አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የምግብ ይዘትን በመከለስና በመለወጥ ለሽያጭ በሚያቀርቡ ግለሰቦች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እንደቀጠለ ቢሆንም በተጠርጣሪዎች ላይ በቂ የፍርድ ውሳኔ እየተሰጠ አለመሆኑን የአዲስ አበባ አስተዳደር የምግብና ጤና ክብካቤ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ሁንዱማ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ምግብን በመከለስና ይዘቱን በመለወጥ ለህብረተሰቡ በሽያጭ የሚያቀርቡ ህገወጥ ነጋዴዎች ተበራክተዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ከነሐሴ 2011 አስከ ጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓም ድረስ በከተማዋ የተለያዩ ስፍራዎች ድርጊቱን በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ በተደረገ አሰሳ በቂ የሚባል ማስረጃ የተገኘ ቢሆንም ተጠርጣሪዎቹን ለህግ አካል አቅርቦ ማስቀጣት ያለመቻሉን ግን ተናግረዋል።
በተጠቀሱት ጊዚያት በተለያዩ ክፍለከተሞች በባለስልጣኑ ባለሙያዎች በተደረገው ፍተሻ በድርጊቱ መሳተፋቸው የተረጋገጠ 151 እንጀራ ቤቶች ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ሲሆን 55 በሚሆኑት ላይም የማሸግ ዕርምጃ በመውሰድ 45 ሊትር የተከለሰ ሊጥን ለማሰወገድ ተችሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ በወፍጮ ቤቶች ላይ በተደረገው ቁጥጥርና ፍተሻ ለ190 ያህሉ ማስጠንቀቂያ በመስጠትና 4 ውፍጮ ቤቶችን በማሸግ 423 ኪሎግራም ጥራቱን ያልጠበቀና ለመፈጨት የተዘጋጀ አህልን ማስወገድ ተችሏል።
በከተማዋ በሚገኙ አንዳንድ ዳቦ ቤቶች ላይ በተደረገው ተመሳሳይ ፍተሻም ከምግብነት የተረፉና የደረቁ ዳቦዎችን መልሶ በማዘጋጀት ለሽያጭ ማቅረባቸው በተደረሰባቸው 23 ዳቦ ቤቶች ላይ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ድርጊቱን የሚከወኑባቸውን 150 የተለያዩ ቁሳቁሶችን ጭምር በመያዝ ማስወገድ ተችሏል።
አቶ አለማየሁ እንደሚሉት በነዚህ ሦስት ወራት እንደተደረገው አሰሳ ሁሉ በተለያዩ ጊዚያት በከተማዋ ተመሳሳይ ድርጊቶች ስለመፈጸማቸው በባለሙያዎች በታገዙ ድንገተኛ ፍተሻዎች ሲረጋገጥ ቆይቷል።ይሁን እንጂ አስካሁን አጥፊዎችን በበቂ ማስረጃዎች አስደግፎ ለህግ አካላት ማቅረብ ያለመቻሉ አጥፊ ግለሰቦች እንዲበራከቱና ድርጊቱ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል።እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ይህ ከሆነበት ዋንኛ ምክንያት አንዱ በባለስልጣን መስሪያቤቱ በፍተሻ ተይዘው የሚቀርቡ ማስረጃዎችን ተቀብሎ በላብራቶሪ የሚረጋግጥ አካል ያለመኖሩ ነው።
ባዕድ ነገሮች የተቀላቀለባቸውን ምርቶች ለማስመ ርመር የተስማሚነት ምዘና ድርጅትን ጨምሮ ወደ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቢላክም ምርመራው ግን በምርቱ ላይ ያሉትን ተጨማሪ ይዘቶች ከመጠቆም በተለየ ውህዱ መርዛምነት ወይም ጀሶን መሰል ባዕድ ነገሮች ስለመቀላቀላቸው የሚያመላክት ባለመሆኑ ለክስ ሂደት የሚያግዝ ማስረጃ እንደማይገኝበት ገልጸዋል።ይህ በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና በነጻ እንዲለቀቁ ምክንያት እየሆነ መጥቷል ።
አልፎ አልፎ ጀሶና መሰል ባዕድ ነገሮችን በተመለከተ በአንዳንድ ግለሰቦች ላይ የተሰጠው የፍርድ ውሳኔን በተመለከተ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ሲናገሩ ውህዱ በባለሙያዎች ፍተሻ አጅ ከፍንጅ በመያዙና በምስክሮች በመረጋገጡ ጭምር መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
የላቦራቶሬ ምርመራ ከሚያደርጉ ተቋማት የሚገኘ ውን ማስረጃ ለክስ ከመጠቀም ይልቅ የተያዘው ንጥረ ነገር መርዛማ ያለመሆኑ ላይ ብቻ ማተኮሩና ጉዳት አያደርስም የሚል እሳቤ መለመዱም እህልና መሰል ምግቦች ባልተገባ መልኩ እየተከለሱ ለገበያ እንዲውሉ ሰፊ ዕድልን እያበረከተ ነው ብለዋል።
ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት ማነስና የባለሙያዎች ቁጥር አለመመጣጠን ለባለስልጣን መስሪያቤቱ ችግር ሆኗል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በወረዳና በክፍለከተሞች ላይ የሚስተዋለው የበጀት እጥረትም የቁጥጥር ሂደቱን በታሰበው ፍጥነት ላለመከወን ዕንቅፋት መፍጠሩን ገልፀዋል።
ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ጉዳይ አጣሪ ዳይሬክተር ወይዘሮ ወሰንየለሽ አድማሱ በበኩላቸው የምግብ መከለሱንና የችግሩን ስፋት ከጉዳዩ ማስረጃ ማነስ ጋር ያያይዙታል።ዳይሬክተሯ እንደሚሉት ምግብ ከሌሎች እህል ነክ ጉዳዮች ጋር መቀላቀሉ ብቻ መርዛማ ነው ሊያስብለው አይችልም። ተገኘ የተባለው ውህድ ለጤና ጎጂ መሆኑን የሚያመላክት ማስረጃ በሌለበት አግባብም ተከሳሾችን ወደ ፍርድ ሂደት አምጥቶ ተጠያቂ ለማድረግ አዳጋች ይሆናል።
እንደ ወይዘሮ ወሰንየለሽ ገለጻ ጤፍን ከሰጋቱራና ከጀሶ ጋር ቀላቅሎ ማስፈጨት ማሕበራዊ ተጠያቂነት ያለውና ነውር የሚባል ድርጊት ነው።ውህዱ ጉዳት የሚያስከትል ስለመሆኑ በበቂ ማስረጃ ካልተረጋገጠ ግን ግለሰቦቹን በህግ የሚያስጠይቅ አስገዳጅነት ሊኖር አይችልም።እነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ባልተሟሉበት ሁኔታም የህግ አካላት ግዴታቸውን አልተወጡም ብሎ መውቀስ ተገቢ ያለመሆኑን ጭምር ዳይሬክተሯ ይናገራሉ።
ዳይሬክተሯ አያይዘውም በቅርቡ በጸደቀው የመድሀኒት ቁጥጥር አዋጅ ላይ ባዕድ ነገርን አስመልክቶ የሰፈረው ነጥብ በበቂ ሁኔታ ያለመብራራቱን ተናግረዋል።በተቋሙ የአፈጻጸም መመሪያ ለጤና ጎጂ የሚባሉትና መርዛማ የሆኑት ተለይተው ያልተቀመጡ መሆናቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ ወሰንየለሽ ተቋሙ ይህን ችግር ለመከላከል በራሱ አቅም የተደራጀ ላቦራቶሪ ሊኖረው እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና ስነ-ምግብ ምርምር ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ተሰማ ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር የመቀላቀል ድርጊት በኢትዮጵያ ብቻ ያለ እንጂ በሌሎች ሀገራት ያልተለመደ ስለመሆኑ ይናገራሉ።ይህ በመሆኑም አስከዛሬ ይህን ቴክኖሎጂ የመጠቀም አጋጣሚው ሳይተገበር ቆይቷል ።በመሆኑም እስከአሁን በነበረው ሁኔታ የላቦራቶሪ ውጤቱ በምግብ ውስጥ የተቀላቀለውን ባዕድ ነገር በአግባቡ ለይቶ ይህ ጀሶ ነው፤ይህ ሰጋቶራ ነው የሚል መረጃን አይሰጥም።
ለችግሩ ስፋት ትኩረት በመስጠት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ተመራማሪዎች ተግባራዊ መሆን በጀመረው የላብራቶሪ አገልግሎት ግን ሰጋቱራና ጀሶ በጤፍ ውስጥ ሲጨመር በእንጀራ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ለውጥ የሚያረጋግጥ ቴክኖሎጂን ይፋ ማድረግ ተችሏል።
ለዚህ የላብራቶሪ አገልግሎት የእውቅና ሰርተፍኬት መገኘቱን የተናገሩት አቶ ማስረሻ አስከዛሬ በነበረው ሂደትም ከላቦራቶሪ ባልተሰጠ ማረጋገጫና በምልከታ ብቻ በሚኖር አሰሳ ግለሰቦችን የመያዝ ልምድ እንደነበረ ያስረዳሉ።ይህ ሆኖ ሲገኝ ያለምንም ማስረጃ ሰዎች የሚጠየቁበት አግባብ በመኖሩ በተለመደ ውዥንብር ማህበራዊ ተጽዕኖ ሲፈጠር እንደነበር አስታውሰው፤ይህም አግባብ እንዳልሆነ አስታውቀዋል።
በመሆኑም ላቦራቶሪው ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገባ የተቀላቀለውን ባዕድ ነገር በአግባቡ ለይቶ ስለሚያስረዳ አጥፊዎች ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚ ያስችል ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
መልካምስራ አፈወርቅ