አደሬ ሠፈር
በማለዳው መርካቶ ምን አለሽ ተራ ከሚባለው ሥፍራ ከመድረሴ በፊት ‹‹አደሬ ሰፈር›› ከሚባለው ስፍራ ተገኝቻለሁ። የአካባቢው ሁኔታ ግሩም ነው። አቤት ግፊያ! በዚህ አካባቢ ለሚያልፉት ሳይሆን መኖሪያቸውን በዚሁ አድርገው ሕይወታቸውን የሚገፉ አቅመ ደካሞችን በዓይነ ህሊናዬ ታሰቡኝ። ሁሌ ግፊያ የማይለየውን ኑሮ እንደምን ችለውት ይሆን ህይወታቸውን የገፉት ስል ራሴን ጠየኩኝ፤ ምላሽ ባላገኝም። እንደምን የአካባቢውን ግፊያ ችለው ወጥተው ይገቡ ይሆን? ግፊያና ጥድፊያው ሰዎች ከኑሮ ጋር እሽቅድምድም ስለመጀመራቸው ያስበቃል። ወጪ ወራጁ በሩጫ ላይ ነው።
ትንሹም ትልቁም እንደአቅምቲ ተፍ! ተፍ! ይላል። በዚህ ሰፈር ሁሉም ታታሪ፤ ሁሉም ሰርቶ አደር ነው። ከእንቅስቃሴ ውጭ የሚታዩ ሠዎች በጣም ጥቂት ናቸው። አካባቢው ላይ ካለው እንቅስቃሴ አኳያ ማየት የማይታክታቸው ዓይኖች፤ ሠርተው የማይዝሉ እጆች፤ ተራምደው የማይታክቱ እግሮች፤ ተናግረው የማይደመጡ አንደበቶች መገኛቸው ከዚህ ሰፈር ይመስላል።ከዚህ ስፍራ ዕጣን፤ ጭሳጭስ፣ ስራስር እና ሌሎች ተያያዥ እቃዎችን ከሚሸጡ ሰዎች መንደር ተገኘሁ። እንደ ገዥ ሆኜ ጠየኩኝ፤ እንደተመልካች ሆኜ አካባቢውን በሁሉም አቅጣጫ ቃኘሁኝ፤ እንደጋዜጠኛም ያወቁትን ለሌሎች ለማሳወቅ መቅረፀ ድምጼን አስተካክዬ ከአንዱ ጥግ ከሚገኙ እናት ጋር ወግ ጀመርኩኝ።
ወይዘሮ ሙሃባ ሰማው ይባላሉ፤ ውልደታቸው ወልቂጤ ነው። ጭሳጭስ እና ስራስር ንግድ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ አሳልፈዋል። በእርሳቸው አገላለፅ የጭስ ንግዳቸው አራት የአገር መሪዎችን (መንግስቱ ኃይለማርያም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን) አሳይቷቸዋል።
ገና በልጅነት
ወይዘሮ ሙሃባ ወደ አዲስ አበባ የመጡት ገና በልጅነታቸው ነበር። ታዲያ ያኔ ወደዚህ የመጡት አጎታቸው ዘንድ ነበር። በወቅቱ ወደ ትምህርት ከማዘንበል ይልቅ የአጎታቸውን ሚስት በሥራ እያገዙ አደጉ። አካባቢው ነጋዴዎች ይበዙበት ስለነበርም በማየት ብቻ እውቀት ቀሰሙ። ዕድሜያቸው ለአቅመ ሄዋን ሲደርስም ከትዳር አጋራቸው ጋር ተጣምረው እህል ውሃቸውን አብረው መቁረስ ጀመሩ። እየተሳሰቡ እተጋገዙ ሕይወታቸውን ይመሩ ጀመር። ስድስት ልጆችም ወለዱ፤ የሚቻላቸውን ሁሉ እየሰሩ የአብራኮቻቸውን ክፋይ ማሳደጉን ተያያዙት።
በዚህ ሂደት ውስጥ እያሉ የትዳር አጋራቸው ከ12 ዓመታት በፊት በሞት ተለዩዋቸው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ እነዚህን ስድስት ልጆች ለማሳደግ ትልቅ ኃላፊነት በጫንቃቸው ላይ አረፈባቸው። ይህም ብቻ አይደለም ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ለመምራትም ግዴታዎች ሁሉ በወይዘሮ ሙሃባ ትከሻ ላይ ወደቀ።
እኝህ እናት ስድስት ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከእሾህና ቆንጥር የበለጠ የሚዋጋ የሚያደናቅፍ የኑሮ ውጣ ውረድ ፈትኗቸዋል፤ ብዙ ፍዳም አይተዋል። በዚህ ስራስርና ጭሳጭስ ንግድ ስድስት የአብራካቸውን ክፋይ ጉሮሮ ደፍነው ኑሯቸውን ደጉመዋል። ልጆቻቸውን የሰው ፊት ከማየት አድነው ትምህርታቸውን እንዲማሩ አድርገዋል- ታታሪዋ እናት። በዚህም ብቻ ሳያበቃ ማህበራዊ ሕይወታቸውን እየደጎሙ ከሰዎች ጋር ተዋውለዋል፤ ተዳድረዋል። ሰባተኛ ልጃቸውም ካደገች በኋላ በድንገተኛ ሕይወቷ አልፏል። እነዚህን ሁሉ ልጆችም በዚሁ በጭሣጭስ ንግድ ከዛሬ ላይ አድርሰዋል።
«ሥራሥራዊ» ትንታኔ
ወይዘሮ ሙሃባ የሚነግዷቸው ስራስሮች፣ ጭሳጭሶችና ቅጠላቅጠሎች ቤትን በጥሩ ጠረን ከማወድ በዘለለ ብዙ ጥቅም እንዳላቸው ይናገራሉ። ለዓመታት በዚህ ሥራ ላይ የቆዩት ወይዘሮዋ ታዲያ ጥቅማቸውን በሚገባ እየተነተኑ ያስረዳሉ። ብዙ ሰው አስተምሬ ከዛሬ ደርሻለሁ ይላሉ። በዚህም ዛሬ እንጀራቸው የተከፈተ ብዙ ሰዎች አሉ ይላሉ።
ወይዘሮዋ የሚሸጧቸውን ስራስሮች ጥቅም ሲተነትኑ ‹‹የጅማ እንጨት›› ከሽቶ በላይ ቤት ያውዳል። ሴቶቹ ቁም ሳጥን ላይ ሲያስቀምጡት ሁሌ ቤቱ ሽቶ ሽቶ ይሸታል። ‹‹ወይባ›› ደግሞ ከአጋምና እሬት ጋር ተቀላቅሎ ለሰባት ቀን ቢታጠኑ ለማህጸን ካንሰር ፍቱን መድሃኒት ነው። በዚህም የዳኑ አውቃለሁ ባይ ናቸው።
‹‹ቀበሪቾ›› ከሌሎች ጭሳጭሶች ጋር ሆኖ ለብዙ ነገር መድሃኒት ነው። ወገርት፤ ግዛዋ እና ቀበሪቾ በአንድ ላይ ሲሆኑ ደግሞ ‹‹ጂኒ›› ከአካባቢው ብን ብሎ ይጠፋል ይላሉ። ጃርዲያ፣ ኮሶና ታይፎይድ ላለበት ሰው ደግሞ ‹‹መተሬ›› የሚባለው ፍቱን መሆኑን ይናገራሉ። ‹‹መቅመቆ›› የሚባለው ሰባት ቀን ከተጠጣ ደም ብዛት ላለበት ሰው ለውጡን ይመለከተዋል። ‹‹ፌጦ›› ለደም ብዛት ለመቀነስ፤ ብርድ ለማጥፋትና ለመጋኛም መድሃኒት ነው። ለስኳር በሽታም የሚሸጥ ቅጠል አለኝ ይላሉ። ‹‹አርቲ›› ጥሩ መዓዛ ያለው ሲሆን ቤት በጥሩ ጠረን ያውዳል። ‹‹ድንገተኛ›› የሚባለው ደግሞ ሰዎች በጠዋት ሲወጡ በድንገት ሲታመሙ ወዲያውኑ ከወሰዱበት ከህመማቸው ይታደጋቸዋል። ‹‹የምድር እንቧይ›› ደግሞ ቁስል በማድረቅና በመፈወስ የሚስተካከለው የለም። ታዲያ የእነዚህን ስራስሮችና ጭሳጭሶች እንደጥቅማቸው ዋጋቸው ከፍ ያለ ነው። ለአብነት ቀበሪቾ በኩንታል ከ3ሺ500 እስከ 4000 ብር፤ ወይራ 600 እስከ 700 ብር፣ ፌጦ በኩንታል ደግሞ ከ10 እስከ 12ሺ ብር እንደሚገዙ ይናገራሉ። ግን እነዚህን ሁሉ መድሃኒቶች በባለሙያ ትዕዛዝ ካልሆነ በዘፈቀደ መጠቀም አደጋ እንዳለው ያስጠነቅቃሉ። ከዚህም በተጨማሪ ዘመናዊ ህክምናን ከባህላዊ ህክምና ጋር ተሳስሮ ቢሠራ ኢትዮጵያም ተጠቃሚ ናት ባይ ናቸው።
ለህክምና
እነዚህን ስራስሮች በዋናነት ሰዎች ለማጨስና ለመልካም ጠረናቸው ብሎ ይገዛቸዋል። ከዚህ ውጭ ደግሞ የባህል ህክምና የሚቀምሙ ሰዎች ከዚህ ስፍራ ዋንኛ ግብዓት እንደሚያገኙ ወ/ሮ ሙሃባ ይናገራሉ። ለረጅም ጊዜ እነዚህን ስራስሮችና ጭሳጭሶች የሚገዛቸው አንድ ኤርትራዊ ወዳጅ እንደነበራቸው ያስታውሳሉ። ለምን በብዛት እንደሚገዛ ሲጠይቁትም እነዚህ ስራስሮችና ጭሳጭሶች በመጠን፤ በዓይነትና በጥራት ተቀምመው ፍቱን መድሃኒቶች እንደሆኑ ይነግራቸዋል። በዚህም የተነሳ ይህ ደንበኛ ለረጅም ጊዜ ከእርሳቸው ከየዓይነቱ ይሸምት ነበር። አሁን በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ሠላም በመውረዱ ሰውዬው ወደ አስመራ አምርተዋል። ከእኝህ ሰውዬ ውጭም አንዳንድ የባህላዊ ህክምናን የሕይወታቸው አካል አድርገው የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ከዚህ ስፍራ እንደማይጠፉ አጫውተውኛል።
ሥራ-ለልጆቼ
ወይዘሮ ሙሃባ ደፋ ቀና ብለው ከ30 ዓመታት በላይ በዚህ ሥራ ልጆቻቸውን አስተምረው የዕለት ጉርሳቸውን ሸፍነው ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ታዲያ አሁን ላይ አቅማቸውም እየደከመ ሥራውም እየቀዘቀዘ ስለሆነ ኑሮ ከብዷቸዋል። በተለይ ደግሞ ልጆቻቸው በደካማ ጎናቸው አስተምረው ሥራ አጥ ሆነው መቀመጣቸው ይቆጫቸዋል። አንድ ልጃቸው ብቻ ወራቤ ባንክ ተቀጥሯል። ከዚህ ውጭ ከልጆቻቸው አንድም ሰው የእርሳቸውን ሥራ ለምዶ አጠገባቸው ሆኖ የሚያግዝ የለም፤ሥራ ይዘውም ደካማ እናታቸውን አይደጉሙም። ታዲያ ይህ ነገር እኝህን እናት እረፍት ነስቷቸዋል። በተቻለ መጠን ለልጆቼ ሥራ ለማስያዝ ብሞክርም ሁሉ በዘመድ በመሆኑ ግራ ግብት ብሎኛል ይላሉ። አሁን ፀሎቴ ሁሉ ልጆቼን የሥራ ዕድል የሚያገኙበት መንገድ መፈለግ ነው ይላሉ። ታዲያ የሚቻላቸው ሰዎች ችግሬን ቢመለከቱ ሲሉ ይናገራሉ።
በአራቱም ማዕዘናት
እነዚህን ጭሳጭሶችና ስራስሮች ከአንድ ስፍራ ብቻ የሚመጡ አይደሉም። ከባሌ እስከ መቐለ፤ ከጅማ እስከ አዳማ፤ ከቀብሪድሃር እስከ ጎንደር፣ በአራቱም ማዕዘናት ግብዓቶች የሚያቀርቡ አካላት አሉ። አንዳንዶቹን ቀጥታ ጭነው የሚመጡ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በተሽከርካሪ ጭንው ይልካሉ። በቃላት መታመን ላይ በተመሰረተ ውል እርሳቸው ሰዎችን ሳያስቀይሙ፤ ሰዎችም በእርሳቸው ሳይቀየሙ ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ዘልቀዋል።
ቀደም ሲል ደግሞ እራሳቸው በየቦታው ተንቀሳቅሰው ገዝተው ለመምጣት ይሞክሩ ነበር። ግን ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ በዚህ ላይ ደግሞ ውጣ ውረዱ እየበዛ ድካሙ እየጨመረ ሲሄድ ወደ ክልሎች መሄዱን ትተውት ሌላ አማራጭ ይጠቀሙ ጀመር። ምንም እንኳን ይህን ያክል ትርፋማ ባያደርግም የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ግን ዛሬም መደባቸው ላይ ቁጢጥ ብለው ይውላሉ። ከሁሉም በላይ የሚያስደስታቸው ነገር ቢኖር በአራቱም ማዕዘናት የሚያገኟቸው ግብዓቶች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ኢትዮጵያን እንዲያውቁ አግዟቸዋል። በአራቱም ማዕዘናት ፍቱን የሆኑ መድሃኒቶች ስለመኖራቸውም ተገንዝበዋል። አገሪቱ ከጠረፍ እስከ ጠረፍ ድረስ የምትወደድ፤ የምትሞገስ የምትወደስ ናት ይላሉ። ከአንዱ ስፍራ ያለው ከሌላው ስፍራ ለመኖሩ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያን ተደጋግፈን እንጂ ተገፋፍተን እንደማይሆንልን ማሳያ ነው ሲሉ በህይወታቸውና በሥራቸው ያካበቱትን ልምድ ያካፍላሉ- ወይዘሮ ሙሃባ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር