አዲስ አበባ፡- በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በእምነት ተቋማት ላይ በደረሰው ቃጠሎ የወደሙ የእምነት ተቋማትን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ።
የሞጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የህዝብና ሚዲያ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መንግስቱ አለማየሁ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ባንኮች የባንክ ሒሳብ ተከፍቶ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ እየተሰራ ነው። ከባንክ ሒሳብ በተጨማሪም ደረሰኝ ተዘጋጅቶ ከኅብረተሰቡ ገንዘብ እየተሰባሰበ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎችም የመመዝገብ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማና በምሥራቅ ጎጃም ወረዳዎች ውስጥ ኅብረተሰቡን በማከለ መልኩ የድጋፍና የምክክር መድረኮች እየተከናወኑ መሆኑንና በሚሰባሰበው ገንዘብም የእምነት ተቋማቱ እና የንግድ ተቋማቱ እንደሚገነቡ አቶ መንግስቱ ተናግረዋል። በቀጣይም በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ መድረኮችን በማዘጋጀት የማሰባሰብ ሥራውን ለማስፋት በሂደት ላይ መሆኑንና ለዚህም አስተባባሪ ኮሚቴ መቋቋሙን አስረድተዋል።
ከገንዘብ ማሰባሰብ በተጨማሪ ለተጎጂ ወገኖች ህብረተሰቡ የሞራል ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፤ የአካባቢው ማህበረሰብ ጉዳት ከደረሰባቸው ወገኖች ጎን በመሆን ጉዳቱን በጋራ እየተካፈለ መሆኑን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
ዋለልኝ አየለ