አዲስ አበባ፡- አገራት በኢትዮጵያ ላይ የቱሪዝም ጉዞ እገዳ እንዳያደርጉ የአገሪቱን ሰላም ማስጠበቅ እንደሚገባ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ትናንት በሐርመኒ ሆቴል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ እንደተገለጸው፤ በብዙ አገራት ላይ የቱሪዝም ጉዞ እገዳ የሚያደርጉ የቱሪስት ምንጭ የሆኑ አገራት እስካሁን ኢትዮጵያ ላይ አላደረጉም። የአገሪቱ የሰላም እጦት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ግን ኢትዮጵያንም የእገዳው አካል ልትሆን ትችላለች።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በአንዲት አገር ላይ የጉዞ እገዳ የሚደረገው ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ግጭት ሲኖር ነው። ሽብርተኝነትና ዘረፋ ሲበራከት አገራት የጉዞ እገዳ ያደርጋሉ። ኢትዮጵያ እስከአሁን በደህንነት የተሻለች አገር ናት። ዳሩ ግን እገዳ ከመደረጉ በፊት ቅድመ መከላከል ሊደረግ ይገባል። ለዚህም ሁሉም ኅብረተሰብ ሰላምን መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
መጭውን የገና እና የጥምቀት በዓል ምክንያት በማድረግ ብዙ የውጭ አገራት ቱሪስቶች እንደሚመጡ የገለጹት አቶ ስለሺ፤ በክልሎችና በአዲስ አበባ የፀጥታ የመረጃ ማዕከላት እየተከፈቱ እንደሆነ ተናግረዋል። የአገራት ኤምባሲዎች የጉዞ ክልከላ እንዳያወጡ እየተሰራ መሆኑንና እስከአሁንም ከአሥር ኤምባሲዎች ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
ለቱሪስቶች ደህንነት ሲባልም ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሥራት የመረጃ ማዕከል መዘጋጀቱንና የቱሪስቶችን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል 6168 የጥሪ ማዕከል ከኢትዮ ቴሌኮም ግዥ መፈጸሙን አቶ ስለሺ አስረድተዋል። ቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ባቀረቡት ጽሑፍ፤ ቱሪዝም ማለት የሰዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ማለት ስለሆነ ህልውናው ሙሉ በሙሉ በሰላም ላይ የተመሰረተ ነው። በአንዲት አገር ላይ ሰላም ከሌለ አገራት የቱሪዝም ጉዞ ካርታ ዝርዝር ያወጣሉ። እገዳ የተደረገባቸው አገሮችም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ውስጥ ይገባሉ።
‹‹የግብርና ምርቶችም ሆኑ የፋብሪካ ውጤቶች ገቢ የሚያስገኙት ቱሪስት ሲኖር ነው›› ያሉት አቶ ስለሺ፤ የቱሪዝም ዘርፉ ከተቀዛቀዘ ኢኮኖሚውን እንደሚጎዳ ገልጸው ኢትዮጵያን የሚገበኙ ሰዎች ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸሩ የተማሩና በዕድሜ የበሰሉ እንደሆኑና ሰላምን ተቀዳሚ ምርጫቸው እንደሚያደርጉ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በቱሪስቶች ላይ የደረሱ ወንጀሎች ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዙ እንደሆኑም የአቶ ስለሺ ጥናት ያመለክታል። በሌሎች አገራት ላይ እገዳ የተጣለው ሆን ተብሎ ቱሪስቶች ላይ ጉዳት ለማድረስ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የደረሱት ግን ለገንዘብ ጉጉት ተብሎ የተደረጉ ስርቆቶች ናቸው። የኮምውተርና የስልክ ስርቆቶችም የተደረጉ ሲሆን ልመናም አንዱ ችግር እንደሆነ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
ዋለልኝ አየለ