ተወልደው ያደጉት ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ከአምቦ ከተማ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቶኬ አካበቢ ነው፡፡ እኚህ የገበሬ ቤተሰብ ያፈራቸው ታዋቂና አንጋፋ ፖለቲከኛ ከፖለቲካው ጎን ለጎንም ራሳቸው በተማሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዛሬም ድረስ በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ለኦሮሞ ህዝብና ፍትህን ላጡ ዜጎች ዘብ በመቆም በግንባር ቀደምትነት የሚነሱት የፖለቲካ ምሁሩ በውጭና በአገር ውስጥ ከሚገኙ ደጋፊዎቻቸውና አድናቂዎቻቸው መኖሪያ ቤትና ዘመናዊ መኪናን ለመሸለምም የበቁ ናቸው፡፡
የዛሬው የአዲስ ዘመን ተጠየቅ አምዳችን እንግዳ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ናቸው። ከእንግዳችን ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡
አዲስ ዘመን ፦ የፌዴራሊስት ኃይሎች በሚል መቐለ ላይ በተካሄደው ስብሰባ አልተጋበዛችሁም ?
ፕሮፌሰር መረራ፦ መጠራት ተጠርተናል ግን አልሄድንም።
አዲስ ዘመን፦ ለምን ቀራችሁ?
ፕሮፌሰር መረራ፦ ባለው ሁኔታ ተጨማሪ ችግር እንዳንፈጥር ብለን ነው የቀረነው።
አዲስ ዘመን፦ መገኘታችሁ ምን ዓይነት ችግር ይፈጥራል?
ፕሮፌሰር መረራ፦ ኢህአዴግ እራሱ ውዝግብ ውስጥ ገብቷል ፤ አንድ ሆኖ ወደ ውህደት እየሄደ አይደለም። በዚህም የተነሳ የራሳቸው ጭቅጭቅ አላቸው። እኛ ደግሞ ተጨማሪ ችግር እንዳንፈጥር አስበን ነው ። በሌላ በኩልም ሁኔታው ብዙ ትርፍ እያየንበት ስላልሆነ በስብሰባው ላይ መገኘት አልፈለግንም።
አዲስ ዘመን፦ ስብሰባውን እንዴት አገኙት እርስዎ?
ፕሮፌሰር መረራ፦ በአጠቃላይ ኢህአዴግ አንድ ሆኖ ወደ ውህደት መሄድ አልቻለም፤በተለይ በለውጡ ፍጥነትና ጥልቀት ላይ ስምምነት የላቸውም። ከዚህም በላይ ደግሞ ምን ዓይነት ለውጥ የሚባለው ላይ የጋራ ስምምንት አልፈጠሩም። በዚህ ሁኔታ ወደፊት እየተገፋ ነው እንግዲህ ያሉት፤ የኢህአዴግ መዋቅር እንደ መዋቅር አንድ ላይ ወደፊት መሄድ አልቻለም። መጨረሻቸውን አናውቅም። ምንልባትም ከዚህ የበለጠ ውዝግብ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፤ አልያም በስምምንት መፋታት ሊኖር ይችላል። በጠቅላላው ግን ሰፊ ውዝገብ ሊፈጥር የሚችል ጉዳይ ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፦ ይህ ስምምነት ላይ አለመድረስ በዚሁ ከቀጠለ እንደ አገርና ህዝብ የሚያስከፍለው ዋጋ አይኖርም?
ፕሮፌሰር መረራ፦ አገሪቷንና ህዝቦቿን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም ዋጋ ሊያስከፍላቸው የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። ወደ ግጭት ሊያስገባ ይችላል። ግጭቱ ደግሞ የህይወት መስዋዕትነት ሊጠይቅ ይችላል ።
አዲስ ዘመን፦ ይህንን ለማርገብ መንግሥት የሚሠራው ወይም የሚጠበቅበት ኃላፊነት እንዳለ ሆኖ እንደ እናንተ ያለ በፖለቲካው ውስጥ ብዙ ልምድ ያለው ፓርቲ ሚናው ምን ሊሆን ይችላል?
ፕሮፌሰር መረራ፦ ኢህአዴግ አንድ ሆነ 11 መብቱ ነው። ግን መሰረታዊ የሆኑትን የአገሪቷን ችግሮች ዝም ብሎ ጥሎ እንዳይሄዱ እኛ እንደ ኦሮሞ ድርጅት እንፈልጋለን።
አዲስ ዘመን ፦ የትኞቹ ጉዳዮች ናቸው ጥለው እንዳይሄዱ የምትፈልጉት ? ከመፈለግ ባሻገርስ የራሳችሁን ኃላፊነት ለመወጣት ያላችሁ ቁርጠኝነት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ፕሮፌሰር መረራ፦ እኛ እንደ ኦሮሞ ድርጅት ለምሳሌ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ፣ በማንነት ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝምና ሌሎችም ጥያቄዎች መልስ ወይም መፍትሔ ሳያገኙ ዝም ብሎ አንድ ሆንን ተብሎ ተጥለው የሚኬዱ ነገሮች እንዳልሆኑ ደጋግመን እየተናገርን ነው። ይህንንም እኛ እንደ ፓርቲ አጥብቀን እንጠይቃለን።
በሌላ በኩልም አንድ የሆነው ኢህአዴግ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫን በሚመለከት ዝም ብሎ አላስፈላጊ ጨዋታ ውስጥም እንዳይገባ እንፈልጋለን ። ግን አንድ ሆነ 11 የራሱ መብት ነው ።መሰረታዊ የሆኑ ራስን በራስ የማስተዳደርና ሌሎች ጥያቄዎችን ትቶ መሄድ ግን ዋጋ ያስከፍላል።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ በኦሮሚያ ክልል በርካታ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርዎች ይንቀሳቀሳሉ፤ ኦፌኮ ለምርጫ ሲቀርብ ራሱን ችሎ ነው፤ ወይስ የመዋሀድ ሃሳብ አለው?
ፕሮፌሰር መረራ፦ እኛ መድረክ አለን። ከኦሮሞ ድርጅቶች ጋርም ሆነ ከሌሎቹ ጋር አብረን እንሠራለን። በዚህ ደረጃም ብዙ የጠየቁን ፓርቲዎች አሉ። እየሠራንበትም ነው። በኦፌኮ በኩልም ቀደም ብለንም ቢሆን ከሰባት ዓመት በፊት ነፃ ሆኖ ከሚንቀሳቀስ ፓርቲ ጋር ውህደት ፈጥረናል። አሁን የምንጠብቀው ከውጭ ከገቡና የኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር ውህደት መፍጠር ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ አስቀድሞ አካሄዳቸውን መቃኘትና በምርጫ ቦርድ መመዝገባቸውን ማጤን ይጠበቅብናል። ምርጫው እውን መሆኛው ሲቀርብም ተደራድረን ወደ ውድድር እንገባለን። ብዙ የሚያስጨንቀን ነገርም የለውም።
አዲስ ዘመን፦ በነባሩ ኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ያለው አለመግባባት በምን መልኩ ሊፈታ ይገባል ይላሉ?
ፕሮፌሰር መረራ፡- እሱን እንግዲህ እኛ ቀደም ብለንም ለመምከርም ሞክረናል። ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር ማለት ነው። እንዳውም ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት አዲስ ደም፤ አዲስ ኃይል ወደ መንግሥት እንዲገባ ኢህአዴግ መንገድ መክፈት አለበት ብለን ስንሟገት ነበር። አሁንም ለውጡ እዚያው ነው የሚሽከረከረው ባይ ነኝ። ውሳኔ የሚወሰነው፥ ድርድር የሚደረገው እዚው ነው። ስለዚህ ካሉበት ሳጥን ውስጥ መውጣትና ማሰብ ይገባቸዋል። እሱን እስከአሁን ድረስ አልጀመሩም።
ግን ደግሞ መፍትሔው እሱ ብቻ አይመስለኝም። ምክንያቱም እርስ በርስ እየተጓተቱ በተለይ ደግሞ ስልጣን ያጣው አካል እኔም ድምፅ አለኝ እያለ የለውጥ አራማጆችን እግር እየጎተተ ከሄደ የታሰበው ለውጥ ከግብ ይደርሳል ለማለት ይከብደኛል። ከዚህ መውጣት የሚቻለው በኢህአዴግ ቁመት ልክ የተሰፋው ጥብቆ ወደ 100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ መሻገር ሲችል ነው።
አሁን ግን በአንድ በኩል እነዶክተር አብይ አሉ ይላል፤ ከገፋንም ችግር ላይ ይወድቁብናል ብሎ ይፈራል፤ ዝም ማለቱ ደግሞ የተጨማለቁ ብዙ ነገሮች ይቀጥላሉ የሚል ስጋት ነው ያለው። ስለዚህ ለእኔ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አደገኛ የሆነ መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት። ስለዚህ እነዶክተር አብይ እነዚህን ነገሮች በጥልቀትም በፍጥነትም ሊሄዱባቸው ይገባል። አለበለዚያ ቦንብ በፈነዳ ቁጥር እሳት የማጥፋት ሥራ የትም አያደርሰነም። አጠቃላይ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ አቅጣጫ ማስያዝ ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የእርሶ ፓርቲ ለምርጫው ምንዓይነት ዝግጅት እያደረገ ነው?
ፕሮፌሰር መረራ፡- አቅማችን የፈቀደውን ያህል እየሠራን ነው። በአሁኑ ወቅት ስልጠና ውስጥ ገብተናል። ውይይቶችም እያካሄድን ነው። እርግጠኛ ነኝ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ዝግጅት አለን። ግን አሁን ዋናው ጉዳይ የእኔ ፓርቲ ስልጣን እንዲይዝ ማድረግ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ፈጣን ምላሽና ለውጥ እንዲያገኝ ማስቻል ነው።
ምርጫው ነገም ሆነ ከነገ በስቲያ በቂ ተወዳዳሪዎች አሉን ፤ የህዝብ ድጋፍም ያለን ይመስለኛል። ስለዚህ ለኦፌኮ ምርጫው የሚያስጨንቀው አይሆንም።
አዲስ ዘመን፦ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ግን ኦሮሚያ ክልል ላይ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማድረግ ይቻላል ብለው ያምናሉ?
ፕሮፌሰር መረራ፦ ችግሩ ምንድነው? አንዳንድ ሰዎች አይቻልም የሚል ሃሳብ ያነሳሉ። እኔም ቢሆን አስቸጋሪ እንደሚሆን እገነዘባለሁ። ነገር ግን ከዚህ የተሻለ ጊዜ ሊመጣ ይችላል ወይ ? የሚለው ደግሞ መመለስ ያለበት ጥያቄ ይመስለኛል። ግን እየባሰበት ነው የሚሄደው፡፡ ሰዎች መናገር ከጀመሩ ወዲህ ነው ችግሮች ጎልተው እየወጡ ያሉት ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ምንም የተስተካከለ፣የተሻሻለና መግባበት ላይ የተደረሰበት ነገር የለም ።
በመሆኑም ከዚህ የተሻለ ሁኔታ ይፈጠራል ብለን ምርጫው ይዘግይ የምንልበት ምክንያት የለንም። የመንግሥት መዋቅርም ሆነ ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ ችግር ውስጥ ገብቷል። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ይዘን ከዚህ የተሻለ ሁኔታ ፣ጊዜ ይመጣል ብሎ ማሰቡ ለእኔ የሚያስኬድ ነገር አይደለም። በተቻለ መጠን ወደፊት ከመግፋት ውጪ ሌላ አማራጭ ያለን አይመስለኝም።
አዲስ ዘመን፦ የፌዴራሊስት ኃይሎች በተሰኘው የመቐሌው ስብሰባ ላይ የተካፈሉት ኢህአዴግ ቀለብ የሚሰፍርላቸው በማለት በተደጋጋሚ ገልጸዋቸዋልና ይህ ምን ማለት ነው?
ፕሮፌሰር መረራ፦ ኢህአዴግ ባለፉት 27 ዓመታት ሲያደራጅ ነው የኖረው፡፡ ለምሳሌ በእርሱ አደራጅነት ከቅንጅት የወጡ ከእኛም ፓርቲ ተገዝተው የሄዱ እንዲሁም ከሌሎችም እንደዚያው አሉ፤ ራሳቸውን ችለው ነፃ የፖለቲካ ድርጅቶች ይሁኑ አይሁኑ እርግጠኛ ባልሆንም እኔ የማውቃቸው ግን ከፍተኛ ችግር ያለባቸው ናቸው።
አንዱ ኢህአዴግ እነዚህን ይዞ መቀጠል ሲያቅተው ሌላው የኢህአዴግ ክንፍ ደግሞ ይዞ ለመሄድ እየሞከረ ይመስላል። እኔም ከዚህ ታሪካቸው ተነስቼ ነው የኢህአዴግ ቀለብተኛ ናቸው ወደሚለው የሄድኩት።
አዲስ ዘመን፦ እነዚህ ቀለብ የሚሰፈርላቸው ያሏቸው ፓርቲዎች ወይም ግለሰቦች ምን ያህል ርቀትስ ከኢህአዴግ ጋር አብረው ይጓዛሉ ማለት ይቻላል?
ፕሮፌሰር መረራ፦ ይህንን እንግዲህ ውህደት የፈጠረው ኢህአዴግ ጥንካሬና ህወሓት እስከምን ለመሄድ ነው ስትራቴጂ የነደፈው የሚለውን አናውቅም። ለምሳሌ
ኢህአዴግ ከፈረሰ በኋላ አሁን ያለው መንግሥት ህጋዊ ስለመሆኑም እየተጠራጠረና አላውቅም እስከማለት እየሄደ ነው፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ ለማዕከላዊ መንግሥት አልገዛም፤ አልቀበልም ማዕከላዊ መንግሥት ህጋዊ አይደለም ማለት በእርግጥ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ተፈራርመውና ተስማምተው መንግሥት የፈጠሩበት አካሄድ አሁን ላይ በመፍረሱ። ከዚህ በኋላ ያለውን መንግሥትም ህጋዊነት ላይ መከራከር ይችላሉ። ግን ምን ያህል ርቀት አብረው ይጓዛሉ የሚለውን የሚመልሰው ጊዜ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ይህንን ችግር ሊፈታ የሚችለው ብቸኛው አማራጭ ምርጫ ነው ?
ፕሮፌሰር መረራ ፦ ምርጫው ያግዛል፡፡ የተለያዩ ማህበረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን መሪዎቻቸውን ከመረጡ በኋላ በኢህአዴግ ውስጥ ያለው ችግርም ሊረግብ ይችላል። ሌላ የሚፈጠረው መንግሥትም ምናልባት አሁን ካለው መንግሥት የተሻለ ውክልና፣ ድጋፍና ተቀባይነት ሊያገኝ ስለሚችል ችግሩ ወደ መርገቡና ወደ ድርድር ሊሄድ ይችላል። አሁን ያለው የኢህአዴግ መንግሥት ነው። እሱ ደግሞ ገመድ ጉተታ ውስጥ ገብቷል። ችግሩ ይህ ነው።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ ደጋግመው ስለ ብሔራዊ እርቅና መግባባት ያነሳሉና አሁን ደግሞ ምርጫ እየደረሰ አዲስ ውህድ ፓርቲም እየተመሰረተ ከመሆኑ ጋር ምን አስተያየት አለዎት? ብሔራዊ መግባባቱስ ተፈጥሯል ማለት እንችላለን?
ፕሮፌሰር መረራ፦ በተወሰነ ደረጃ ኦሮሚያ አካባቢ ይሻል ይሆናል እንጂ በቂ ብሔራዊ መግባባት የትኛውም አካባቢ ላይ አልመጣም። የቀጣዩ ምርጫ ትልቁ ፈተናም ብሔራዊ መግባባት በአገሪቷ ባልሰፈነበት ሁኔታ መካሄዱ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ብሔራዊ መግባባቱን ለማምጣት ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
ፕሮፌሰር መረራ፦ በዋናነት ገዥው ፓርቲ በቂ ሥራ መሥራት ይኖርበታል። ለምሳሌ በብሔራዊ መግባባት አቅጣጫ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች እንዲሰባሰቡ እንዲደራደሩ ማድረግ ያለበት እርሱ ነው። መጀመሪያ ዶክተር አበይ ስልጣን ላይ እንደወጡ ወይም አቶ ኃይለማርያም የስልጣን ማብቂ ጊዜያት ውስጥ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ያስፈልጋል፤ ይህንን ለውጥ ለመምራትና በተሻለ ስብስብና እውቀት እንዲሁም ልምድና ችሎታ ባለቸው ኃይሎች የለውጥ መዋቅሮቹ ካልተመሩ በቀር ዝም ብሎ በአንድ ፓርቲ ፍላጎት ብቻ መሄዱ ዋጋ ሊያስከፍል ስለሚችል ድርድር ያስፈልጋል ብለን አቅርበን ነበር።
በዚህም ወሳኝ የሆኑና ብዙ የህዝብ ተቀባይነትና ተሰሚነት ያላቸው እንዲሁም ለችግሩም ለመፍትሔውም አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ኃይሎች ተሰባስበው ወደዚህ አካሄድ ቢሄዱ ጥሩ ነበር፤ ግን ማድረግ አልቻሉም። እነሱ ቢገቡ ኖሮ ብሔራዊ መግባባቱም ህይወት ሊኖረው ይችል ነበር። ካቀረብናቸው ሃሳቦች መካከል መንግሥት በራሱ የተወሰኑትን ለመመለስ ቢሞክርም ፍሬያማ ሳይሆን ቀርቷል። አሁንም ዋጋ እያስከፈለን መጥቷል። እኛ ቀድሞውንም የያዝነው አቅጣጫ እርሱ ነው፤ ወደፊትም ይሻላል ብለን የምንለው ያንኑ ነው።
በተለይም ትላልቅና አቅም አላቸው የሚባሉ ባለድርሻ አካላት ይህን የጋራ ለውጥ ቢመሩት ይሻላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የኢህአዴግ መንግሥት እስከ ምርጫ ድረስ ሊቀጥሉ ይችላሉ። ነገር ግን እውቀቱም ችሎታውም ፍላጎቱም ልምዱም ባላቸው ኃይሎች ለውጡን መምራት ቢቻል የተሻለ ስኬታማ ይሆናል። ብሔራዊ መግባባትና የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ለውጥም ሊመጣ ይችላል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ይህንን ለማድረግ ታዲያ ዝግጁነት የጠፋው በእናንተ የፖለቲካ ኃይሎቹ ዘንድ ነው ወይስ በመንግሥት በኩል ?
ፕሮፌሰር መረራ፦ የመንግሥት ዝግጁነት እኛ በምንፈልገው ልክ እየሄደ አይደለም። ምናልባት የአቅሙን ያህል እየሠራ ይሆናል ግን አሁን ባለው ሁኔታ ይህ ጨዋታ በቂ አይደለም። አገሪቱ ወደፊት እንድትሄድ ከተፈለገ፤ ወደምርጫም ልንሄድ ከሆነ ፤ከዚያ በኋላ ሽግግሩን በተሻለ ሁኔታ የሚመራ ብሔራዊ መግባባት ቢፈጠር ጥሩ ነው።
ከዚያ በኋላም ደግሞ ስልጣን የሚይዘው አካል 50 በመቶ ድምፅ አግኝቻለሁ በሚል ሳይሆን አብዛኛውን ባለድርሻ አካላት በመያዝና ብዙሐኑም የእኔ መንግሥት ነው ሊል በሚችልበት ሁኔታ መዋቀር ይኖርበታል።
ለምሳሌ እኛ ብናሸንፍ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንመሰርታለን የሚል አቋም ነው ያለን። አሁን ያለው ሁኔታ ‹‹እነንትና ከተመረጡ ወይም የበላይነት ካገኙ እኔ እጠፋለሁ፣እንዲህ እሆናለሁ፣ እታሰራለሁ›› ከሚል ስጋት ነፃ ሆኖ አብሮ ፖለቲካ መሥራት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባትም ሊመጣ የሚችለው እነዚህ ችግሮች ሲፈቱ ነው ።
አዲስ ዘመን፦ ምርጫው እየተቃረበ ነው፤ አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ መካሄድ አለበት ብለው ያምናሉ?
ፕሮፌሰር መረራ፡- የእኔ እምነት በተያዘለት ጊዜ ምርጫው መካሄድ አለበት የሚል ነው። ይህንን ለማለት ያስገደደኝም ሁለት ትላልቅ ስጋቶች ያሉኝ በመሆኑ ነው። አንደኛው ለውጥ የሚባለው ነገር ወደ ታች አልወረደም፤ ሁለተኛው የቀበሌና የወረዳ ምርጫዎች እስከአሁን አለመካሄዱ ህዝብ ባልመረጣቸው ሰዎች እየተመራ ባለበት ወቅት ምርጫ ማራዘሙ የከፋ ችግር ያመጣል ብዬ ስለማስብ ነው።
ለእኔ እስኪመች ድረስ ብሎ ጊዜ መውሰድ ህዝብ ስህተት ሲሠራ መጠየቅ የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም። ስለዚህ ህዝብን ወደዚያ ሁኔታ መግፋቱ አስፈላጊ አይደለም። ሌላው ስጋቴ ከዚህ የተሻለ ጊዜ ይኖረናል ወይ? የሚለው ነው። ህዝብ ባልመረጠው አካል ነው እየተገዛ ያለው። ኢህአዴግ ባለፈው ምርጫ በምን መልኩ ስልጣኑን እንዳራዘመ እየታወቀ አሁንም ምርጫው ይራዘም ማለት ላልፈለግነውና ላልጠበቅነው ችግር ሊያስገባን ይችላል።
በተለይም ወጣቱ ለውጥ የሚፈልገው አሁን ነው። የምርጫውን መራዘም አልታገስም ካለ ይህ ወጣት ማነው ሊያሳምነው የሚችለው? ስለዚህ ኢህአዴግ በዚህ ጉዳይ ላይ ደጋግሞ ማሰብ አለበት።
ዋናው መታየት የሚገባው ውድ ዋጋ የሚያስከፍል የፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ እንደሚያስገባን ማወቁ ነው። ይህንን ማድረጉ ብዙ ቅሬታ ያለውን ህዝብ ልብ ሊገዛ ይችላል። የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል ምርጫ መካሄድ ያለበት ለዚህ ህዝብ እንጂ ዝግጅት ያንሰናል ለሚሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሲባል አይደለም። ስለዚህ ይህ የምርጫ ጉዳይ መጥፎ ቁማር እንዳይሆን ስጋት አለኝ።
እዚህ ላይ ምርጫውን ነፃና ፍትሐዊ እንዲሁም ሰላማዊ ማድረግ የአንድና የሁለት ፓርቲዎች ፍላጎት ሳይሆን ገዥው ፓርቲም መንግሥትም ተጽዕኖ ፈጣሪ የፖለቲካ ኃይሎች እንዲሁም ማህበረሰቡ ሁሉም የራሱን ድርሻ መወጣትና የቤት ሥራውን መሥራት መቻል አለበት። ምንም እንኳን ዋናው ቁምነገር መንግሥት እጅ ላይ ያለ ቢሆንም።
አዲስ ዘመን፦ ከምርጫው በኋላ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት መንግሥት ይኖራታል ብለው ያስባሉ?
ፕሮፌሰር መረራ ፦ እኔ ማንም ይመረጥ ማንም ብሔራዊ አንድነት መንግሥት ቢሆን ይመረጣል። ዝም ብሎ 50 በመቶ አግኝቻለሁ በሚል አገርን እንመራለን የሚለው ነገር ዋጋ ያስከፍላል። ስለዚህ የእኔ ራዕይ ለአምስቱ መሸጋገሪያ ጊዜ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ቢቋቋም ይሻላል።
አዲስ ዘመን፦ እንደ አንጋፋ የፖለቲካ ሰው አሁን አገሪቷ ላይ ለተከሰተው አለመረጋገት መንስኤው፣ ተጠያቂውና መፍትሔው ምንድን ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰርመረራ፦ ተጠያቂው ከመንግሥት ጀምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ቢሆኑም ዋናው ግን መንግሥት ነው። ላለፉት 27 ዓመታት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ብሎ ከሁለቱም ያልሆነ አስተዳደሩን በጉልበት ህዝቦች ላይ ሲጭን ነበር፤ የአንድ ፓርቲ ገናናነትን ፈጥሮ ሲያፍን ፣ ተራው የእኔ ነው ብሎ መጠነ ሰፊ የሆነ ዘረፋን ሲያካሂድ ቆይቷል፤ ከዚህ አንጻር በዋናነት ተጠያቂው እርሱ ነው።
በሌላ በኩልም በእኩልነት ላይ የተመሰረተ መንግሥታዊ ሰርዓት አልፈጠሩም፤ ፌዴራሊዝም አሉ ግን እሱም ቢሆን ሀቀኛ ፌዴራሊዝም ሳይሆን የነበረው የሞግዚት አስተዳደር ነው። ከዚህ አንጻር አሁን የምናያቸው ብዙ ችግሮች የተፈጠሩት በዚህ ምክንያት ነው። እዚህ ላይ ግን ሌሎች ኃይሎች ደግሞ የራሳቸው ስግብግብነት ገኖባቸው ያበረከቱት አስተዋጽዖ የለም ማለት አይደለም።
27 ዓመታት የገዛው ኢህአዴግ አንድ፤ ቀጥሎ የመጣው ኢህአዴግ ሁለት አሁን ደግሞ ኢህአዴግ ሦስት ይሁን ብልጽግና ፓርቲ አካባቢ የተፈጠሩ ነገሮች መንስኤ ናቸው።
አሁንም ደግሞ እናገራለሁ አገሪቷና ህዝቧ ወደ ብሔራዊ መግባበት ካልገቡና ፖለቲካዊ ጨዋታው ካልተለወጠ ኢትዮጵያ ከዚህ ጣጣ አትወጣም።
አዲስ ዘመን፦ የመንግሥት ችግር እንዳለ ሆኖ አገር እንድትተራመስ የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ ያሉት የፖለቲካ ኃይሎችስ እንዴትና መቼ ነው መጠየቅ ያለባቸው ይላሉ?
ፕሮፌሰር መረራ፦ መነሻችን በዋናነት ጨዋታውን የቀየረው ማነው የሚለው ነው፡፡ እዚህ ላይ እዚህ ጨዋታ ውስጥ የገቡ ኃይሎች ምንም አላደረጉም ንጹሐን ናቸው የሚል አስተሳሰብ የፖለቲካ የዋህነት እለዋለሁ። ግን በዋናነት የዚህ ስርዓት ፈጣሪዎችና እዚህ ያደረሱት በስርዓቱም ህዝብን የበደሉና ያሠሩ የዘረፉና ያዘረፉ ኃይሎች ናቸው ተጠያቂዎቹ። መቼ የሚለው ግን መልሱ ከባድ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ህወሓት አሁን ካለው የአገሪቱ ሁኔታ እራሱን አግልሎና ውህደቱንም ሳይቀበል ቀርቷል፤ ይህ ሁኔታ በእርስዎ አረዳድ ፖለቲካዊ እንደምታው ምን ሊሆን ይችላል?
ፕሮፌሰር መረራ፦ ይህንን ውሎ አድሮ የምናየው ይሆናል፤ አሁን ላይ እየተደራደሩ ነው፤ ተደራድረውስ ምን ለማግኘት ነው? አሁን ያለውና ኢህአዴግን የተካውን አካል እንደ መንግሥት የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች ምን ያደርጉታል የሚለው በራሱ ገና የሚታይ ነው። አሁን ላይ ወደ ጉባኤ እንሄዳለን እያሉ ነው፤ ከጉባኤው የድርድር ሃሳብ ነው ይዘው የሚወጡት ወይም ማዕከላዊ መንግሥት ትዕዛዝና ፖሊሲዎችን አናከብርም፤ ህጋዊ መንግሥት አይደለም፤ ስለዚህ በአስቸኳይ ወደ ምርጫ እንሂድና የኢትዮጵያ ህዝብን ድምፅ ያገኘ መንግሥት ይፈጠር ነው የሚሉት የሚለው ነገር ገና ያልለየለት በመሆኑ ከጉባኤው በኋላ ማየቱ ይሻላል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ነው የሚገነዘቡት?
ፕሮፌሰር መረራ፦ አሁን አገሪቷ እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት። በመሆኑም ሁሉም ኃይሎች የራሳቸውን የቤት ስራ ሰርተው ሁኔታውን አቅጣጫ የማስያዝና የመረዳዳት በተለይም መሬት ላይ ህይወት ያለው ብሔራዊ መግባበት ውስጥ ካልተገባ በቀር አገራችንን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይገጥሟታል የሚል ኃሳብ ነው ያለኝ።
የመጠላለፍ ፖለቲካን መተውና እነዚህን የማስተካከል ስራ ላይ ቢያተኩር ኖሮ የሚደርሱት ችግሮች ይቀንሳሉ የሚል ነገር አለኝ። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥትን የምመክረው ፖለቲካችንን ለማስተካከል ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። በዋናነትም ለአገራችን ብሄራዊ መግባባት መፈጠር የበኩሉን ሚና መጫወት ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፡፡
ፕሮፌሰር መረራ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22/2012
እፀገነት አክሊሉ