በቅጥር ግቢው በርካታ አውቶቡሶች ቆመዋል:: የተሽከርካሪዎቹ ዝግጁ መሆን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለልምድ ልውውጥ ይሁን ለጉብኝት ከግቢው ለመውጣት የተዘጋጁ አስመስሏል:: በ2009 ዓ.ም ወደ ተመሰረተው ደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ጊቢ ስንዘልቅ ያስተዋልነው ደግሞ ግቢው ‹‹ቅጥር›› ሊያስብል የሚያስችለው የተጠናቀቀ ስራ አለመኖሩን ነው::
በቢሯቸው ያገኘናቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ለታ ተስፋዬ እንደሚሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ሲቀበል የዘንድሮው ለሶስተኛ ጊዜ ነው:: በ2010 ዓ.ም በመደበኛ ሁለት ሺህ 276 ተማሪዎችን እንዲሁም በተከታታይ እና የርቀት ትምህርት ደግሞ 770 ተማሪዎችን ተቀብሏል::ከአጠቃላይ ተማሪዎቹ መካከልም 186ቱ የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ተማሪዎች ናቸው:: በጥቅሉ በሶስቱም ፕሮግራሞች (በቅድመ ምረቃ፣በድህረ ምረቃና በተከታታይ) ሶስት ሺህ 46 ተማሪዎችን በ36 የትምህርት ዘርፎች ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል::
ዘንድሮ አዲስ የገቡት ተማሪዎች አንድ ሺህ 600 አካባቢ ይሆናሉ፤ እነዚህን ተማሪዎች እንደ ሌሎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ የተቀበሏቸው ዝግጅት በማድረግ ነው:: ዩኒቨርሲቲው አዲስ ከመሆኑ የተነሳ የፀጥታ ችግር እንዳያጋጥም ብዙ ዝግጅቶች ከአገር ሽማግሌዎች ጀምሮ የኃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና ከከተማው ወጣቶች ጋር በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል::
ዶክተር ለታ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት የግቢውን ደህንነት የሚያስጠብቀው የፌዴራል ፖሊስ ነው:: ምክንያቱም ተማሪዎቹን ስንቀበል በአደራ ነውና ደህንነታቸውን መጠበቅ ግድ ይለናል::
የፊቱ የግቢው ፖሊስ ብዙም አቅም አልነበረውም:: ከዚያም የተነሳ እኛም በተለያየ ጊዜ ፌዴራል ፖሊስ ወደ ግቢ ገብቶ ፀጥታውን እንዲያስከብርና ውስጥና ውጭ ያለውን ደህንነት እንዲያረጋግጥልን ጠይቀን ነበር:: መንግስትም ጉዳዩን ስላመነበት ወደ 63 የሚሆኑ የፌዴራል ፖሊስ አባላት መድቦልናል:: እነሱ ከመጡ በኋላም ብዙ ለውጦች ታይተዋል›› ይላሉ::
ዩኒቨርሲቲው አሁንም ሌሎች በርካታ ችግሮት አሉበት የሚሉት ዶክተር ለታ፣ ግቢው አጥርም መግቢያ በርም እንደሌለው ነው የሚጠቁሙት:: በዚህም ምክንያት ተማሪው ከግቢው በማንኛውም ሰዓት የመውጣት እድሉ ሰፊ ነው:: ካፒታል በጀት ለዩኒቨርሲቲው መውረድ የነበረበት ቢሆንም ይህ አልሆነም፤ እንደ ወንበር፣ ፍራሽ ያሉትን ጥቃቅን ነገሮችን ሳይቀር ለመግዛት መንግስትን እንጠይቃለን ሲሉ ያብራራሉ::
እንደ ዶክተር ለታ አባባል፤ ዩኒቨርሲቲው ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎች የሉትም ፤ ከተወሰኑ ተሸከርካሪዎች ውጪ ሙሉ ለሙሉ የሚጠቀመው በኪራይ ነው:: የትራንስፖርቱን ችግር በተመለከተ ለሶስት ዓመት በተከታታይ ዩኒቨርሲቲው ጠይቋል፤ እስካሁን መፍትሄ አልተገኘም:: ግቢ ውስጥ የሚታዩት ወደ ዘጠኝ አውቶቡሶች በኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው::
የመምህራን ደመወዝ እየዘገየ መድረሱም ሌላው ችግር መሆኑን ይጠቁማሉ:: በየ15 ቀኑ ሪፖርት እያደረጉ ነው የሚጠይቁት:: የተማሪዎች የመመገቢያ አዳራሽ እንዲሁም የማደሪያ ክፍሎችንም ማስፋት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ::
እንደ ዶክተር ለታ ገለጻ፤ ቤተመጻህፍቱ መፅሐፍት እንደልብ የሉትም:: ግዢ አካባቢ ችግሮች በመኖራቸው መጻህፍት የሚገዛው በለቀማ ነው::
ግልፅ ጨረታ አውጥቶ ለመግዛት መጻህፍቱን በገበያ አያገኙም:: የውሃ ፓምፕ ቢቃጠል ለመግዛት ብዙ ሂደት መከትልን ይጠይቃል:: ሂደቱ እስከ ስድስት ወር ሊፈጅ ይችላል፤ ይህ በጣም ፈታኝ ጉዳይ ሆኗል:: ስለዚህም ካፒታል በጀት ወደ ዩኒቨርሲቲ መውረድ አለበት በሚል ዩኒቨርሲቲው መንግስትን በተደጋጋሚ ጠይቋል፤ ችግሩ ግን አልተፈታም ::
የዩኒቨርሲቲው የጥናት ፣ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ዮሴፍ ሽፈራው ፤ ዩኒቨርሲቲው ሶስት ተልዕኮዎች እንደተሰጡት ይገልጻሉ:: የመጀመሪያው መማር ማስተማር፣ ሁለተኛው ደግሞ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናቶችን ማካሄድ ሲሆን ሶስተኛው የማህበረሰብ አገልግሎት ወይም ህብረተሰቡን ያሳተፈ አገልግሎት መስጠት እንደሆነ ያብራራሉ::
‹‹እኛ መኪና መግዛት አልተፈቀደልንም፤ የምርምር ስራ ደግሞ በቂና ምቹ ትራንስፖርት ያስፈልገዋል::›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ለአብነትም ከደምቢዶሎ አዲስ አበባ አንድ ናሙና ለመውሰድ ደህንነቱ መጠበቅ እንዳለበት ተናግረው፣ ይህ እንዲሆን ለማድረግ ግን የትራንስፖርት ችግር መሆኖሩን ያመለክታሉ::
ለአካባቢው ህብረተሰብ የሚጠቅም ምርምርና ቴክኖሎጂ ማፍለቅ የሚቻለው በአንኳርነት ሊሟሉ የሚችሉ ጉዳዮች ሲሟሉ ነው የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ መንግስት እዚህ ላይ ትኩረት ቢያደርግ የተሻለ መሆኑን ይናገራሉ:: በዩኒቨርሲቲው በኩል የማህበረሰብ አገልግሎቱን በተነቃቃ መልኩ ለመስራትም ዝግጁ መሆናቸውን ያስረዳሉ::
ዩኒቨርሲቲው አሉብኝ ያላቸውን ችግሮች በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የ11ዱ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ግርማ መኮንን ፤ እርሳቸው ወደስራ አስኪያጅነቱ ከመጡ ቀናትን ብቻ
እንዳስቆጠሩ ጠቅሰው፣ ዩኒቨርሲቲዎች እያቀረቡ ያሉት የመሰረተ ልማት ችግር ጉዳይ እየተጣራ መሆኑን ይገልጻሉ::
‹‹በአሁኑ ወቅት አንዱ ለሰላም መደፍረስ በምክንያትነት የተቀመጠው የዩኒቨርሲቲዎች አጥር አለመኖር መሆኑ በግምገማ ተነስቷል:: ይህን ችግር ለመፍታት በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ምን እየተሰራ ነው ቢባል በአሁኑ ወቅት ለቦታው አዲስ ከመሆኔ ጋር ተያይዞ እርገጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም::›› ሲሉ ገልፀው፤ በቅርበት የሚያውቋቸው የሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችን የውሃ ችግር ለመንግስት እንደቀረበ ተናግረዋል:: ማቅረባቸውንና እና ውሳኔም እንደሚሰጥበት እምነታቸው መሆኑን ያብራራሉ:: የደምቢቦሎ ግን እርሳቸው እስከሚያውቁት ድረስ ጥያቄው አልቀረበላቸውም::
ዶክተር ግርማ እንደሚናገሩት፤ በጀት ወደዩኒቨርሲቲዎቹ የማውረዱ ነገር ችግር የለውም፤ መንግስት በቀጣይ ርምጃ እየወሰደ ወደዚያ እንዲሄድ ያደርጋል:: ይሁንና የበጀት ወደ ዩኒቨርሲቲዎች መውረድ አለመውረድ ያን ያህል የመሰረተ ልማት ግንባታውን የሚጓትት አይሆንም::
በሚኒስቴሩ የምርምርና አካዳሚ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ኤባ ሚጃና በበኩላቸው፤ ተማሪዎች የፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም ኮማንድ ፖስት አያስፈልገንም፤ ሰላማችንን እኛው መጠበቅ እንችላለን ለሚሉት ምላሽ ሲሰጡ እንዳስረዱት፤ በእርግጥም ሰላም እስካለ ድረስ ሌላ ተጨማሪ ጥበቃ በህጉም ቢሆን አያስፈልግም:: ብለዋል::
አሁን በየዩኒቨርሲቲው ሰላም ስለደፈረሰና ከዚህም አልፎ የሰው ህይወት ስለጠፋ ጭምር ነው በመንግስት ተወስኖ ዩኒቨርሲቲዎች በሌላ ሀይል እንዲጠበቁ እየተደረገ ያለው ይላሉ:: ሰላሙ ወደነበረበት የሚመለስ ከሆነ ጥበቃውም እስከዘላለም የሚቀጥል እንዳልሆነና እንደሚነሳም አስገንዝበዋል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2012
አስቴር ኤልያስ