሰብስቦም የድርጊቱን ፈጻሚ ለመያዝ ተንቀሳቀሰ።በመርማሪው ረዳት ኢንስፔክተር ሲሳይ ተሾመ የሚመራው ቡድን ከቀናት በኋላ የሟች ሞባይል ከአንድ ግለሰብ እጅ እንደሚገኝ ሲያውቅ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር አውሎ በጥያቄ አፋጠጠ።
ግለሰቡ ስልኩን ሁሌም ከሚጠጣበት ጠጅ ቤት ከአንድ ግለሰብ ላይ በ350 ብር ስለመግዛቱ አልደበቀም። የሰውየውን ማንነትና አቋም ከጠቋሚው የተረዳው ፖሊስ ተጠርጣሪውን ካለበት አስሶ ለመያዝ ጊዜ አልፈጀበትም። በሀይሉ ተይዞ ሲጠየቅ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ አልካደም።
ውሳኔ
በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 690/2010 ተጠናክሮ የተዘጋጀው ዶሴ ለክስ የሚያበቃውን መረጃዎች ሁሉ አጠናቆ መዝገቡን ለዓቃቤ ህግ በማሳለፍ ወደፍርድ ቤት አስተላልፏል። ጥቅምት 20 ቀን 2011 ዓም የተሰየመው የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከሳሹን የወንጀል ድርጊት ከህጉ ጋር በማገናዘብ ባሳለፈው ውሳኔም ተከሳሹ ‹‹ይገባዋል›› ያለውን የ16 አመት ጽኑ አስራት በማሳለፍ መዝገቡን ዘግቷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
መልካምስራ አፈወርቅ