አንድ ገበሬ ናቸው። በዘመናቸው ሮጠው ያሻቸውን አድረገዋል፤ አንሰተው ጥለው እንዳላለፉ ሁሉ ዕድሜ ገሰገሰና ጉልበታቸው ከዳቸው። ጊዜ ሲገፋ አቅማቸው ሲደክም እጅ ሰጡ። በወጣትነታቸው ሌላውን የጦሩት ያህል ተረኛ መሆን ግድ አላቸው። ግን ደግሞ እድለኛ አልነበሩምና ‹‹ጧሪዬ ይሆናል›› ብለው ተስፋ የጣሉበት አንድያ ልጃቸው እስር ቤት ይገባል። ለዚያው ለገበሬ ወሳኝ በሆነው የአዝመራ ወቅት። ይህ ወቅት ገበሬው አቅሙን አሟጦ የሚጠቀምበት ነውና ሽማግሌው መሬታቸው ጦሙ ማደሩን ሲረዱ ሀሳብ ገባቸው።
እናም ለልጃቸው ‹‹ልጄ አቅሜ እንደደከመ ጉልበቴ እንደዛለ ታውቃለህ። ዘንድሮ አንተም የለህ መሬቱ ፆሙን ማደሩ ነው። የአንተ መታሰርና ከእኔ መለየትን ሳስብ መጪው ጊዜ አስጨንቆኛል። በርሃብ መሞቴ ነው። መሬቱን ማን ቆፍሮና አለስልሶ አዝመራውን ይዘራልኛል? ችግር ውስጥ ወድቄብሃለሁ።›› በማለት ወደ እስር ቤት ደብዳቤ ላኩ።
ልጃቸው የአባቱን መልዕክት አንብቦ ምላሽ ፃፈ። ‹‹አባቴ ዘንድሮ ሌላ ሰው የሚያግዝህ ቢኖር እንኳን የአዝመራውን ቦታ እንዳታስቆፍረው። አይዞህ! አምላክ ሌላ መፍትሄ ያቀርብልናል። የገደልኳቸውን ሰዎች የቀበርኩት እዚያ ቦታ ላይ ስለሆነ በፍፁም እንዳይቆፈር ሌላ ሰው ከቆፈረው ማስረጃ ይገኝብኛል፤ አደራ›› ብሎ መልዕክቱን ይመልሳል።
ይህ መልዕክት ከተላከ ከጥቂት ቀናት በኋላ አባት ለልጃቸው በድጋሚ ደብዳቤ ላኩ። ‹‹ልጄ በጣም አመሰግንሃለሁ፤ ባለፈው የላከው ደብዳቤ እኔ ዘንድ ከመድረሱ በፊት ፖሊሶች አይተው ነበርና ማሳውን ሲቆፍሩ ከረሙ። ምንም አይነት ሬሳ ግን አላገኙም፤ ይህንን ያደረከው ቁፋሮው በዘዴ በእነሱ እንዲፈፀም አስበህ መሆኑን ተረድቻለሁ። እናም እነሱ በቆፈሩት ማሳ ላይ አዝመራዬን ዘርቼ እፎይ ብያለሁ። ልጄ እዚያም ሆነህ እገዛህ ስላልተለየኝ እጅጉን አመሰግናለሁ›› አሉት።
እናም ምን ለማለት ነው ወዳጆቼ፤ የቀረበንን መጥፎ አጋጣሚ በመላ ብናልፈው አጋጣሚውን በመልካም ብንጠቀመው መልካም ነው። ‹‹የተወረወረብህን ጠጠር ለቅመህ መልሰህ ከመወርወር ይልቅ መሸጋገሪያ ድልድይ ስራበት›› የሚል ምክር ተደጋግሞ ይደመጣል። ልክ ነው። ስለማን ብለን መጥፎ አጋጣሚዎችን መጥፎነታቸው ላይ ብቻ በማተኮር እንቆዝማለን? ይልቅ መጥፎ ገጠመኙን እራሱን መግጠም የተሻለ ነው።
በየዕለት እንቅስቃሴያችን የገጠመን አስቸጋሪ ጉዳይ ወደ ጥሩ አጋጣሚና ጥቅም የመለወጥ ልማዳችን ምን ያህል ይሆን? ያሰብነው አልሰምር፤ ያቀድነው አልሳካ ቢለን ፈፅሞ ወደ ተስፋ መቁረጥ መገባት የለበትም። ስንት ነገር ከፊታችን እያለ በአንድ ሙከራ መሳካት አለመሳካት እጅ ከተሰጠማ መነሻችን ላይ ለጉዳዩ የሰጠነው ቦታ ትልቅ መሆኑ እንጂ ገና ስናስበው ላይሳካ እንደሚችል አላስተዋልንም ማለት ነው።
በነገራች ላይ ሙከራ የሚሳካው አልፎ አልፎ እንጂ ሁሌም አይደለም፤ የስኬታማ ሰዎች ገጠመኝና የህይወት ውጣ ውረድ ብንመረምር መንገዱ አልጋ ባልጋ ሆኖለት ያለፈ አይገጥማችሁም። በጉዛችን ውስጥ ወደኛ የሚቀርቡን መጥፎ አጋጣሚዎች ወደ መልካም ገጠመኝ መለወጥ እርግጥ የሚያወሩትን ያህል ቀላል አይደለም። ነገር ግን አንዴ ያ መጥፎ አጋጣሚ ወደኛ መጥቷልና ፈጥሮብን የሚያልፈው ጉዳት ከመቀበል ይልቅ ወደ በጎ አጋጣሚ መለወጡ ግድ ይለናል።
ብዙ ጊዜ የበጎ ነገሮች አልያም የግኝቶች መነሻ አስቸጋሪ ወይም መጥቶ አጋጣሚዎች ናቸው። እንደውም በችግር ምክንያት የተፈጠሩ መፍትሄዎች የሰው ልጅ ኑሮ ሲያቀሉ በተደጋጋሚ አስተውለናል። ዛሬ ላይ አለም ጭለማን የረታበት ብርሃን ወይም መብራትን የፈጠረው ቶማስ ኤድሰን እጅጉን ጭለማ ይፈራ እንደነበር እናውቅ ይሆን? ጭለማን መፍራት ደግሞ ጭለማን ለመግፈፍ እንዲማስን አደረገውና መፍትሄ ወለደለት።
እናም መከራ መፍትሄን ይወልዳል፤ ፍርሃት ማምለጫን ያበጃል። ድህነትን አጥብቆ የሚፈራ ሰው ከድህነት ለመውጣት ብርቱ ጥረት ያደርጋል። እራሱን ለመለወጥ ለሊት እና ቀን ሲማስን እራሱን የተሻለ ቦታ ላይ ለማድረስ ሁሌም ሲፍጨረጨር የተሻለ ቦታ ላይ መገኘቱ አይቀሬ ነው። እየንዳንዱ መጥፎ ገጠመኞቻችንን ወደ እድል እና መልካም አጋጣሚ መቀየር መቻላችን ጥቅሙ ያየለ የሚያደርገው ለዚሁ ነው።
ውዶቼ አንድ ነገር ካስተዋልን ብዙ ጊዜ የኛ ስኬት መቃረቢያ የሚሆኑ ጉዳዮች ትኩረት የሰጠንባቸውና እንዳይደናቀፉብን ጠንቃቃ የሆንባቸው ጉዳዮች ናቸው። ስለ ጉዳይ አስልተን መመርምር ጉዳዩን ጠንቅቀን ማወቅና በዚያ ዙሪያ ያለንን ሁኔታ ምቹ ማድረግ እንዳለብን ፍላጎታችን ያስገድደናል። የጀመርነውን ጉዳይ ከዳር ለማድረስ መውተርተራችን ፍሬ ያፈራል። ነገር ግን ስኬትን አልመን የጀመርነው ጉዳይ ዋነኛ እና ወሳኝ ነው። ያመንበትን ሳይሳካልን ቢቀር አለመሳካቱን መነሻ አድርገን ያልተሳካበት ምክንያት መመርመር ተገቢ መሆኑ አያጠያይቅም።
ያ ጉዳይ የኛ የመጨረሻ አማራጭ አድርገን መውሰዳችን የመጀመሪያው ስህተት ነው። አለም በብዙ ገጠመኞች የተሞላች ለሰው ልጆች ሰፊ ዕድልን ይዛ የቀረበች ሆና ሳለ የኛ ምልከታ ውስን ይሆንና አንድ መንገድ ላይ ብቻ ችክ እንላለን። ያ መንገድ ደግሞ የሚጓዙበት ብዙዎች ናቸውና የተጣበበ ሆኖ ይጠብቀናል። አስፍቶ መመልከትና ሌሎች አማራጮችን ማየቱ የኛ ልምድ ሊሆን ይገባል። በጥረታችን ውስጥ የሚገጥመንን ጋሬጣ መመንጠር የሚያስችል አቅም ይዞ መገኘትና መፋለም፤ ይህን የማድረግ አቅምን ከፈጠርን ሌላ ዘዴ መዘየድና ችግሩን እራሱ በመፍትሄነት መጠቀሙ ልምድ ብናደርግ መንገዶች ሁሉ ይቀናሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2012
ተገኝ ብሩ