አዲስ አበባ፤ ቻይና ትልቋ የኢትዮጵያ የንግ ድና የኢንቨስትመንት አጋር ሆና መቀጠሏን እና በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት 2020 በርካታ የቻይና ኢንቨስትመንቶችም በኢትዮጵያ እንደሚከናወኑ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂአን ትናንትና ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ መጪው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የኢትዮጵያ እና ቻይና የዲፕሎማቲክ ግንኙነት 50ኛ ዓመት የሚከበርበት ነው። ከዚህ ቀደም የነበሩ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካ ግንኙነቶችም በተሻለ መንገድ ይከናወናሉ። ቻይናም የኢትዮጵያ ትልቋ የንግድ አጋር እና የኢንቨስትመንት ምንጭ ሆና ትቀጥላለች።
እንደ አምባሳደር ታን ጂአን ገለጻ፣ በመጪዎቹ ጊዜያት ሰፊ ሥራዎች በሁለቱ አገራት መካከል ይከናወናሉ። ለአብነት የቻይና መንግሥት ለሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት የሚያደርገውን ድጋፍ በማጠናከር የ12 ኪሎ ሜትር ወንዝ ዳርቻ ልማቱን እስከ ግንቦት ወር ድረስ አጠናቆ ለማስረከብ ጥረት ያደርጋል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ለሚከፈተው ሰፊ የቀርከሃ ምርት ማዕከል የአዋጭነት ጥናት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ከጤና ዘርፉ ጋር በተያያዘ ደግሞ የወባ መከላከያ የአፍሪካ ማዕከል እና የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠሪያ ማዕከልን በአዲስ አበባ ለማቋቋም ቻይና አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች።
በቀጣይ ጊዜያት የሀገራቱ ግንኙነት የሚጠናከ ርባቸውን የተለያዩ መንገዶች ያነሱት አምባሳደር ታን ጂን በመጠናቀቅ ላይ ያለው የፈረንጆቹ 2019 ዓ.ም ደግሞ ሰፊ ሥራ የተከናወነበት መሆኑን አስታውሰዋል። በ2019 እ.አ.አ. አሥር ወራት ብቻ ከቻይና ለመጡ 147 የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶች ኢትዮጵያ ፍቃድ መስጠቷን እና ወደሥራ ማስገባቷን ገልጸዋል። በተለይ በጨርቃጨርቅ፣ ግንባታ እና በፋርማሲው ዘርፍ በርካታ ቻይናውያን ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እያደረጉ ይገኛል። በቅርቡ አንድ የዓለማችን ከፍተኛ የካልሲ አምራች ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ለመስራት እንቅስቃሴ ሊያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል። በርካታ የቻይና ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ከፍተው እንደሚሰማሩ እና ለዚህም ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ከጤፍ ምርት ማሻሻያ ጋር ተያይዞ በቻይናውያን የተሠሩ መሣሪያዎችም ጥቅም ላይ ስለሚውሉበት መንገድ ከኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት አምባሳደር ታን፤ ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የልማት ስራዎች ቻይና በቀጣይነትም ከጎኗ እንደምትቆም አረጋግጠዋል። በሌላ በኩል የዶክተር አብይ መንግሥት የአገሪቷን መረጋጋት እንደሚያመጡ ቻይና ሙሉ እምነት እንዳላት በመግለጽ የውጭ ሀገራትን ጣልቃ ገብነትን መቀነስ ካልተቻለ ግን ነገሮች ሊወሳሰቡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
ጌትነት ተስፋማርያም