ወይዘሮ ገነት እሸቱ እና ወይዘሮ አስቴር ያኢ በኦሮሚያ ክልል ሞጆ ከተማ 02 ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው፡፡በአካባቢያቸው የሚገኘው ሉሜ አዳማ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ዩኒየን ባቋቋመው ዱቄት ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ወይዘሮ አስቴር ለስድስት አመት አገልግለዋል፡፡ወይዘሮ ገነት ደግሞ 8ኛ ወራቸውን ይዘዋል፡፡ሁለቱም በፅዳት ስራ ተቀጥረው በሂደት ወደ ፋብሪካ ስራ እንደተዛወሩ ይናገራሉ፡፡
ወይዘሮ ገነትና ወይዘሮ አስቴር እንደገለጹት የጽዳት ሰራተኞች ሆነው በቀን 30 ብር ያገኙ ነበር ፡፡ ወደ ስንዴ ዱቄት ፋብሪካ ስራ ከተዛወሩ ወዲህ በቀን 40 ብር እየተከፈላቸው ነው የሚሰሩት፡፡ በሥራው ላይ የቆዩት ወይዘሮ አስቴር እንዳሉት የደመወዝ ክፍያው እያደገ ነው፡፡ ከስድስት አመት በፊት ለጽዳት ስራ ሲቀጠሩ በቀን 15 ብር ነበር ክፍያው፡፡አሁን የሚያገኙት ወርሃዊ ደመወዝ የኑሮ ውድነቱን የማይሸፍንላቸው ሆኖባቸው እንጂ ዩኒየኑ ተጨማሪ የስራ ዘርፎችን በማሳደግ የሰራተኛውንም ደመወዝ በማሻሻል የአካባቢውን ነዋሪ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡የስራ ቦታቸው በመኖሪያ አካባቢያቸው በመሆኑም ለትራንስፖርት አያወጡም፡፡ የዩኒየኑ ገቢ ሲያድግ የእነርሱ ደመወዝም እንደሚያድግ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡
በአካባቢው ያገኘናቸው አርሶአደር አሰፋ ለማ እንደገለጹልን ለዩኒየኑ ምርታቸውን በትራንስፖርትና በሸክም አጓጉዘው ገበያ ከመውሰድ በአካባቢያቸው መሸጥ መቻላቸው ድካማቸውን ቀንሶላቸዋል፡፡ ዩኒየኑ ገበያው ላይ ያለውን ዋጋ አይቶ ስለሚገዛቸው አይጎዱም፡፡ዩኒየኑ ምርጥ ዘር፣ ሸቀጣሸቀጥና ዳቦ ስለሚያቀርብላቸው ጠቅሟቸዋል፡፡
ዩኒየኑ የስንዴ ዱቄት ፋብሪካውን ከአምስት አመት በፊት ያቋቋመ ሲሆን፣ በቀን እስከ 360 ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም አለው፡፡ ተረፈምርቱንም ለመኖ በማቅረብ ገቢ ያገኛል፡፡ጎን ለጎን በቀን እስከ 20ሺ ዳቦ በመጋገር ለአካባቢው ህብረተሰብ እያቀረበ መሆኑን እንዲሁም ማህበሩ ከአርሶአደሩ ሰብል ሰብስቦ የሚያከማችበት አራት መጋዘን እንዳለውና ቦረና ከሚገኘው ከገዳ ዩኒየን ከአንድሺ በላይ ከብቶችን ተረክቦ ማድለብ መጀመሩን የዩኒየኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ታደለ አብዲ ገልጸውልናል፡፡ ዩኒየኑ የፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካ የማቋቋም እቀድ እንዳለውና ከማሽን ግዥ ጋር ተያይዞ በገጠመው ችግር መዘግየቱንም ነግረውናል፡፡
አቶ ታደለ እንዳሉት በምስራቅ ሸዋ የሚገኘው ሉሜ አዳማ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን በ1989ዓ.ም በ3ሺ740 ወንዶችና በ235 ሴት አባላትበ150ሺ ብር ካፒታል በአራት ህብረት ስራ ማህበራት ነው የተመሰረተው፡፡ባለፉት 16 አመታት ጊዜ ውስጥ 103 አባላትን ማፍራት ችሏል፡፡ካፒታሉም 55 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡በአሁኑ ጊዜም 73 ቋሚ ሰራተኞችና እስከ ሶስት መቶ ለሚሆኑ ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
ዩኒየኑ ከአባላት ምርት ሰብስቦ ከተመሳሳይ ዩኒየኖች፣ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፣እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ካሉ ትላልቅ ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ለተጠቃሚው በማቅረብ እንዲሁም ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ኬሚካል ፣ለእርሻ ትራክተር በተመጣጣኝ ዋጋ በማከራየት፣የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ አርሶአደሩን ተጠቃሚ በማድረግ፣ እህል የማበጠር አገልግሎት በመስጠትና ከብት በማድለብ የማህበሩን ገቢ ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል::
እንደ አቶ ታደለ ማብራሪያ ዩኒየኑ አሁን ከሚገኝበት ደረጃ በላይም ማደግ ይችል ነበር፡፡ነገር ግን ከውጭም ከውስጥም ጣልቃገብነት አለበት፡፡ዩኒየኑ በባለሙያዎች የሚመራ ባለመሆኑ በሂሳብ አያያዙ፣ገበያ በማፈላለግ፣በአጠቃላይ በገንዘብና በንብረት አያያዝ ላይ ችግሮች ነበሩበት፡፡የሙያ ምክክር አያገኝም፡፡ የገበያ ትስስሩም ጠንካራ አይደለም፡፡ከመንግስት የሚደረግለት ድጋፍ አነስተኛ ነው፡፡እነዚህ ሁሉ የሚፈለገው ውጤት ላይ አላደረሱትም፡፡ካለፈው አመት ወዲህ ግን እርሳቸውን ጨምሮ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ባለሙያዎች ተቀጥረዋል፡፡የቦርድ አባላትም በአዲስ አባላት ተተክተዋል፡፡አሁን ያለው እንቅስቃሴ ጥሩ ቢሆንም ብዙ መስራትና የጎላ ጥቅም ማስገኘት ይኖርበታል፡፡
ሉሜ አዳማ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን በውጤታማነታቸው ከሚጠቀሱት ጥቂቶቹ መካከል ቢሆንም አሁንም ገና በሚባል ደረጃ ላይ ነው፡፡የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ አብዲ ሙመድ እንዳሉት መሰረታዊ የህበረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ ገለልተኛ ቢሆኑም አልፎ አልፎ ከመርሀቸው ወጥተው እንዲንቀሳቀሱ የመንግስት ጣልቃገብነት አለባቸው፡፡ጣልቃገብነቱ ገበያ በመወሰንና በውስጥ አሰራራቸው ውስጥ በመግባት ይገለጻል፡፡ ይህ ደግሞ የሀብት ብክነት አስከትሎ ባቸዋል፡፡ የራሳቸውን ገንዘብ የሚያመነጩበት ባንክ የላቸውም፡፡ ስራዎች በተማረ ኃይል እንዲከ ናወኑ አለማድረግ፣ አመራሮቹም ጠንካራ አለመሆንና አሰራራቸውን አለማዘመን ክፍተቶቻቸው ናቸው፡፡
የማህበራትና የዩኒየኖች መጠናከር ሸማቹን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉና የመንግስትንም ጫና እንደሚቀንሱ ያለው ግንዛቤም አናሳ ነው፡፡ ማህበራቱን የመንግስት አካል አድርጎ ማየት በስፋት ይስተዋላል፡፡ በማህበራት በኩልም በተለይ ሸማቾች የፍጆታ እቃዎችን ብቻ በማከፋፈል ለመቀጠል ፍላጎት መኖርና ሌሎችም ችግሮች ጠንካራ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች እንቅስቃሴ ለውጥ ቢኖርም እድገታቸው የተመጣጠነ አይደለም፡፡ጠንካራ፣መካከለኛ እና ለስም ብቻ የተደራጁ ተብለው ተለይተዋል፡፡
ሀሳቡን በማጠናከር የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር በየነ ታደሰ‹‹ዩኒየኖችና ማህበራት የብዙ ባለቤት ግን ባለቤት የሌላቸው››ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ጠንካራ እንዳይሆኑ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከልም የአመራር ብቃት ማነስ፣ሂሳባቸውን የማስመርመር ልምድ አለመኖር፣ለሙስና መጋለጣቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ በሀገሪቷ ካሉ ዩኒየኖችና ማህበራት ሁለት አስርት አመታት ዕድሜ ያስቆጠሩ የቡና አምራች ዩየኖች ምርታቸውን ለውጭ ሀገር ገበያ እያቀረቡ እንኳን ጠንካራ የሚባሉ እንዳልሆኑና ለአባላቶቻቸውም የትርፍ ክፍፍል እንደማያከናውኑ ያስረዳሉ፡፡
ዶክተር በየነ እንዳስረዱት ዩኒየኖችም ሆኑ ማህበራት በበጎ ፈቃድ በተደራጀ ኮሚቴ ነው የሚመሩት፡፡ኮሚቴ በየሰአቱ የሚለዋወጠውን ገበያ አይቶ የሚወስን አይደለም፡፡ኮሚቴ በወር አንዴና ከዛም በላይ ሲመቸው ነው ስብሰባ የሚያካሂደው፡፡ በዚህ አካሄድ ለውጥ ማምጣት አይታሰብም፡፡ መንግስት ከማህበራቱ ገቢ ስለማያገኝ ትኩረት አልሰጣቸውም፡፡ማህበራቱ ክትትልና የአመራር ስልጠና ያስፈልጋቸዋል፡፡
ዶክትር በየነ ከሁለት አመት በፊት በፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ላይ ባካሄዱት ጥናት በወቅቱ የተገኘው መረጃ የማህበራት ቁጥር መጨመር ነው፡፡ይህም ቢሆን ቁጥሩ መጨመሩ እንጂ በምን ዘርፍ እንደተሰማሩ በተሟላ ሁኔታ አያሳይም፡፡ የአብዛኞቹ ማህበራት አድራሻም በትክክል አይታወቅም ፡፡ የሚቀርቡ ሪፖርቶችም ማህበራቱ ምን እንደሰሩና ምን እንዳተረፉ አይገልጽም፡፡ ከቀረበም እጅግ በጣም ጥቂት ማህበራት ናቸው፡፡ አንዳንድ ማህበራትም የተቋቋሙበትን ዓላማ ሳያሳኩ ተበታትነዋል፡፡ በመካከላቸውም መግባባት የላቸውም፡፡ ችግሮቹ ሰፊ እንደሆኑና ለመለወጥ የሚደረገው ጥረትም ደካማ እንደሆነ ዶክተር በየነ ያስራደሉ፡፡ችግሩ ደግሞ ካለፈው ስርአት ጀምሮ የቀጠለ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡
እርሳቸው እንዳሉት ባለፈው ስርአት የግብርና ሜካናይዜሽን ወይም በትራክተር ማረስ ቢጀመርም ከዚህ ባለፈ ማህበራቱ ጠንካራ ነበሩ ለማለት አያስደፍርም፡፡አሁንም ከ1997ዓም ወዲህ የመንግስት መዋቅር በማህበራቱ ውስጥ በመግባቱ ስለማህበራቱ እድገትና ስለስራ ዕድል መፍጠር መሆኑ ቀርቶ አጀንዳቸው ፖለቲካ ላይ እንዲያተኩር ያደረገ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ ክትትልና ዳጋፍ እንዲያደርግ የተቋቋመው የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲም ከፖለቲካ የጸዳ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡
የህብረት ስራ ማህበር በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፋ ለመጣው ዘመናዊ የሽርክና ማህበር ፈር ቀዳጅ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር በየነ ህብረት ስራ ማህበር በተለይ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ጠቃሚ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡የጋራ ዓላማ ያላቸው አንድ ላይ ተሰባስበው ሀብት የሚያፈሩበት ብቻ ሳይሆን ገበያ በማረጋጋት፣ በውስን ባለሀብቶች ቁጥጥር ስር ሆኖ የሚቀርበውን ምርትና አገልግሎት እንዲሁም ህገወጥ ንገድ በማስቀረት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ በተለይ በህገወጥ ከሀገር ውጭ ለገበያ የሚቀርቡ የቅባት እህሎችን በማስቀረት የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲጨምር በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና አላቸው፡፡
የህብረት ስራ ማህበራት አደረጃጀታቸው መሰረታዊ፣ዩኒየንና ኮንፌዴሬሼን ቢሆንም ኮንፌሬሬሽን አልተመሰረተም ፡፡ጤናማ ሕብረት ስራ ማህበርን መፍጠር የሚቻለው ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን፣ የባለቤትነት ስሜት ሲኖርና አባላትም ሲቆጣጠሩ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ከፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፉት ሰባት አመታት መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት ቁጥር 55በመቶ ጨምሯል፡፡2003ዓ.ም 38ሺ454 ነበሩ፣2010 ዓ.ም 85ሺ494 ደርሷል፡፡ዩኒየኖች በ2003ዓ.ም 245 ነበሩ በ2010ዓ.ም 388 ደርሰዋል፡፡ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት20ሚሊዮን አባላት አፍርተዋል፡፡የሴቶች የአባልነት ድርሻም 31በመቶ ደርሷል፡፡የኅብረት ስራ ማህበራቱ በአይነት ደግሞ 31በመቶ ግብርና፣36 በመቶ ገንዘብን ቁጠባ ፣8በመቶ ሸማቾች፣25 በመቶ ደግሞ የተለያዩ የሙያ ዘርፎች ናቸው፡፡ የህበረት ስራ ማህበራት ከ2006ዓ.ም እስከ 2010ዓ.ም ባሉት አመታት ለአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ዜጎች የሰራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡
በፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ የፋይናንስ ህብረት ስራ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክትር አቶ ብርሃኑ ዱፌራ የህብረት ሰራ ማህበራት የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ እንደገለጹት ኤጀንሲው ባዘጋጀው የ15 አመት ፍኖተ ካርታ ላይ የሀገር ውስጥ ግብርና ምርቶች ድርሻን 70 ከመቶ፣የውጭ ግብይት ድርሻን 65በመቶ፣ለገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶች መቶ በመቶ እሴት የተጨመ ረባቸው እንደሆኑ ታቅዷል፡፡
የግብርና ሜካናይዜሽን አቅርቦትና አገልግሎት 50 በመቶ ማድረስና 12 የህብረት ስራ ልህቀት ማዕከሎች ግንባታ በዕቅዱ ተካትቷል፡፡60በመቶ የሚሆኑ የግብርና ህብረት ስራ ማህበራትም ከቀላል እስከ ከባድ ኢንዱስትሪ ገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ስራ በመስራት ለ20ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል የመፍጠሩም ተግባር የዕቅዱ አካል መሆኑን አቶ ብርሃኑ አመልክተዋል፡፡
የህብረት ሥራ ማህበር በኢንዱስትሪ አብዮት በእንግሊዝ ማንችስተር እ.አ.አ.በ1844 እንደ ተመሰረተና እ.አ.አ.በ1852 ህግ እንደወጣለት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡በኢትዮጵያም 60 አመት ዕድሜ እንዳለው መረጃዎቹ ይገልጻሉ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
ለምለም መንግሥቱ