ባሳለፍነው ሳምንት በኪነ ጥበብ አምዳችን ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ፊልም ከየት ተነስቶ የት ደረሰ›› በሚለው ሀሳብ ዙሪያ ጥቂት ጉዳዮችን አንስተናል። ይህን ጉዳይ አንስተን የተወያየነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና የሲኒማቶግራፊ ባለሙያ የሆኑትን አቶ አበበ ቀፀላን እንግዳችን በማድረግ ነበር። በዚህ የሙያ ዘርፍ በሰነድም ሆነ በሌላ አግባብ ትክክለኛውን ታሪካዊ እውነት አስረድተዋል።
ከእንግዳችን ጋር በነበረን ቆይታ በተለይ አሁን አሁን የሚሰሩ ፊልሞች ከጥቂቶቹ በስተቀር ዓለም አቀፍ ይዘት የጎደላቸውና ለውድድር ብቁ ያልሆኑ መሆናቸውን ነግረውናል። ፊልሞቹ የይዘት እና የጥራት ችግር እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል። በሙያው ላይ በቂ ግንዛቤ የሌለው ማንኛውም ሰው በፊልም ውስጥ እየገባ መሆኑ እንደሚያሳስባቸውም ሳያጫውቱን አላለፉም።
‹‹ፊልም ለመስራትና የሚፈለገውን መልዕክት ለማስተላለፍ የግዴታ ተሰጦና እውቀቱ ያስፈልጋል›› የሚል ድምዳሜ አስቀምጠዋል። ይህ እንዲሆን የራስ ጥረትን ጨምሮ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ያስፈልጋል የሚል ምክረ ሀሳብም የሲኒማቶግራፈር አበበ ቀፀላ ሰንዝረዋል።
በተለይም ከእንግዳችን ጋር በነበረን ቆይታ ከላይ የተነሱትን ችግሮች ለመቅረፍ የትምህርት ቤቶችን አቅም ማሳደግና ቀድሞ የነበረውን የፊልም ኮርፖሬሽን መልሶ ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል። ይህ ከሆነ ያለውም ምስቅልቅልና ደርዝ የሌለው ኢንዱስትሪ ከማስተካከል ባለፈ የኢትዮጵያን ሲኒማ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማስቻል ቀላል መሆኑን ተነጋግረናል።
በዚህኛው ሳምንት ደግሞ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር የኢትዮጵያን ሲኒማ ወደፊት ለማሳደግ ምን እየታሰበ እንደሆነ ምላሽ አግኝተናል። ይህንን ቃለ ምልልስ ለማድረግ ፍቃደኝነታቸውን ያሳዩንን የአዲስ አበባ አስተዳደር የመንግስት ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ ተሾመ በቅድሚያ ልናመሰግናቸው ወደናል።
አዲስ ዘመን፦ በኢትዮጵያ ሲኒማ እድገት ዙሪያ ያተኮረ የአራት ቀን የውይይት መድረክ ሰሞኑን ተዘጋጅቶ ነበር። ይህን መድረክ ማዘጋጀት ለምን አስፈለገ? ይዘቱስ ምን ይመስላል?
አቶ አስናቀ ፡ – ይህንን ውይይት ለማዘጋጀት ያቀድንበት መሰረታዊ ምክንያት የኢትዮጵያ የሲኒማ ዕድገት ያለበትን ደረጃ ለይቶ ለማወቅና ወደፊት ምን አይነት መልክ ሊኖረው ይገባል የሚለውን ለመወሰን እንዲቻል ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ነው። በዚህም በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች፣ ፕሮዲዩሰሮችን ጨምሮ በተዘዋዋሪም ሆነ በከፊል ጥበብ ጋር ግንኙነት ካላቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መመካከሩ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
በምክክር መድረኩ ላይ ከዚህ ቀደም ሲሰራባቸው ከነበሩ እና ጠንካራ የሆኑ ሂደቶች እንደተጠበቁ እያለ ሌሎች ተጨባጭ ለውጥ አምጪ ጉዳዮች ስለሚኖሩ፤ እነርሱን እንደ ግብዓት በመጠቀም ኢንዱስትሪው እንዲያድግ በሚያስችል መልኩ ለመንቀሳቀስ እንደሚረዳ ታምኖበታል። ይህንንም መነሻ በማድረግ ከባለድርሻ አካላቱ ጋር ምክክር ተደርጓል።
የመንግስት ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር በአዋጅ የተሰጠ ስልጣን ስላለ ፊልምና ፊልም ነክ ነገሮችን እያሳደጉ መምጣት አስፈላጊ ነው። ይህ ሆኖ እያለ እስካሁን በመንግስት ተቋም ደረጃ ፌስቲቫል ተዘጋጅቶ አያውቅም። በመሆኑም አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ማዘጋጀት አለብን ብለን ወስነናል። ነገር ግን በቀጥታ ወደ ተግባር ከምንገባ በመጀመሪያ ‹‹በዘርፉ ያለው ተግዳሮት ምንድን ነው›› በሚል መድረኮችን ፈጥረን ውይይት ለማድረግ ፈልገናል። ይህ ደግሞ ችግሮችን ነቅሰን አውጥተን ለመለየት ያስችለናል። የመጀመሪያ መድረክ ከፈጠርን በኋላ በውይይቱ በርካታ ሃሳቦች ተነስተዋል።
ከእነዚህ ሃሳቦች ተነስተን ለተከታታይ አራት ቀናት ተወያይተናል። የኢትዮጵያ የሲኒማ ዕድገት ምን ይመስላል በሚል በአራቱ ቀን ነባር ፊልሞችን እያቀረብን ዶክመንቶችን እያየን ፣የፓናል ውይይቶች እየተደረጉ ነው ምክክሩ የተካሄደው።
አዲስ ዘመን፦ የመጀመሪያውን ፌስቲቫል መቼ ለማድረግ አሰባችሁ?
አቶ አስናቀ ፦ በቀጣይ ዓመት መስከረም ላይ ለማድረግ አስበናል። ለሚካሄደው የፊልም ፌስቲቫል የተደራጀ እና የተቀናጀ ስራ ለመስራት ታቅዷል። በተቻለ መጠን የምንሰራቸው ስራዎች እንከኖችንም ሆነ ችግሮች የቀነሰ ውጤታማ የሆነ ስራ ለመስራት ነው። ይህ መድረክ የተዘጋጀው ሌላው አዳዲስ ሲኒማ ቤቶች ማስፋፋት ተገቢ መሆኑን ለመወያየት እና ትኩረትም እንዲሰጠው ለማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ሲኒማ ቤቶችን ከማገዝ አንፃር ምን አስባችኋል?
አቶ አስናቀ፣ የመንግስትም ሆነ የግለሰብ ሲኒማ ቤቶችን በዚህ ማገዝ ይኖርብናል። የነባር ሲኒማ ቤቶችም ሲኒማ ኢትዮጵያ ፣ሲኒማ አምፒር ፣ሲኒማ አምባሳደር አሁን ያለበት ቁመና በጣም የተዳከመ ነው። ረጅም ዕድሜ የፈጁ ሲኒማ ቤቶች ናቸው ፤ለአገር ግንባታ ከአደረጉት አስተዋጽኦ አንጻር አሁን ያላቸው ገጽታ በጣም የተዳከመ ነው። ስለዚህም በአዲስ እንዲሁም ክላሲክ በሆነ መንገድ መታደስ አለበት ብለን ወስደናል ፤ ይህንን ዕድሳት ለማድረግ መንግስትም ሆነ ይመለከተኛል የሚሉ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የታሰበ ሲሆን ዕድሳቱ ሲደረግ ሲኒማ ቤቶቹ የቀድሞውን ይዘታቸው እንዳይለቁ ይደረጋል ። ከዚህም በተጨማሪ አሁን ላላው የኢንዱስትሪ ግንባታ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ የሚያደርግበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ታስቧል።
አዲስ ዘመን፦ ቀደም ባሉት ዘመናት የተሰሩ የኢትዮጵያ ፊልሞች ጥንካሬና ክፍተታቸው ምን ይመስላል?
አቶ አስናቀ፡- በአራቱ ቀናት መድረክ ላይ በተጨባጭ ከቀደሙት ውስጥ ያሳየናቸው ፊልሞች አስቴር፣ ሂሩት አቧቷ ማን ነው፣ ጉማ ሲሆኑ በቅርብ ከተሰሩት ደግሞ ቁራኛዬ አለበት። ከፊልሞቹ መረዳት እንደሚቻለው ከዚህ በፊት የነበረው ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ነበር። በተቋም ደረጃም ‹‹የፊልም ኮርፖሬሸን›› ከዚያ በፊትም ደግሞ ‹‹የፊልም ማዳበሪያና መቆጣጠሪያ ማእከል›› በሚል ደረጃ ተዋቅሮ ሲሰራ የነበረ ተቋም ነው። ይህ ተቋም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ጠንካራ ነበር። ለገጽታ ግንባታ የሚሰሩ ዶክመንተሪ ፊልሞች ነበሩ። አገራዊ ፊልሞችም በሙሉ የአገር ግንባታ ላይ አሻራ ለማሳረፍ እንዲሁም የፊልም ዕድገቱንም ጭምር ለማሳደግ እንቅስቃሴ የተደረገበት መሆኑን በጥቅሉ ማወቅ ችለናል።
ነገር ግን አሁን ባላው ተጨባጭ ሁኔታ የቀድሞ አሰራር ፈርሶ የሲኒማ ቤቶች አስተዳዳር በሚል ነው የተዋቀረው። የቀድሞ አሰራሩ የፈረሰበትን ምክንያት የሚያውቀው ያፈረሰው አካል ነው። እንደ እኔ ግን እስካሁን ቢቀጥል ኖሮ ለፊልም ኢንዱስትሪው ምን ያህል አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል መገመት አያዳግትም ነበር። በዚያ ዘመን የነበሩ ፊልሞች ሲታዩ ‹‹በዘመኑ ፊልሞች እንደዚህ ይሰሩ ነበር›› በማለት በአድናቆት እንዲታሰብ የሚያደርግ ነው። በተለይ በአራቱ ቀን መድረክ የታዩት የቀድሞ ፊልሞች በዘርፉ የተሰማሩ የጥበብ ባለሙያዎች ቁጭት እንዲያድርባቸው አድርጓል።
ባለሙያው የቀድሞውን በማሰብ የተደነቀበትን ሁኔታ ማየት ችለናል። በወቅቱ በነበረው ፍጥነት እና መንገድ ቢኬድ ኖሮ አሁን በዓለም ላይ ጥሩ ተፎካካሪ እንሆን ነበር። ከአፍሪካ ግንባር ቀደም በመሆን ደረጃ የፊልሙን አቅም ከፍ ከማድረግ አንጻር ትልቅ አስተዋፆ ይኖረዋል።
እንደ አገር በዚያው መንገድ ቀጥለን ቢሆን ኖሮ አሁን በአፍሪካ ደረጃ የፊልም ማዕከላት ተደርገው የሚጠሩ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ትሆን ነበር ። ነገር ግን መሀል ላይ የተፈጠረው ዘርፉን በተገቢው መንገድ አለመምራትና እንቅስቃሴ አለማድረጉ ሊደገፍ የሚገባው ሙያ በተገቢው መንገድ እንዳልተደገፈ የሚያሳይ ነው። ስለዚህም ይህንን ማረም ይጠይቃል። ይህን በተመለከተ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል። የሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ድርጅትም ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በተለይ በቀጥታ ከሚያገባቸው የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ከአንጋፋ አርቲስቶችና በቀደምትነት ይህንን ስራ ሲያንቀሳሱ ከነበሩ መሪ ተዋናዮች ጋር በቁርኝት በመሆን ስራዎችን መስራት ተጀምሯል። በእርግጠኝነት አሁን በያዝነው መንገድ መቀጠል ከቻልን የነበሩ ክፍተቶች ሙሉ በሙሉ ማጥፋት እንኳ ቢቸግር፤ በተወሰነ መልኩ ለመቀነስ እንችላለን። እዚህም እዚያም የፈረሱ ስርዓቶችን አስተካክለን መሰራት የሚገባቸውን ተግባራት ለይተናል።
አዲስ ዘመን፦ አሁን በሲኒማ ቤቶች የሚታዩ ፊልሞች ችግራቸው ምንድን ነው?
አቶ አስናቀ፣ በተጨባጭ መናገር የሚቻለው በሲኒማው ላይ አሁንም ብዙ በጎ ነገሮች እንዳሉ ነው። እንደ ችግር የሚታው የተጣለውን መሰረት አለማስቀጠል ነው። አሁን ግን ከተማ አስተዳደሩም ሆነ የሲኒማ ቤቶች አስተዳደር እንደ መንግስትም ይህንን ዘርፍ ለማገዝ መወሰናቸው በኢኮኖሚው ሆነ በማህበራዊ ዘርፍ አስተዋፆኦው ከፍተኛ ነው።
ዘርፉ የኢኮኖሚ ማነቆም አለበት። ዕድገት እንዲያመጣ እንዲሁም ማህበረሰባዊ የሆነውን እሴቶቻችን ላይ ጠንካራ አስተዋፆ እንዲያኖር መደገፍ አለበት። አሁንም ቢሆን ዘርፉ ሳይታገዝ ከዚህም ከዚያም የሚሰሩ ፊልሞች ከእነ ችግራቸው ውጤት እያሳዩ ነው። በተገቢው መንገድ ዘርፉን ሳንደግፍ እንከኖቹን እየነቀሱ ማውጣትም ተገቢ አይደለም። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በያዝነው ልክ ፈጥነን ለሌሎች ዓለማትም አገሮችም አርዓያ የሚሆን ስራ መስራት ይቻላል። ክፍተቶቹ ተብለው አንድ ሁለት ሶስት ተብሎ በፓናል ውይይቶቹ ተነስቷል። የመፍትሄ ሀሳብም ቀርቧል።
ከተነሱት ጠንካራና ደካማ ጉዳዮች ባሻገር ወደ ፊት ምን መደረግ አለበት የሚለው ዋና ተግባራችን ሊሆን ይገባል። በነበረው ውይይት የፊልሙ እንቅስቃሴ ጥሩ እንደነበር ማየት ችለናል። አሁንም ቢሆን በግለሰብ፣ በቡድን፣በማህበር እዚያም እዚህም እየተሰሩ ያሉ ፊልሞች አሉ። እነዚህን ድምር ውጤቶች ሰብስቦ በቀጣይ እንዴት ማጠናከር ይኖርብናል የሚለው የኛ የቤት ስራ ነው። እርሱ ላይ ነው ትኩረት ማድረግ ያለብን። በቀጣይ በዘርፉ የሚለፉትን ግለሰቦች ይሁኑ ማህበራት ዕውቅና መስጠት መሸለም ያስፈልጋል። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመደገፍ ለሚፈለገው ነገር ማዋል አለብን። ስለዚህም በመጪው ዓመት መስከረም ላይ የምናደርገው ፌስቲቫልም አንድ እርምጃ ነው ብለን እናስባለን።
እንደሚታወቀው በግለሰቦች ደረጃ ፌስቲቫሎች እየተካሄዱ ነው። እዚያ ላይ መጨመር መደገፍ ያለብንን አድርገን ዘርፉን ማሳደግ አለብን። ይህ ማለት ግን ግለሰቦች እየሰሩ ያሉት ነጥቆ መስራት ሳይሆን ስራቸውን በተሻለ መንገድ እንዲሰሩ ነው የምናደርገው። የሚጎሉ ነገሮች በመጨመር ደረጃዎችን በማውጣት በጋራ የተቀናጀ ስራ መስራት ነው ያሰብነው። እዚህ ላይ ዋናው ቁልፍ ጉዳይ ዘርፉን ማሳደግ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ግባችሁ ምንድነው?
አቶ አስናቀ፣ ሲኒማው እዚህ ይደርሳል ብለን ያስቀመጥነው ግብ አለን። በአጭር ጊዜ እናሳካዋለን ያልነው ተመሳሳይ መድረኮችን ማዘጋጀት ነው። የነበርንበትን ሁኔታ በማንሳት በዘርፉ በተሰማሩት ባለሙያዎች ዘንድ ቁጭት በመፍጠር የፊልም ኢንዱስትሪ ማዕከል ማድረግ ነው ዋና ዓላማው። በረጅም ጊዜ ደግሞ የፊልሙንና የኪነ ጥበብ ዘርፉን የላቀ ደረጃ ላይ በማድረስ በኢኮኖሚ ለአገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ማስቻል ነው።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19/2012
ዳግም ከበደ