በአሁኑ ወቅት 36 ነጥብ 9 የሚሆኑ የዓለማችን ህዝቦች ከኤች አይቪ ኤድስ ጋር ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት መረጃዎች ያመለክታሉ።ከነዚህ መካከልም 21 ነጥብ 7 በመቶ ያህሉ የፀረ ኤች አይቪ ኤድስ መድሃኒት ይጠቀማሉ።1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በየአመቱ አዳዲስ በኤች አይቪ ኤድስ የሚያዙ ናቸው ተብሎ ይገመታል፤ 940 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ከኤች አይቪና ጋር በተያያዘ በሚመጡ በሽታዎች ምክንያት ይሞታሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ2018 የኤች አይቪን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከኤች አይ ቪ ኤድስ ጋር አብረው ይኖራሉ ተብለው ከሚገመቱ 649 ሺ ሰዎች ውስጥ አዋቂዎች 90 ነጥብ 7 ፣ ህፃናት 9 ነጥብ 3፣ ሴቶች 62፣ እና ወንዶች 38 በመቶ ያህሉን ይይዛሉ። በኢትዮጵያም ባለፉት አስርት ዓመታት በኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ በተከናወኑ ጠንካራ ስራዎች በመጡ ለውጦች በመርካትና በመዘናጋት ምክንያት የኤች አይ ቪ ስርጭት ከወረሽኝ ደረጃ ላይ ደርሷል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እ.ኤ.አ በ2018 ባወጣው መረጃ መሰረትም በጋምቤላ 5 ነጥብ 7፣ በሀረሪና ድሬዳዋ 4 ነጥብ 6 እንዲሁም አፋርና አማራ 4 ነጥብ 1 በመቶ በመያዝ እንደየቅደም ተከተላቸው ከፍተኛ የኤች አይቪ ስርጭት የሚታይባቸው ክልሎች መሆናቸውን ጠቁሟል።
በኢትዮጵያ የፀረ ኤች አይቪ ህክምና አገልግሎት ከሚሰጡ የጤና ተቋማት ውስጥ አንዱ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሲሆን፣ በተለይ ደንበኛን ማዕከል ያደረገና ጥራት ላይ መሰረት ያደረገ በኤች አይ ቪ የተያዙ ወገኖች እንክብካቤ እና ህክምና አገልግሎትን በማቅረብ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን ችሏል።የኤች አይ ቪ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ አድልን በመቀነስ ረገድም በርካታ ስራዎችን አከናውኗል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የህፃናት ህክምና ትምህርት ክፍል ጠቅላላ ሃኪም ዶክተር አሜን በቀለ እንደሚሉት ፤የኤች አይቪ ኤድስ ህክምናና እንክብካቤ አገልግሎቱ አርባ የህክምና ባለሙያዎችን በማካተት ላለፉት አስራ ስድስት ዓመታት ሲሰጥ ቆይቷል።አገልግሎቱ ሲጀመር ለሁለት ዓመታት ያህል በክፍያ የነበረ ቢሆንም፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ በነፃ እንዲሰጥ ተደርጓል።
በክሊኒኩ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራና ምክር አገልግሎት፣ ለህክምና ወደክሊኒኩ የሚመጡትን በፍላጎት ላይ የተመሰረተ የኤች አይቪ ኤድስ ምርመራና ምክር አገልግሎት፣ ለኤች አይቪ ተጋላጭ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ የህብረተሰብ ክፍሎችን የምርመራና የምክር አገልግሎት፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የመከላከል አገልግሎቶች፣ የፀረ ኤች አይቪ መድሃኒት፣ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ልየታ፣ የቤተሰብ እቅድና ሌሎችም አገልግሎቶች ይሰጣሉ።
እንደ ዶክተር አሜን ገለፃ፤ ክሊኒኩ በሳምንት 99 ለሚሆኑ ሰዎች በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤች አይቪ ምርመራና ምክር አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ ከያዘው እቅድ በላይ አገልግሎቱን መስጠት ችሏል። ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ለሚገኝና በክሊኒኩ ክትትል ለሚያደርጉ 2ሺ996 ደምበኞች የምክርና የኤች አይ ቪ እንክብካቤ አገልግሎት ለማድረግ ታቅዶ 3ሺ050 የሚሆኑት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ተደርጓል።
ለኤች አይቪ ኤድስ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ለሚታሰቡ የህብረተሰብ ክፍሎችም የኤች አይቪ ኤድስ ምርመራና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፣ የኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ተገኝቶባቸው የትዳር አጋራቸውን ወደ ክሊኒኩ አምጥተው ማስመርመር ላይ ግን አሁንም ክፍተቶች የሚታዩ እንደመሆናቸው በዚህ ላይ በቀጣይ ጠንካራ ስራዎች መስራትን ይጠይቃል።
የኤች አይ ቪ ቫይረስ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍም ካሉት የሆስፒታሉ 121 ደምበኞች ውስጥ 35 ነፍሰ ጡሮችን፣ 86 ወላድ ሴቶችን እና የኤች አይቪ ቫይረስ ተጋላጭ ለሆኑ ጨቅላ ህፃናት የህክምናና እንክብካቤ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።
ከፍተኛ የኤች አይቪ ኤድስ ህክምናና እንክብካቤ ከሚያስገፈልጋቸው የክሊኒኩ 1ሺ 753 አዋቂ ደምበኞች ውስጥ 8ሺ446ቱ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ተደርጓል፤ 4ሺ 797 የሚሆኑት ደግሞ በአሁኑ ወቅት ያሉት የሆስፒታሉ ደምበኞች ናቸው።በሆስፒታሉ የኤች አይቪ ኤድስ ህክምናቸውን ከሚከታተሉ 482 ህፃናት መካከልም 292ቱ አገልግሎቱን ሳያቋርጡ እየተከታተሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም 214 ድምበኞች አሉ።
ዶክተር አሜን እንደሚሉት፤ ኤች አይቪ ኤድስን በሚመለከት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሳምንቱን ሙሉ ደምበኛን ማእከል ያደረገ የህክምናና እንክብካቤ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑ፣ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ቤተሰቦች የምግብና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ፣ ተደራራቢ በሽታዎች ላሉባቸው የኤች አይቪ ህሙማን ተጨማሪ ድጋፍ ማድረጉ፣ ሁሉንም አይነት አገልግሎቶችን በአንድ ስፍራ መስጠቱ፣ በሰውነት ውስጥ የሚገኘውን የኤች አይቪ ቫይረስ ለመቀነስ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ሳምንቱን መሆኑና ሌሎችም ክሊኒኩን ልዩ ያደርገዋል።
በቀጣይም ተቋሙ የኤች አይ ቪ ኤድስ ህክምናና እንክብካቤ አገልግሎትን ይበልጥ ያሰፋል ያሉት ዶክተር አሜን፣ በተለያዩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለኤች አይቪ ኤድስ እንዳይጋለጡ አስቀድሞ እንደሚሰራም ተናግረዋል።ከፍተኛ ጥራት ያለው እንክብካቤን ለመስጠት የሚያስችሉ የጥራት ማሻሻያ ፕሮጀክቶችን መንደፍ የማህበረሰብ ተደራሽነትን ለማሻሻል ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረው፣ የአዋቂዎች ድጋፍ መርሃ ግብርን ለማጎልበትም አበክሮ ይሰራል ይላሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም
አስናቀ ፀጋዬ