ከሰሞኑ አንዲት አሽከርካሪ መኪናቸውን ቦሌ አካባቢ አቁመው ወደጉዳያቸው በእግር ያቀናሉ። ከየት እንደመጣ ያልታወቀ አንድ ግለሰብ ታዲያ መኪናዋን በምን ይክፈታት በምን ባልታወቀ ሁኔታ አስነስቶ እየነዳ ይሄዳል። በዚህ ወቅት ታዲያ ሁኔታውን የተመለከቱ ሰዎች ተጠርጣሪውን ለመያዝ ሲሯሯጡ መሪ መጨበጡን ከቁብ ያልቆጠረው ይኸው የመኪና ሌባ በፍጥነት ሲያሽከረክር ከሁለት በላይ ተሽከርካሪዎችን ገጭቶ ይቆማል።
ሰዎችም ተባብረው ግጭት ከደረሰባት ተሸከርካሪ ጋር አብረው ይይዙታል። እንዲህ ባለ መልኩ ባይሆንም ተሽከርካሪዎችን በተመሳሳይ ቁልፍ ከፍተው የት እንዳደረሱ ያልታወቁ አጭበርባሪዎች እየበዙ መምጣታቸው ደግሞ አሳሳቢ መሆኑን የመዲናዋ አሽከርካሪዎች እየገለጹ ይገኛል።
የአውቶሞቢል አሽከርካሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን ዘውዱ፤ ባለአራት እግር ተሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ ጊዜ ከቆሙበት ቦታ እየጠፉ መሆናቸው እርሳቸውንም እንዳሳሰባቸው ይናገራሉ። የመንግሥት ታርጋ የተለጠፈባቸው ተሽከር ካሪዎች ጭምር ከቆሙበት እየተነዱ መሰረቃቸው ከተሰማ ወዲህ ጉዳዩ ከባድ ደረጃ መድረሱን ህብረተሰቡ መገንዘቡን ያስረዳሉ። ተሽከርካሪዎች ከዚህ ቀደም አንዱ አካላቸው ተሰርቆ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ስፍራዎች ላይ ይገኙ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን ተሰርቀው እየተነዱ ከ500 ኪሎሜትሮች በላይ ተጉዘው ተያዙ ሲባል መሰማቱ የችግሩን ግዝፈት እንደሚያሳይ ይናገራሉ።
አቶ ሰለሞን የተሽከርካሪ ስርቆቱን መበራከት ተከትሎ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ይገልጻሉ። እንደ እርሳቸው፤ በተለይ የተሽከርካሪ እጥበት በሚከናወንባቸው ቦታዎች የሞተር ቁልፍ ለሰው መስጠት ችግር ውስጥ ሊያስገባ ይችላል። አንዳንዶች የሞተር ቁልፍ በተለያየ ምክንያት ተቀብለው ወዲያው ተመሳሳዩን የሚቀርጹበት መንገድ አላቸው በመሆኑም ቁልፉ ከባለቤቱ እጅ ምንጊዜም መለየት የለበትም ይላሉ።
ሌላዋ አሽከርካሪ ወይዘሮ ሰዓዳ አበራ በበኩሏ እንደምትገልጸው፤ አሁን ላይ በመዲናዋ በሚገኙ ሰዋራ ቦታዎች ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ አስፈሪ ሆኗል። ተሽከርካሪዎች እየተነዱ ጠፉ የሚለው ጉዳይ እየጨመረ በመምጣቱ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ቢያደርግ ጥሩ ነው። በተለይ የቁልፍ መያዣ በነፃ የሚሰጡ ሰዎች ከተማዋ ውስጥ ተበራክተዋል። እነዚህ ሰዎች ቁልፍ ማንጠልጠያው ላይ የ‹‹ጂፒኤስ›› መቆጣጠሪያን በመግጠማቸው አሽከርካሪው የት እንዳለ በማረጋገጥ፤ ከፍተኛ ክትትል አድርገው ለመስረቅ የተዘጋጁ ሰዎች ስለመሆናቸው በርካታ እማኞች እንዳሉ ያስረዳሉ።
አሽከርካሪ ከመሰረቁ በፊት አስቀድሞ መጠንቀቁ አይከፋም የምትለው ወይዘሮ ሰዓዳ፤ ማንኛውም መረጃ ሲገኝ በፍጥነት ለፖሊስ ሪፖርት ማድረጉ ችግሩን ለመቀነስ እንደሚረዳ ትናገራለች። ፖሊስም በበኩሉ አጭበርባሪዎቹ የመጡበትን አካሄድ በመገንዘብ አስፈላጊውን የማስጠ ንቀቂያ መልዕክት ለኅብረተሰቡ ማስተላለፍ እንዳለበት ትገልጻለች።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ እንደሚገልጹት፤ የተሽከርካሪ ስርቆቱን ስፋት በተመለከተ እና የት አካባቢ እንደሚበዛ ለመግለጽ ዝርዝር ጥናት ያስፈልጋል። ነገር ግን ፖሊስ በየዕለቱ የኅብረተሰቡን ንብረት ከመቆጣጠር ባለፈ አጭበርባሪዎችን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል። ፖሊስ ከሚያደርገው ጥበቃ እና ክትትል ባለፈ ግን አሽከርካሪዎች የተለያዩ የጥንቃቄ ቴክኖሎጂዎችን ሊጠቀሙ ይገባል።
እንደ ኢንስፔክተር ማርቆስ ከሆነ፤ በተለይ የምስል እና የድምጽ መልዕክት የሚያስተላልፉ ቴክኖሎጂዎች ወንጀልን ለመከላከል ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ በመሆኑ አሽከርካሪዎች ሊተገብሯችው ይገባል።ከቴክኖሎጂ ገጠማው ባለፈ ማንኛውም አይነት አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥም ኅብረተሰቡ ለፖሊስ ጥቆማ በማድረግ አጭበርባሪዎችን ማስያዝ ይኖርበታል። መረጃ የመስጠት ልምዱ አሁንም ደካማ ቢሆንም ኅብረተሰቡ በአቅራቢያው ለሚገኝ የፀጥታ ኃይሎች ጥቆማ በማድረግ አጭበርባሪዎችን ማጋለጥ አለበት።
እንደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ፤ ባለፉት አምስት ወራት 84 ተሽከርካሪዎች በስርቆት የተመዘገቡ ሲሆን በማጣራት ሂደት 62 ተሽከርካሪዎች አሳቻ ቦታ ላይ ቆመው እና አንዳንድ አካላቸው ጎድሎባቸው ተገኝተዋል። በዚህም መሰረት 22 ተሽከርካሪዎች መጥፋታቸውን እና ከ15ቱ ተሽከርካሪዎች ዝርፊያ ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል። በተለይ የተሽከርካሪ አከራዮች ለማንኛውን ሰው መኪናቸው በሚሰጡበት ወቅት አስፈላጊውን ማስረጃ መዝግበው መያዝ እና ማጣራት እንዳለባቸው መረጃው ያመለክታል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
ጌትነት ተስፋማርያም