አዲስ አበባ፡- ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በአዲስ አበባ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ አውደ ርዕይና ባዛር ከ4 ሚሊየን ብር በላይ የገበያ ትስስር ይፈጠራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቡድን መሪ ወይዘሮ አቦዘነች ነጋሽ ትናንት በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሀገር አቀፍ ዐውደ ርዕዩና ባዛሩ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፣ዛሬ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀሞ ቁጥር አንድ በሚባለው ስፍራ በሚጀመረው አውደ ርዕይና ባዛር 180 ሞዴል ኢንተርፕራይዞች እና 10 አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ይሳተፉበታል፡፡
አውደ ርዕይና ባዛሩ ከ17 ሺ በሚበልጡ ሰዎች ይጎበኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቡድን መሪዋ ጠቅሰው፣ የአምራቾችና የጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ምርቶች ብቻ የሚቀርቡበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ባለፈው ዓመት በሁለተኛው ዙር ተመሳሳይ ባዛር ያልተሳተፉና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንተርፕራይዞች በዚህ አውደ ርዕይና ባዛር ቅድሚያ እንደተሰጣቸውም አስታውቀዋል፡፡
ከተሳታፊዎቹ መካከል 95 ኢንተርፕራይዞች በሴቶች ባለቤትነት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ተናግረው፣ አምስት በአካል ጉዳተኞች ባለቤትነት የሚመሩና መሥፈርቱን የሚያሟሉ ኢንተርፕራይዞችም ቅድሚያ እንዲያገኙ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ አቦዘነች ማብራሪያ፤ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደርን ጨምሮ ከዘጠኝ ክልሎች የተመለመሉ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በሚሳተፉበት በዚህ ዐውደ ርዕይና ባዛር ላይ የአዲስ አበባ ነጋዴ ሴቶች ማኅበርና የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት በድምሩ ስድስት፣ከሴቶች ራስ አገዝ ልማት ድርጅት፣ ከፋሽን ዲዛይን ማኅበር እና ከሴቶች ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ፕሮግራም ከእያንዳንዳቸው አምስት አምስት በአጠቃላይ ከአጋር አካላት 29 ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡በተጨማሪም ከአዲስ አበባና አሮሚያ የቴክኒክና ሙያ ትምህርና ሥልጠና ተቋማት በልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና ፈጠራ ሥራዎች የተመረጡ አራት ኮሌጆች እና የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ልማት ድርጅት የአውደ ርዕይና ባዛሩ ተሳታፊ ናቸው፡፡
የአውደ ርዕይና ባዛሩ ግቦች የጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በጥራትና ስብጥር የደረሱበትን ደረጃ ለተጠቃሚው ለማስተዋወቅ ፣የገበያ ትስስርና ሽያጭ ለማመቻቸት ፣ ከተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች የተሰባሰቡና በልዩ ልዩ ዘርፎች የተሰማሩ ብቁና ተዋዳዳሪ ኢንተርፕራይዞችና አንቀሳቃሾችን በአንድ ማዕከል በማገናኘት በሚፈጠረው ትውውቅና የልምድ ልውውጥ በመካከላቸው ጤናማ የውድድር ስሜት ለመፍጠር እንዲሁም አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና ሥራዎችን ለማቅረብና ማስተዋወቅ ፣ፈጠራንና የፈጠራ ባለሙያዎችን ዕውቅና መሥጠትና ማበረታታት ናቸው ፡፡
ባህላዊና ዘመናዊ የጨርቃ ጨርቅ እና የቆዳ አልባሳትና የምርት ውጤቶች፣ ባህላዊ ዕደ ጥበባት ፣የቅርጻ ቅርጽ ሥራዎች፣ የብረታ ብረትና የእንጨት ሥራና የኢንጅነሪንግ ሥራ ውጤቶች፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች፣ የከተማ ግብርና ውጤቶች፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የፈጠራ ሥራዎች በአውደ ርእይና ባዛሩ ላይ እንደሚቀርቡም አስታውቀዋል ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ