ታኅሣሥ 15 ቀን 2012 ዓ.ም መስቀል ፍላወር አካባቢ የሚገኘው ቱሊፕ ኢን ሆቴል ደጃፍ ላይ በርከት ያሉ ጋዜጠኞች ተሰባስበዋል። ጋዜጠኞቹ ወደ ሆቴሉ የመጡት የኢትዮ ተሽከርካሪዎች አስመጪ ባለቤቶች ማኀበር የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለመታደም ነበር። ግን መግለጫው ፍቃድ አልተሰጠውም በሚል ምክንያት ሊካሄድ አልቻለም። አዘጋጆቹ እንደሚሉት መግለጫ እንደሚሰጥ ለአካባቢው ፖሊስ ማሳወቃቸውን ሆኖም መግለጫው ሊሰጥ ከሰዓታት ቀደም ብሎ ከሆቴሉ ስልክ ተደውሎ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ ክፍል ማስፈቀድ እንዳለባቸው እንደተነገራቸው ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት ጋዜጣዊ መግለጫው ቢስተጓጎልም ከማኀበሩ የበላይ ኃላፊዎች ጋር ሃሳብ ለመለዋወጥ ዕድል ማግኘታችንም አንድ መልካም አጋጣሚ ነበር።
የኢትዮ የተሽከርካሪዎች አስመጪ ባለቤቶች ማኀበር አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ከውጭ በሚገቡ መኪኖች ላይ ከ100 እስከ 500% ማለትም ከ 0 እስከ 1 ዓመት ያገለገሉ 100%፣ ከ1 እስከ 2 ዓመት ያገለገሉ 150%፣ ከ2 እስከ 4 ዓመት ያገለገሉ 200%፣ ከ4 እስከ 7 ዓመት ያገለገሉ = 300%፣ ከ7 ዓመት በላይ ያገለገሉ 500% ኤክሳይዝ ታክስ ለመጣል ማሰቡ ዘርፉን ከጨዋታ ውጪ ሊያደርገው እንደሚችል ሥጋታቸውን ይገልጻሉ። በአጠቃላይ 4 ሺ 500 ገደማ የተሽከርካሪዎች አስመጪዎች በሥራ ላይ እንዳሉ የሚናገሩት እነዚህ ወገኖች እጅግ ከበድ ያለው ጭማሪ ሲተገበር በዘርፉ ውስጥ ላሉ ወገኖች ምን የተመቻቸ ሌላ አማራጭ አለ ሲሉም ይጠይቃሉ። በዘርፉ በርካታ ወገኖች መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰዋል፣ በርካታ ወገኖች ተቀጥረው ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩበት ይገኛሉ። ዘርፉ ሲጎዳ እነዚህ ወገኖች አብረው እንደሚጎዱ ለምን አልታሰበም በማለት ይጠይቃሉ።
በተጨማሪም የኤክሳይዝ ታክስ መጨመሩ የመኪና ዋጋ እንዲሰቀል ያደርጋል የሚሉት እነዚህ የዘርፉ ተዋንያን ሰዎች በራሳቸው ጥረት እንኳን በቀላሉ መኪና ገዝተው ሐብት እንዳያፈሩና የትራንስፖርት ችግሩንም በመቅረፍ ረገድ ሚና እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነው ሲሉ ይኮንናሉ።
አንድ የመኪና አስመጪ ለዚህ ጹሑፍ አቅራቢ እንደተናገሩት መኪና አዲስ ስለሆነ እንደማይበላሽ፣ የተወሰነ ዓመት ያገለገለ በመሆኑ ደግሞ በተደጋጋሚ እንደሚበላሽ ተደርጎ የሚነገረው ፕሮፖጋንዳ ስህተት ነው ይላሉ። ከቻይና የሚገቡ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ስድስት ወራት ገደማ አገልግለው ማጨስ ይጀምራሉ። እኛ ግን የምናስመጣቸው መኪኖች የጃፓን ምርት የሆኑ ቶዮታ መኪኖችን ነው። መኪኖቹ ጠንካራ ናቸው። በአገር ውስጥ በቂ መለዋወጫ አላቸው። ሌላው ቀርቶ መካኒኮችም በሚገባ የሚያውቋቸው መሆኑ በአስተማማኝ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ አስችሏቸዋል። መሸጥ ቢፈለግ ቶሎ ከእጅ የሚወጡ ናቸው። እነዚህ መኪኖች ላይ ታክስ መቆለል በእውነቱ ዘርፉን ማሽመድመድ፣ ሕዝቡም በአቅሙ ሐብት እንዳያፈራ ማድረግ ነው ብሏል።
ከመስከረም ወር አጋማሽ ወዲህ የታክስ ባለሥልጣኑ ከዚህ ቀደም የሚያደርገውን የ30 በመቶ የእርጅና ቅናሽ እንዲቀር በማድረጉ የመኪና ዋጋ በነጠላ ከ100 ሺ ብር በላይ ጭማሪ ማሳየቱን አስረድተዋል። የመኪና አስመጪው ይህንን በምሳሌ ሲያስረዱ ቪትስ (የሁለት ሺ ሞዴል) 520 ሺ ብር ገደማ እየተሸጠ ነው። ከመስከረም ወር በፊት ግን ከ400 ሺ በታች ነበሩ። ኮሮላ (2003 ሞዴል) 820 ሺ ብር ገደማ እየተሸጠ ነው። ቀደም ሲል ከ690 እስከ 700 ሺ ብር ነበሩ። አሁን ደግሞ የኤክሳይዝ ታክሱ በሥራ ላይ ሲውል በምን ያህል ዋጋው ሊሰቀል እንደሚችል መገመት ይቻላል ብለዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር ግን ከኤክሳይዝ ታክስ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን መሠረት አድርጎ እንደሚከተለው ማብራሪያ ሰጥቷል።
ኤክሳይዝ ታክስ የቅንጦት ዕቃዎች ሆነው ዋጋቸው ጨመረም አልጨመረ መሠረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ተፈላጊነታቸው በማይቀንስ ዕቃዎች ላይ እንዲሁም የኅብረተሰቡን ጤና የሚጎዱ እና ማህበራዊ ችግሮችን የሚያስከትሉ ዕቃዎችን አጠቃቀም ለመቀነስ ሲባል የሚጣል ነው።
በሥራ ላይ የቆየው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307/2002 አዋጅ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ እና ከሌሎች ሀገራት ልምድ አኳያ መሻሻል ስለሚገባው ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡት እና ሀገር ውስጥ በሚመረቱት በተለያዩ ምርቶች ላይ ለውጥ ለማድረግ ረቂቅ ወጥቶ ታኅሣሥ 7/2012 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀረበ በኋላ ለዝርዝር እይታ ወደ ፋይናንስና ገቢ ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።
ረቂቅ አዋጁ የተዘጋጀው በገንዘብ ሚኒስቴር ሲሆን ቀጣይ የኮሚቴው ምርመራ እና የሕዝብ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ፀድቆ ወደ ገቢዎች ሚኒስቴር የሚመጣው ለተግባር ብቻ ነው። በሌላ አገላለጽ የታክሱን ረቂቅ በማዘጋጀት የመወሰን ስልጣን ላለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያቀርበውና የሚያስወስነው የገንዘብ ሚኒስቴር ነው ማለት ነው።
ረቂቅ አዋጁ ካሰፈራቸው በርካታ የማሻሻያ አይነቶች በተጨማሪ አዳዲስ ምርቶችም ወደ ኤክሳይዝ ታክስ ውስጥ የገቡ ሲሆን በርካታ ምርቶችን ያካተተ ለውጥ ቢኖረውም በዋናነት እያነጋገረ ያለው የመኪና ጉዳይ ነው። ከዚህ በፊት በነበረው አዋጅ መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ይከፈል የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ በአዋጅ ቁጥር 307/2002 መሠረት እንደ ሲሲያቸው መጠን ነበር። ይኸውም፤ እስከ 1 ሺ 300 ሲሲ 30 በመቶ፣ ከ1 ሺ 301 እስከ 1 ሺ 800 ሲሲ 60 በመቶ እና ከ1 ሺ 801 በላይ 100 በመቶ ነበር። ይህ አመዳደብ ለአዳዲስም፣ ላገለገሉትም ተሽከርካሪዎች ተመሳሳይ ስለነበር በርካታ አሮጌ መኪኖች ወደ ሀገር እየገቡ ችግር አስከትለው ነበር።
ችግሮቹም፤ አሁን እየተበራከተ ለመጣው የትራፊክ አደጋ አንድ መንስኤ መሆን፣ ለአየር ብክለት አስተዋጽኦ ማድረግ፣ ከፍተኛ የነዳጅ ፍጆታን መጠቀም፣ በተደጋጋሚ ቴክኒክ ብልሽት መለዋወጫን መጠቀም እና ሀገር ውስጥ በሚመረቱት ላይ የገበያ ጫና ማሳደር ናቸው።
ለዚህ ረቂቅ አዋጅ መነሻ የሆነው ጥናት እንደሚያመለክተው በኢኮኖሚ ዕድገታቸው ወደ ኋላ የቀሩ አገሮች ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ የሚያመርቱ ሳይሆኑ ከውጪ የሚያስገቡ ናቸው። ከውጪ ከሚያስገቧቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ ያገለገሉ ናቸው። ዲሏት (Deloitte) የተባለው ኩባንያ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በናይጄሪያ ባደረገው ጥናት፤ ወደ እነዚህ ሀገራት ከሚገቡ አስር ተሽከርካሪዎች ውስጥ ስምንቱ ያገለገሉ ናቸው። እ.ኤ.አ. በ2017 የሀገራችን ጉምሩክ መረጃ መሰረት ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 88 በመቶዎቹ ያገለገሉ ናቸው።
በዓለም ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ወደ 1.2 ቢሊዮን የሚጠጉ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ ይገመታል። ከነዚህ ተሽከሪካሪዎች አብዛኞቹ በአሮጌነት ተገዝተው በማደግ ላይ ወደሚገኙ ሀገሮች የገቡ ናቸው። በብዙ ሀገሮች የትራንስፖርት ዘርፍ በከተሞች ለሚከሰተው የአየር ብክለት ዋና ምክንያት ሲሆን በአንዳንዳንድ ከተሞች እስከ 80 በመቶ ለሚሆነው የአየር ብክለት አስተዋጽኦ ያደርጋል። ለአየር ብክለቱ ዋነኛ ምንጭ ደግሞ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ናቸው።
ከሁሉም በላይ የሚያስጨንቀው ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ከአዲሶቹ ይልቅ ወደ አካባቢ አየር ከፍተኛ መጠን ያለው ብክለት ሲለቁ ህይወት ባላቸው ፍጡራን ላይ የሚስከትሉት ጉዳት ነው። ለአብነትም፡-
– የመተንፈሻ አካል በሽታን (እንደ አስምና ብሮንካይትስን) ያባብሳል፣ ተክሎችን ይጎዳል፤
– የአሲድ ዝናብ ያስከትላል (ሰልፈር ዳይኦክሳይድ)፤
– ከፍተኛ ልቀት ባለው ጭስ የሚወጣው ካርቦንሞኖኦክሳይድ በደም ውስጥ የኦክሲጅን ዝውውርን በማወክ ለከፍተኛ ጉዳት፤ በተለይ የልብ ሕመም ላለበት ሰው የከፋ ጉዳት ያስከትላል፤
– በቀጥታ የሰውን ጤንነት ባያውክም የግሪን ሐውስ ኢፊክት በመፍጠር ለአካባቢ አየር መሞቅ እና ለአየር ንብረት መለወጥ ምክንያት ነው (ካርቦንዳይኦክሳይድ)፤
– በታችኛው የከባቢ አየር ክፍል ኦዞን እንዲፈጠር ምክንያት በመሆን የዐይን መቆጥቆጥ እና የመተንፈስ ችግር ይፈጥራል (ናይትሮጂን ኦክሳይድ)፤
– በጣም ደቃቅ የሆኑ ብናኞች ወደ ሳንባ ውስጥ ዘልቀው ሳንባን በመጉዳት የመተንፈሻ አካል ሕመምን ያባብሳሉ (ተናኝ ኦርጋኒክ ውህዶች)፤
– በተለይ ሕጻናትን የሚጎዳ ሲሆን የነርቭ እና የአእምሮ ሥርዓትን ያቃውሳል።
በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሠረት በዓለማችን በየዓመቱ 1 ነጥብ 25 ሚሊዮን ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ፤ ከ20 እስከ 50 ሚሊየን ያህሉ ደግሞ የአካል ጉዳት ይደርስባቸዋል። ከዚህ አደጋ ውስጥ እስከ 90 በመቶ የሚሆነው በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት የሚከሰት ሲሆን በኢትዮጵያ በ100 ሺ ተሽከርካሪዎች 5 ሺ የሞት አደጋዎች በመድረስ በአደጋው ከፍተኛነት ከዓለም የአምስተኛ ደረጃን አስይዟታል። የአገልግሎት ዘመናቸው ከእስከ 12 ዓመት ከሆናቸው ተሽከርካሪዎች 25 በመቶ እና ከ13 ዓመት በላይ ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች 50 በመቶ አደጋዎች የሚደርሱት በቴክኒክ ብልሽታቸው ነው።
ሌላው፤ ከውጪ ሀገር በሚገቡ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች እና በአዳዲሶቹ መካከል የታሪፍ ልዩነት ባለመኖሩ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ማበረታታት አልተቻለም። ስለዚህ፤ የሀገር ውስጥ አምራቾችን የገበያ ችግር ለመፍታትም የአዋጅ ማሻሻያው አስፈላጊ ነው።
የሀገራችን ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች በዓመት 11 ሺ 600 ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም አቅም ቢኖራቸውም ከነርሱ በሦስት እጥፍ በበለጡና ከውጪ በሚገቡ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ምክንያት በሙሉ አቅማቸው ማምረት እና ገበያውን መቆጣጠር አልቻሉም።
ይህ ሁሉ ተጽዕኖ እያለ ሀገራችን ከ54ቱ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ሀገራቸው በሚገቡ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ገደብ ካልጣሉት 27 ሀገራት አንዷ ሆናለች። (ገቢዎች ሚ/ር)
እንደ ማሳረጊያ
ኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጁ የሚመለከተው ተሽከርካሪዎች ብቻ አይደለም። በተመሳሳይ ሁኔታ የቢራ፣ የለስላሳና ውሃ አምራቾች ቅሬታ እያቀረቡበት መሆኑ እውነት ነው። በተለይ የቢራ አምራቾች በኤክሳይዝ ታክሱ ረቂቅ አዋጅ መሠረት ከ35 እስከ 40 በመቶ ታክስ የተጣለባቸው ሲሆን ይህ መሆኑ በገቢያቸው ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል እየተናገሩ ነው። በአሁን ሰዓት በገበያ ላይ ፋብሪካዎቹ ተቀባይነት ያለው ዋጋ በሚሉት (Recommended price) የአንድ መደበኛ ቢራ ዋጋ ከ15 እስከ 17 ብር ይሸጣል። በአዲሱ ጭማሪ ግን የአንድ መደበኛ ቢራ ዋጋ በጠርሙስ 25 ብር እና ከዚያ በላይ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ይህ ማለት የቢራ ሽያጭ እንዲያሽቆለቁል ሚና ይኖረዋል። የሽያጭ መጠን ሲቀንስ ደግሞ የፋብሪካዎቹ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን ይቀንሳል። አትራፊነታቸው እንዲሁ ይቀንሳል። በዓመት ለመንግሥት የሚከፍሉት የትርፍ ግብርን እንዲሁ ይቀንሳል። ገቢያቸው በመቀነሱም ሠራተኞች እንዲቀንሱ ሊገደዱ የሚችሉበት ዕድል አለ። በተዋረድም ቢራ በማከፋፈልና በመሸጥ የሚተዳደሩ ሰፊ ቁጥር ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ገቢያቸው ይጎዳል። ከሥራ ውጪ የሚሆኑም ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚጠበቅ ውጤት እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ከወዲሁ ሥጋታቸውን እየተናገሩ ነው።
እንደሄይኒከን ዓይነት ግዙፍ የቢራ ፋብሪካዎች ከገብስ አምራች ገበሬዎች ጋር የነበራቸው ጥብቅ ትስስር መቀነሱ አይቀሬ ይሆናል። ይህ ማለት አርሶአደሩ ገብስ ቢያመርትም የሚቀበለው ፋብሪካ ስለማይኖር ገቢው ያሽቆለቁላል። የሚያበረታታው አለመኖሩም በዘላቂነት ምርታማነቱን ይጎዳል። ፋብሪካዎቹ የያዟቸው በቢሊየን ዶላር/ዩሮ የሚቆጠር የማስፋፋት ኢንቨስትመንት (ፕሮጀክቶች) እንዲያጥፉ ይገደዳሉ። ይህም በፕሮጀክቱ ምክንያት የሚፈጠር የሥራ ዕድል፣ ሊገኝ የሚችል የውጭ ምንዛሪ እንዲቀር ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ይህ ሐተታ የኤክሳይዝ ታክስ ዙሩያ ገባ ተጽዕኖዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአግባቡ እንዲታዩ፣ እንዲፈተሹና ከሞላ ጎደል ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዋጅ እንዲወጣ ጥቆማ የሚሰጥ ነው።
በመኪና አስመጪዎች በኩል ከሚነሱ ጉዳዮች ሚዛን የሚደፉት መንግሥት የራሱን ገቢ ለማሳደግ ይህን እርምጃ ሲወስድ እንደዜጋ ለእኛስ ምን ታስቦልናል የሚለው ጥያቄያቸው በአግባቡ መመለስ ያለበት ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የትራንስፖርት እጥረት እጅግ በተባባሰበት በዚህ ወቅት የመኪኖችን የኤክሳይዝ ታክስ ዋጋ መስቀል የሚኖረው ፋይዳ በአግባቡ ስለመታየቱ የሚታወቅ ነገር የለም። በተጨማሪም የዜጎች ሐብት የማፍራት መብት የሚያጣብብ አዋጅ እንዳይሆንም መጠንቀቅ ይገባል።
ጉዳይ የተመራለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮምቴ ርዕሰ ጉዳዩ አወዛጋቢ ከመሆኑ አንጻር በአንድ መድረክ ብቻ ሳይወሰን ሰፋፊ የሕዝብ አስተያየት መሰብሰቢያ መድረኮችን በማዘጋጀት ረቂቅ አዋጁ በተለይ ከሕዝብ ጥቅም አንጻር የሚኖረውን አንደምታ በጥብቅ ሊያየውና ሊፈትሸው ይገባል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
ፍሬው አበበ