አደጉ የሚባሉ አገራት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እጅግ ከፍተኛ ወጪን በመመደብ መስኩን ለመምራት በፉክክር ላይ ይገኛሉ። እርግጥ ነው ታዳጊ አገራት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምጥቀት ተሳታፊነት ላይ ደካማ ቢሆኑም ወቅታዊ ሁኔታዎች ግን ወደ ዘርፉ እንዲያተኩሩ እያስገደዳቸው ይገኛል። ታዳጊ አገራት ባላቸው አቅም የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ከዘመኑ ጋር ለመራመድ የግዴታ ያህል ሆኖባቸዋል። ዘመኑ መጓዣው ቴክኖሎጂ፤ መራመጃው ሳይንስ ነውና መፃይ ዘመንን የተሻለ ለማድረግ በዘር ላይ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይገባል።
አሁን በደረስንበት ዘመን በየትኛውም ዘርፍ አገራዊ አቅምን ለማጎልበት ዋንኛ መሳሪያ ሳይንስ መሆኑ አይካድም። አንዳንድ አገራት ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማጠንከሪያ ዋንኛ የገቢ ምንጫቸውን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ አድርገዋል። ቀድመው በዚህ ዘመን ሳይንስ የማይተካ ሚና እንዳለው ተረድተዋልና ሳይንስና ቴክኖሎጂን በማሳደግና ከቱርፋቱ በመጠቀም የኢኮኖሚ አቅማቸውን በማፈርጠም ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ በሰጠችው ልዩ ትኩረት የተለያዩ እምርታዎች በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች። ይሁንና በሳይንስና ቴክኖሎጂው መስክ ቀዳሚ ከሆኑ አገራት ጋር ስትነፃፀር እጅግ በራቀ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ይህ የሚያሳየው በቴክኖሎጂ አቅም ዳብሮና ተሻሽሎ ውጤት ማስመዝገብ እንዲቻል እንደ አገር ብዙ ስራዎች ይጠበቃል።
በኢትዮጵያም የሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ መረጃና የኢኖቬሽን አጠቃላይ እንቅስቃሴና በዘርፉ ያሉ ጥናቶችና ምርምሮች አንዱ ተግባሩ የሆነው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሀገሪቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ወጪ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ባጠናው ጥናት ለይቷል።
በጥናቱ ውጤትም የቴክኖሎጂ አቅምን የማሳደግ ስራ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀቶችና ቁሶች አጠቃቀም ላይ መሰረት ያደረገ ነበር። በመሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት የአገሪቱን አቅም ባገናዘበ መልኩ ከጊዜ ወደ ጌዜ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በማሟላትና አገራዊ አገልግሎቱን በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ከፍተኛ ወጪዎችን በማውጣት ዘርፉን በማዘመን ላይ መሆኑን አመላክቷል።
ጥናቱ 80 የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይና 41 ከፍተኛ የመንግስት ትምህርት ተቋማት ላይ ያተኮረ ሲሆን በአጠቃላይ 121 የመንግስት ተቋማት ላይ ትኩረት አድርጓል። መንግስት በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ የመንግስት ተቋማት ላይ የሚያወጣቸውን ውጪዎች መሰረት ያደረገው ጥናቱ ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ነክ የሆኑ ትምህርታዊ ጥናትና ምርምሮች እንዲሁም አገልግሎቶች ላይ የሚወጣው አገራዊ ወጪ የተመለከተ ነው።
ኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም ወይም በፈረንጆች አቆጣጠር 2016/17 ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እስከ አምስት ቢሊዮን የሚደርስ ወጪ አውጥታለች። ውጤቱም ከቀደሙ ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የሳይንስና ቴክኖሎጂ ወጪዎች እያደገ ቢመጣም ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ግን አሁንም አነስተኛ ነው። አገራት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገታቸው ለውጥ የሚለካው ለጉዳዩ ከሚሰጡት ትኩረትና እሱን ተከትሎ አጠቃላይ ሁኔታዎች ምቹ በማድረግ ለተግባራቱም አስፈላጊውን በጀት በመመደብ ከዚያም የሚያስገኘውን ውጤት በመለካት ይሆናል።
ይህ ጥናት ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ በሁለተኛነት ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠና መሆኑ የተገለፀ ሲሆን መንግስት በዘርፉ ያወጣው ወጪ በተመለከተ ያስቃኘና አሁን ላይ በአገሪቱ ያለውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንቅስቃሴዎች ያለበትን ደረጃ ለመለካት ያስቻለ ነው። ጥናቱ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ አጠቃላይ አገልግሎትና ጥናትና ምርምሮች በዘርፉ ላይ ያሉ ባለሙያዎች ሁሉ የሚያቅፍ ወጪ ነው። ይህ ጥናት ያመላከታቸው ዋንኛ ጉዳዮች መሰረት በማድረግ በቀጣይ ለዘርፉ የሚመደበው በጀት ምን መልክ መያዝ እንዳለበትና ምን ላይ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ መነሻ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
አቶ ቃል ኪዳን ተሾመ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመረጃ አደረጃጀትና ዕውቀት አስተዳደር ዳይሬክተር፤ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አገራዊ ወጪ ማውቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይገልፃሉ። ስለዚህም አገራት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ወጪያቸውን ለይተውና የሚያወጡትን ወጪ ተግባራዊነቱን ለመገምገም ያስችላቸው ዘንድ የዘርፉን አጠቃላይ ወጪ በየጊዜው ያስጠናሉ።
አገሪቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ የምታወጣቸው ወጪዎች በጥናትነት መልክ መዳሰስና ያሉትን ገፅታ ማወቁ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያስገኘና ፋይዳውም የጎላ መሆኑን ያስረዳሉ። ዳይሬክተሩ፤ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አገራዊ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ዋነኛ መነሻና የቴክኖሎጂ አጠቃላይ አቅምን ለመለካት እንደሚያስችልም ይናገራሉ።
መንግስታዊ ተቋማት በሳይንስና ቴክኖሎጂው ላይ ያወጡት ወጪ በዓይነት ሲመላከት ለውስጥ አገልግሎት የወጪውን 86 በመቶ ሲጠቀሙ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን ለሰሩት የዘርፉ ተግባር 12 ነጥብ ሶስት በመቶ የሚሆነውን ወጪ አውጥተዋል። የመንግስት ተቋማት ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለማስፋፋትና የተሻለ አገልግሎት ማቅረብ እንዲያስችላቸው ተጠቅመውበታል።
አገራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አጠቃላይ ወጪና ተቋማት እየተጠቀሙ ያሉበት ሁኔታን የሚያመላክተው ጥናት የዘርፉ መነቃቃት መልካም ቢሆንም ከሳይንስና ቴክኖሎጂ እንደ አገር ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ለማረጋገጥ ጠንካራ ስራ አስፈላጊ መሆኑ አመላካች ነውና ትኩረት ይገባዋል እንላለን። አበቃን ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2012
ተገኝ ብሩ