ያለፈውን ሳምንት ጽሁፌን የቋጨሁት ቋሚ ተቃዋሚና ቋሚ ደጋፊ መሆንን የጽናት ምልክት አድርጎ የማየት ልማዳችንን እንጣል። እየደገፉ መንቀፍ ፤ እየተቃወሙ ማድነቅ ወላዋይነት አይደለም በሚል ነበር። ቀደም ብዬ የሀሳብ ቀብድ ስላስያዝኩ ሳምንት ያሞካሸሀትን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመውቀስ ብዕሬን ያነሳሁት በኩራት ነው።
በአዲስ አበባ የመሬት ዋጋ እሳት ነው። ከዚህ ቀደም በወጡ ጨረታዎች ለአንድ ካሬ ሜትር ከ350 ሺ ብር በላይ ዋጋ ሲቆረጥ የተመለከቱ ኗሪዎቿ በከተማቸው ተስፋ ቆርጠዋል። የመሬት ዋጋ ከመናሩ የተነሳ የአዲስ አበባ ኗሪ የቀብር ቦታ ሂሳብን እንኳን በአንድ እድር መሸፈን የማይችልበት ደረጃ ደርሷል። በዚህ ምክንያት አቅም ያለው ተጨማሪ እድር ለመቀላቀል ሲገደድ፣ ቀሪው ከነበረበት ዕድር ወጥቶ ተስፋውን ማዘጋጃ ቤት ላይ ጥሏል።
የቀብሩን ቀን የክብሩ ጥግ አድርጎ ከሰርጉ ቀን ጋር አስተካክሎ “ሰርግና ሞት አንድ ነው” ብሎ ለሚዘፍንና የበደለውን “ቀብሬ ላይ እንዳትቆም” እያለ ቅያሜውን ለሚያጸና ማህበረሰብ ፣ የሶስት ክንድ መሬት ትርጉም ብዙ ነው። ሲኖር አትዮጵያዊ ሆኖ መሬት ያላገኘ ዜጋ ቢያንስ ሲሞት ኢትዮጵያ የመሆን መብቱ ያለቅድመ ሁኔታ ይከበርለት !
የአዲስ አበባ ኗሪ “መሬት ለባለሀበቱ” እየተባለ በሊዝ ወደጠረፍ ሲጠለዝ ኖሯል። በሊዝ… መጠለዝ እንዴት እንደሚያም ! አይን የሆኑ ቦታዎችን በውድ ዋጋ ለመቸብቸብ ሲባል ህይወታቸው በሊዝ የለዘዘባቸውን እንሰብስብ ብንል ስንት ሄክታር መሬት ይበቃን ይሆን ? ልጆቹን “አያ ጅቦ መጣ” ብሎ ያሳደገ ሁሉ ጅብ ወዳለበት ተሰዷል። የዘንድሮ ጅብ ሰው ወደ ጫካው ይመጣበታል እንጂ እርሱ ወደ መንድር አይሄድ። አሁን እንኳን ከረፈደም ቢሆን የከተማዋ ኗሪ በልማት ስም ህይወቱና ማህበራዊ ትስስሩ እንዳይፈርስ በኖረበት አካባቢ መልሶ ሰፍሮ የልማቱ አካል እንዲሆን ተወስኗል።
አሁን ያሉት ከንቲባ ስልጣን የያዙ ሰሞን “በምክትል ከንቲባው የሚመራው አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ካቢኔ ሪፎርም ያስፈልጋቸዋል ካላቸው ዘርፎች ግንባር ቀደሙ መሬትና መሬት ነክ ዘርፍ ነው።” ሲባል እልልታ ቀረሽ ድጋፍ ከቸሩት አንዱ ነበርኩ። ሰንበትብት ብሎ ለሪል ስቴት ፣ ለኢንዱስትሪ ፣ ለመኖሪያ ቤቶችና ለንግድ ሕንፃዎች በሊዝ ጨረታና በድርድር የተሰጡ ቦታዎች ኦዲት ይደረጋሉ ተባለ። በኦዲት ወቅት ከሕግና ከመመሪያ ውጪ ቦታ አስፋፍተው የያዙ ፣ በጥቅም ትስስር በሕገወጥነት ቦታ የያዙ ፣ ከግንባታ ፈቃድ ውጪ ግንባታ ያካሄዱና ለዓመታት አጥረው የያዙ አልሚዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተገለጸ።
በምክትል ከንቲባው በተላለፈ ትዕዛዝም ኦዲት እስኪደረግ ድረስ 30ኛው የመሬት ሊዝ ጨረታ፣ የኢንዱስትሪ አልሚዎች የመሬት ጥያቄ፣ የሠነድ አልባና አግባብ ካለው አካል ሳይፈቅድ በወረራ የተያዙ ቦታዎች መስተንግዶ ፣ መሬት ያልተረከቡ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መስተንግዶ አገልግሎቶች እንዲቆሙ ተደረገ። የአዲስ አበባ ከተማ መሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች አገልግሎት በሙስና የተጨማለቀና የመልካም አስተዳደር ዕጦት የተንሰራፋበት ስለነበር ብዙዎች ለእርምጃው ድጋፋቸውን ቸረው ነበር።
ከወራት ቆይታ በኋላ አንዳንድ ክልሎች በአንበጣ መወረር ሲጀምሩ ክፍት የነበሩ የአዲስ አበባ መሬቶችም በእንጨት ተወረሩ። የአዲስ አበባ ኗሪ ካልሆንክ ጠዋት ብቻውን የነበረን መሬት ማታ ተከቦ ስታገኘው ፣ የአዲስ አበባ መሬት የፌስ ቡክ ገጽ ቢኖረው ኖሮ በየቀኑ “ተከብቤያለሁ” እያለ ፖስት ያደርግ ነበር ልትል ትችላለህ። ወይም ደግሞ ግራ ተጋብተህ “ምን እየተዘራ ነው አጥር የሚበቅለው “ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ማታ ሌጣውን የነበረ ቦታ ላይ ጠዋት ቤተ እምነት ተገንብቶበት ስታይ ፣ ለወራት አሸልበህ ከእንቅልፍህ የነቃህ ሊመስል ይችላል።
አጥር በማጠር ፒ.ኤች.ዲ ዲግሪ ያላቸው 50 ወጣቶች መካከለኛ ገቢ ያለው የአዲስ አበባ ኗሪ በማህበር ተደራጅቶ የሚሰጠውን 70 ካሬ በአስር እጥፍ የሚበልጥ መሬት በአስር ደቂቃ ውስጥ አጥረው “የመሬት ባለቤት” ሲሆኑ ስታይ ፣ “መሬት መግፋት ድሮ ቀረ” ትላለህ። አንድ ክንድ ወደ መንገዱ ገባ ብለው የሚያጥሩ “የዋሃን” በዚህ ዘመን የታሉ ? የዛሬዎቹ መሬት ገፊ ሳይሆን ገፋፊዎች ናቸው። የመሬት ቅርምቱን ህገወጥነትና “ህጋዊ”ነት ለማጣራት ቢቃጣህ የከተማ አስተዳደሩ ግልጽነት የጎደለው ውሽቅሽቅ አሰራር ግድብ ይሆንብሃል።
የአዲስ አበባ ኗሪዎች በየአካባቢያቸው ያስተዋሉትን የመሬት ወረራ በመቃወም በአንዳንድ ሚዲያዎች ድምጻቸውን አሰሙ። ከሳምንት በፊት ሪፖርተር ጋዜጣ “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት አሰጣጥ ኗሪዎችን ግራ እያጋባ ነው” በሚል ርዕስ በሰራው ዜና የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያነሱትን ጥያቄና ያደረባቸውን ሥጋት አስነበበ። ለከተማው መሬት ባንክ ኃላፊም “ኦዲት እስኪደረግ ድረስ ይቁም የተባለው አገልግሎት እንዴት ሊቀጥል ቻለ?” ሲል ጥያቄ አቀረበ። የመሬት ባንክ ኃላፊዋ በሰጡት ምላሽ አስተዳደሩ የመሬት ኦዲት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው ፣ አሁን ግን መስጠት ያቆመውን መሬት በምደባ መስጠት መጀመሩን ገለጹ። ለማንና እንዴት እንደተሰጠ ግን ለጋዜጣው ማብራራት አልፈለጉም።
ከከንቲባ ጽህፈት ቤት በተሰጠ መግለጫ የተዘጋው በር ያለኮሽታ ተከፍቶ ግልጽ ባልሆነ መንገድ መሬት መሰጠት መጀመሩ ከተማ አስተዳደሩ ከድጡ ወደማጡ እየገባ ስለመሆኑ አመላካች ነው። አስተዳደሩ መሬት መስጠት ማቆሙን አስመልክቶ መግለጫ እንደሰጠ ሁሉ መሬት መስጠት መጀመሩን ማሳወቅ ነበረበት። የኦዲቱ ግኝትም ይፋ መደረግ አለበት።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬትና መሬት ነክ ዘርፍ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ኦዲት የተካሄደው ከሰባት ዓመታት በፊት በ2003 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ የተካሄደው ኦዲት በሪል ስቴት ዘርፍ ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር። በኦዲት ግኝቱ መሰረት 105 የሪል ስቴት ኩባንያዎች አግባብ ካለው አካል ሳይፈቀድ ቦታ አስፋፍተው በመያዝ፤ አፓርታማ ለመገንባት በወሰዱት ቦታ ላይ ቪላ ቤቶችን በመስራት፤ ምንም ዓይነት ግንባታ ሳያካሂዱ ለሦስተኛ ወገን በማስተላለፋቸው ጥቂቶች በፍርድ ቤት ሲጠየቁ ሌሎች በአስተዳ ደራዊ ዕርምጃ ብቻ ታልፈዋል። አሁን ተደረገ የተባለው ኦዲትስ ? ዝም ጭጭ ነው።
ለአዲስ አበባ ኗሪዎች ድምጽ ለሆነው ሪፖርተር ጋዜጣ ያለኝን አድናቆት ሳልገልጽ ባልፍ የኦዲቱን ግኝት ካልገለጹት እኩል ተወቃሽ እሆናለሁ። በተለምዶ የመንግስት የሚባሉት የህዝብ ሚዲያዎች ግን ከነበሩበት ፈቀቅ ያሉ አይመስሉም። የከተማውን ህዝብ ብሶትና ጥያቄ ወደ ጎን ብለው ጠዋት ማታ አዲሱን ውህድ ፓርቲ እያላመጡ ከህዝብ ሊያዋህዱት ላይ ታች ይላሉ። ጆሮህ የተለየ የዜና ናፍቆ የቴሌቪዥን ጣቢያህን ስትቀይር “ሳተላይቷ አዲስ አበባን ፎቶ እንድታነሳ ልትታዘዝ ነው” በሚል ዜና ኮርኩረው ያስቁሃል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተደጋጋሚ ውስን የሆነውን የህዝብ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰራ ቢገልጽም እየሆነ ያለው ሌላ ነው። የቀደሙት መሪዎቻችን ለኤምባሲዎች ሰፋፊ መሬቶችን የሰጡት የዛሬዋን አዲስ አበባ መልክ በርቀት ተመልክተው ይመስላል። ዛሬ ከእንጦጦ ቀጥሎ የአዲስ አበባ ሳንባ የሆኑት በእነዚህ ኤምባሲዎች ቅጥር ግቢ ውስጥ የተተከሉ ዛፎች ናቸው። ታላቁ ቤተ መንግስት ፊት ለፊት እየተገነባ ላለው የአዲስ አበባ ወንዞችን ማስዋብ ፕሮጀክት አካል ከከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ያለኗሪዎች በጎ ፍቃድ ጭምር ትላልቅ ዛፎች ከነስራቸው እየተነቀሉ ሲወሰዱ ወደ እነዚህ ኤምባሲዎች ዝር አልተባለም። እንግሊዛዊውና አሜሪካዊው ዛፍ መንቀል አይቻልማ!
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጣሊያን ኤምባሲ “ግማሹን ይዞታችሁን ስጡንና የህዝብ ፓርክ እናድርገው” ሲሉ ያቀረቡት ጥያቄ ለተቀሩት ኤምባሲዎች ከመቅረቡ በፊት የአዲስ አበባ ኗሪ ሰልፍ መውጣት አለበት። ይህችን የመንግስት ቀልድ ጠንቅቀን እናውቃታለን። ኤምባሲዎቹ እሺ ብለው ቦታውን ከለቀቁ፣ ለአመታት ታጥሮ እንዲቀመጥ ተደርጎ ድንገት ለአንዳች ግንባታ ታጭቶ በድንጋይ ይሸፈናል። ዛፎቹና ነፋሻ አየሩም ታሪክ ሆነው ይቀራሉ።
ለዚህ የአድዋ ፓርክ ታሪክ ጥሩ ምሳሌ ነው። አድዋ ፓርክ በቦሌ ክፍለ ከተማ ከአየር ማረፊያው በቅርብ ርቀት ላይ ሞይንኮ ፊት ለፊት የሚገኝ ረግረጋማ ቦታ ነው። 74 ሄክታር የሚሰፋው ይህ ቦታ በከተማዋ ማስተር ፕላን ለአረንጓዴ ስፍራነት የታጨ ነው። ግንባታው ከዛሬ ነገ ይካሄዳል እየተባለ ለአመታት ክፍት ሆኖ ከቆየ በኋላ በከተማዋ ማስተር ፕላን የማይመራው የከተማዋ አስተዳደር በ2012 ለመገንባት ያቀዳቸውን 500 ሺ ቤቶች ከሚገነባባቸው ቦታዎች አንዱ አድዋ ፓርክ መሆኑን አሳውቋል። ይህ ውሳኔ የከተማ አስተዳደሩን የመሬት አጠቃቀም ችግር ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22/2012
የትናየት ፈሩ