አዲስ አበባ፡- ባለፉት ስደስት ወራት ‹‹አንድ ብር ለአንድ ልብ›› በሚል የ6710 አጭር የጽሑፍ መልዕክት መላኪያ የሰበሰበው ገቢ ከጠበቀው አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል አስታወቀ።
የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሄለን በፍቃዱ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ማእከሉ ባለፉት ስድስት ወራት በ6710 የመልዕክት መላኪያ የሰበሰበው ገቢ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ቢሆንም በዚህ መንገድ ለመሰብሰብ ከታቀደው ከአንድ አራተኛ በታች ነው።
ከአርባ ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ በትንሹ አስር ሚሊዮን የሚሆነው ድጋፍ ቢሰጥ በስድስት ወር ውስጥ ከሐምሳ አስከ ስልሳ ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ በየወሩ ለመሰብሰብ ታስቦ እንደነበር ያስታወሱት ሜዲካል ዳይሬክተሯ ይሁንና በዚህ ስድስት ወር የተሰበሰበው የብር መጠን 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ገልፀዋል።
ለገቢው ዝቅተኛ መሆን ዋነኛ ምክንያት በማዕከሉ በኩል የፕሮሞሽን ስራዎች በሚገባ አለመሰራታቸው መሆኑንም ሜዲካል ዳይሬክተሯ የጠቀሱ ሲሆን ማዕከሉን የሚመለከቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ሲመጡም የፕሮሞሽን ስራውን የመርሳት አዝማሚያም ይታይ እንደነበር አመልክተዋል። ከዚህ በፊት ማዕከሉ ሲቋቋም ኅብረተሰቡ ባዋጣው የገንዘብ ድጋፍ እንደነበረም አስታውሰው፤ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡ ለጉዳዩ የሰጠው ክብደት አነስተኛ መሆንም በሚፈለገው ልክ ገንዘብ ለመሰብሰብ ሳይቻል መቅረቱንም አስታውቀዋል።
በማዕከሉ ሰባት ሺ የሚሆኑ ህፃናት የህክምና ወረፋ እየጠበቁ መሆኑንም ሜዲካል ዳይሬክተሯ ገልፀው፤ ለህፃናቱ ዘለቄታዊ መፍትሄ ካልመጣ ሁልግዜም ከልመና መላቀቅ እንደማይቻልም አስምረዋል። በተቀናጀ መልኩ እገዛው እንዲደረግም ኅብረተሰቡ፣ የሚመለከተው አካል፣ በውጪ ሀጋራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮ ጵያውያን በማዕከሉ ድረገፅ በመግባት ሊያግዙ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
‹‹ማዕከሉ ባለፈው አንድ ዓመት ሲቸገር የነበረበት አንዱ ጉዳይ የህዝብ ግንኙነት ክፍል አለመኖር›› ነው ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሯ፤ በዚህም ማዕከሉን በበቂ ሁኔታ የማስተዋወቅ ሥራ ባለመሰራቱ በተለይ ኅብረተሰቡ በሚፈለገው ልክ ለማዕከሉ ድጋፍ እንዳያደርግ የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅትም ማዕከሉ ባለሞያዎችን ያካተ ተና በተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች ላይ የሚገኙ በጎ ፍቃደኞችን ማስተባበር የሚችል ራሱን የቻለ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ማወቀሩን ሜዲካል ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል። ለማዕከሉ የሚደረገውን ድጋፍ የበለጠ እንዲጠናከርም አርቲስት መሰረት መብራቴ ከህዳር ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ የማእከሉ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር ሆና ማዕከሉን እንድታስተዋወቅ እውቅና እንደተሰጣትም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል እያስገነባ ላለው ግዙፍ ህንፃ ማስፈፀሚያ በዓመት ከ40 አስከ 60 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብ ድጋፍ የሚያስፈልገው መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ይህንኑ የገንዘብ መጠን ቢያገኝ ህንፃውን በማስጨረስ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ያለም ንም ችግር የልብ ህክምና አገልግሎቱን በተሟላ ሁኔታ ለመስጠትና በዓመት ለ1 ሺህ 500 ህሙማን ህክምናውን ማዳረስ እንደሚያስችለው ከማዕከሉ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
አስናቀ ፀጋዬ