ኢትዮጵያ በዓለም ከምትታወቅባቸው ባህሎች መካከል የሃይማኖት መቻቻልን ያክል ግዝፈት ያለው አኩሪ ባህል ያለ አይመስልም፡፡ኢትዮጵያ አይሁድን፤ ክርስትናንና እስልምናን ከውጭ የተቀበለችና ለዘመናትም ተቻችለውና ተከባብረው እንዲኖሩ ያደረገች ድንቅ ሀገር ነች።ይህም አኩሪ ባህሏ በውጭው አለም ዘንድ በምሳሌነት ሰርክ የሚነሳና ብዙዎችም የሚቀኑበትና የሚመኙት የህዝቦችዋ የአብሮነት መገለጫ ነው፡፡
ይህን አኩሪ ባህል ለመናድ የሚያስቡና ከጥፋት ፖለቲካዊ ጥቅም ለማጋበስ የቋመጡ ስግብግቦች ይህንን አብሮ ለሺህ ዘመናት ጸንቶ የቆየውን የመቻቻልና መከባበር ባህል ለመናድ ጉድጓድ ሲምሱ ይታያሉ።በአማራ ክልል በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ ከተማ ዓርብ ታኅሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰው ቃጠሎ አንዱ ማሳያ ነው።ሴረኞች በጎነጎኑት በዚህ ጥቃትም አራት መስኪዶች እና በርካታ ሱቆች ሙሉ ለሙሉ ተቃጥለዋል።ይህ በምንም አይነት መልኩ ክርስቲያኑንም ሆነ ሙስሊሙን የሚወክል ደርጊት አይደለም፡፡
ለዘመናት ክፉና ደጉን ጊዜ አብረው ሲያሳልፉ የኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ መስጊድ የሚያቃጥሉበት ሆነ ቤተ ክርስቲያን የሚያነዱበት ታሪክም፤ ምክንያትም የላቸውም። ይልቁንም ኢትዮጵያውያን የሚታወቁት አንዱ የአንዱን ቤተ እምነት ገንዘብ እያዋጣ ሲገነባ፤ አንዱ የአንዱን ቤተ እምነት እንዳይደፈር ሲጠብቅ ነው።ለበርካታ ዘመናት ጠንካራ ትስስር ያለው የሞጣ ሙስሊምና ክርስቲያን፣ ሙስሊሙ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ክርስቲያኑ መስጊዶችን ላለፉት ሺህ ዓመታት እየገነቡና እየተጋገዙ ኖረዋል።የዚህን ህዝብ አብሮነት ለመበጣጠስና ይህም እኩይ ደርጊት ወደ ሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች ተስፋፍቶ ሀገሪቱ የጥፋት አውድማ እንድትሆን በማሰብ የሃይማኖት ተቋማትን በእሳት ለማንደድ ጉልበት አግኝተዋል፡፡ይህ ግን መቼም ቢሆን አይሳካም።አብሮነታችንንም አያናጋውም፡፡
አስተዋይ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሴረኞች ዕኩይ ተግባር ሳይጋለጥ አብሮነቱን በማሳየት ላይ ይገኛል።ያለ ምንም ጣልቃ ገብነትም የአካባቢው ነዋሪና የክልሉ መንግሥት የተቃጠሉትን መስኪዶች ለመገንባት እንቅስቃሴ ጀምረዋል።በተለያዩ አካባቢዎችም ተመሳሳይ የድጋፍና አብሮነት ድምጾች እየተሰሙ ነው።ይህ ድሮም የነበረ፤ ዛሬም ያለ፤ ወደፊትም የሚኖር የአብሮነታችን ማሳያ ነው፡፡
አብሮነታችንን ከማጠናከር ጎን ለጎን ግን ሴረኞች ምሽጋቸው ስር ተሸሽግው መቅረት የለባቸውም።ከዚህ ጥፋት ፖለቲካዊ ትርፍ እናገኛለን ብለው የቋመጡ ግለሰቦችም ይሁኑ ቡድኖች ሳይውል ሳያደር ለህግ መቅረብ አለባቸው።በፍትህ አደባባይ ቆመውም ፍርድ ማግኘት አለባቸው።ለዚህ ደግሞ መንግስትና ህዝብ ተቀናጅተው መስራት አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም ሊካስ የሚችለውም ይህ ሲሆን ብቻ ነው፡፡አሁን በተፈጠረው ክስተት ግን መቼም ቢሆን አብሮነታችን የማይናጋ መሆኑን ጠላትም ወዳጅም ማወቅ አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012