አዲስ አበባ፡- የአገሪቱን የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማትን ሳይንሳዊ፣ ዓለም አቀፋዊ እይታዎችን እና ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል በማድረግ እየተደራጀ መሆኑ ተገለፀ፡፡
‹‹የፀጥታ ተቋማት በፖለቲካ ሽግግር ውስጥ›› በሚል ርዕስ ደህንነትና የፀጥታ አካላት አሠራርና ሪፎርምን አስመልክቶ ትናንት በሃያት ሬጀንሲ በተካሄደው ውይይት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ድኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ እንደተናገሩት፤ የአገሪቱ የፀጥታ እና ደህንነት ተቋማት ሳይንሳዊ፥ ዓለም አቀፋዊ እይታዎችን እና ብሄራዊ ጥቅምን ማዕከል ባደረገ መልኩ እየተደራጁ ይገኛሉ፡፡
ቀደም ሲል በደህንነቱ ዘርፍ ችግሮች መኖራቸውን አማካሪው አስታውሰው፤ በተለይም የሙያዊ ብቃት ማነስ፤ የተዛበ የብሄራዊ ደህንነት ብያኔ፣ ተጠያቂነት አለመኖር፣ ለሥርዓቱ አገልጋይ መሆን፣ ደካማ የበጀት አጠቃቀምና የመሳሰሉ ህጸጾች ተጠቃሽ ሲሆኑ እነዚህን ችግሮች ማስተካከል ያስችል ዘንድ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
እንደ አቶ ተስፋሁን ገለፃ፤ ለድህንነት ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች እንዴትና መቼ ይሰበሰባል፣ እንዴት ይሰራጫል በሚለው ላይ በሰፊው ተሰርቷል።መከላከያ ዘመኑ የሚጠይቀውን አቅምና እውቀት ብሎም አደረጃጀት እንዲኖረው፣ የፍትህና ማረሚያ ቤት አስተዳደሮችም በተሻለ መንገድ ሥራቸውን እንዲያከናወኑ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።የአገሪቱ የደህንነት ጉዳይም ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተናበበ እንዲሆን ተደርጓል።የአገሪቱን ጥቅም የሚያስከብር የባሕር ኃይልና የሳይበር ጥቃትን የሚከላከል አደረጃጀት በሰፊው ተገንብቷል።በቀጣይም የኢትዮጵያን ጥቅም ማዕከል ባደረገ መልኩ በርካታ የአደረጃጀትና የስትራቴጂ ሥራዎች እንደሚተገበሩ ሚኒስትር ዴኤታው አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሠላምና ደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ዮናስ አዳዬ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ሠላምና ደህንነት በአንድ ስፍራ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ባህሪ የተላበሰ ነው።የደህንነት ጉዳይ ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ሆነ ከፋይናንስ ፖሊሲ ተለይቶ የሚታይ አይደለም።የአንድ አገር በጀትም ከደህንነት ተቋማት ጋር የሚናበብ ነው፡፡
የደህንነት ተቋማትን ሪፎርም በማድረግ ረገድም አስቸጋሪ ሁኔታዎች መኖራቸውን ዶክተር ዮናስ አመልክተው፤ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ያለመዳበር፣ በዘርፉ ላይ የሰለጠነ ባለሙያና በቂ ጥናት ያለመኖር፣ ለለውጥ ዝግጁ አለመሆንና ለውጥን መገዳደር፣ አገራዊ ዓላማ አንግቦ አለመንቀሳቀስ፣ ሃብት በአግባቡ አለመጠቀምና ተጠያቂነት አለመኖር ዋንኛ ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የቀድሞ የጦር ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናል ጀነራል ገብረፃድቃን ገብረተንሳይ በበኩላቸው፤ በሽግግር ወቅትም እነዚህ ተቋማት ሪፎርም መደረግ እንዳለባቸውና የአገር ሠላምና ደህንነት በዋናነት በስትራቴጂ ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።የደህንነት ተቋማት የሚመሰረቱት ለአንድን አገር ፖለቲካ በቀረቡና በዘርፉ እውቀት ባላቸው ሰዎች ስለሆነ ፖለቲካው በሥርዓትና በህግ እንዲዛወር በሚገባ ማሰብ እንደሚገባ አስገንዝብዋል።
የደህንነት ተቋማት የተለየ ባህሪ እንዳላቸው የሚናገሩት ሌተናል ጀነራል ገብረፃድቃን ሥራቸው የተወሳሰበ በመሆኑ በሚገባ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል። ጀኔራሉ አክለው እንደገለጹት በለውጥ ወቅት የደህንነት፤ መከላከያ እና ፖሊስ ኃይል ብቻ ሳይሆን የሲቪል ባለስልጣናት የፖሊሲ እውቀትና ጉዳይ አረዳዳቸው ካልተለወጠ የተወሰነ ለውጥ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የሪፎርም ዓላማውም አሠራሩ ስኬታማ እንዲሆንና ብቃት ባለው የሰው ኃይል ለመገንባት፣ ሃብት ቆጣቢ እንዲሆንም ጭምር ታሳቢ መደረግ አለበት። በተጨማሪም እነዚህ ተቋማት የዜጎች ደህንነትና ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ብሎም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሥር እንዲሰድና አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ዋነኛ ማጠንጠኛ መሆን ይጠበቅበታል።
በአደረጃጀት ውስጥ የተጠያቂነት ጉዳይም መኖር እንዳለበት ያመለከቱት ሌተናል ጀነራል ገብረፃድቃን፤ የሃብት አጠቃቀምና ለሚሰሩት ሥራ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።ግልጽነት ያለው አቅጣጫ መከተል እንደሚያስፈልግና ተቋማቱን በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባትም የአገሪቱን ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች በአግባቡ መተንተንና መተንበይ እንደሚገባ ተናግረዋል።ሙያዊና ብቃትና እውቀት ብሎም ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዕይታዎች ደግሞ የደህንነት ተቋማት ለውጥ እና ሪፎርም ሲደረግባቸው በቀዳሚነት ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
መሰል ተቋማት ሲገነቡም በአገር ጥቅም ዙርያ ዘረፈ ብዙ እይታና እውቀት ያካበቱ ባለሙያዎችን ያሳተፈ መሆን እንዳለበት የተናገሩት ሌተናል ጀነራል ገብረፃድቃን ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስቀድም ፖለሲ ዋንኛ መሰረት አድርጎ መውሰድና በአግባቡ ማስተዳደር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ቀደም ባሉት ዓመታት የነበረው የአገሪቱ የደህንነትና ፀጥታ አደረጃጀትና ተቋማት በበላይነት የሚመሩት ፖለቲካ ወገንተኝነት ባላቸው አካላት ስለነበር በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት የማጣት አዝማሚያ ይታይ ነበር።በአሁኑ ወቅት ግን ከፍተኛ የሆነ የሪፎርም ሥራ የተከናወነ በመሆኑ በቀጣይ አገሪቱን ወደፊት የሚያራምዱ ሳይንሳዊና ስትራቴጂካዊ ተግባራት በስፋት ይከናወናሉ ብለዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር