ማረሚያ ቤቶቻችን ወንጀለኞችን ከማስተማር ይልቅ ኢ-ሰብዓዊ በሆነ አያያዝና ድብደባ የታራሚዎችን አካል በማጉደል ህገ-መንግስቱ በማይፈቅደው መልኩ ወንጀል ሲፈፅሙ እንደነበር የድርጊቱ ሰለባዎች ዛሬም ድረስ እማኝ ናቸው፡፡ የተቋቋሙበት ዋና አላማ ወንጀለኞችን በማስተማር የፀፀት ስሜት ተሰምቷቸው ታንጸው እንዲወጡ ማድረግ ቢሆንም በተቃራኒው ሲያሰቃዩና ሰብዓዊ ክብራቸው ሲገፈፉ ቆይተዋል፡፡
በህገ-መንግስታችን አንቀጽ 21(1) “በጥበቃ ስር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎችን የመያዝ መብት አላቸው”፤እንዲሁም 21(2) “ከትዳር አጋሮቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሀይማኖት አባቶቻቸው እና ከህግ አማካሪያቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኙአቸው እድል የማግኘት መብት አላቸው” በሚል ተደንግጓል፡፡
ነገር ግን ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የታራሚ ዘመድ መጥቶ መጠየቅ አይችልም። ከማንኛውም ሀይማኖታዊና ማህበራዊ ተቋም ጋር እንዲገናኙ አይፈቀድም። ይባስ ብለው በህግ አስከባሪዎች መገረፍ፣ ምግብ መከልከልና የተፈጥሮ ህግን በጣሰ መልኩ እንዳይተኙና እንዳይፀዳዱ ማድረግ የተለመደ የማረሚያ ቤቶቻችን ተግባሮች ናቸው፡፡ ማረሚያ ቤት ተብለው ተቋቁመው ተግባራቸው ግን የስቃይ ቤት በመሆኑ ለብዙ ሰዎች የእግር እሳት ሆነዋል፡፡
ይህን ድርጊት በሕግ አግባብ ታሪክ ማድረግ ይገባል ያለው የለውጥ አመራሩ ከትናንት በስቲያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡ በወቅቱ ከህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅራቢነት የፀደቀው ይህ አዋጅ ከፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግና ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ጋር እንዲሁም ከህዝብ ክንፍ ጋር በቂ ውይይት ተደርጎበት ነው፡፡ አዋጁም አለም አቀፉን የሰብዓዊ መብቶች በተሻለ ሁኔታ ለመተግበር ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡
አዋጁ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት እና ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው የወጡ ህጎች እንዲሁም ሀገሪቱ በፊርማ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መሰረት ታራሚዎችን በመጠበቅ እና በማነፅ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ የሚያስችል ከመሆኑ ባለፈ ከላይ ያነሳናቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች በመሰረታዊነት የሚከለክል ጭምር ነው፡፡
በመሆኑም አዋጁ የማረሚያ ቤቶችን አደረጃጀት የተሻለ ለማድረግ ፣የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት ከተልዕኳቸው ጋር የሚመጣጠን ‹የማረሚያ ቤት ፖሊስ› የሚል ስያሜ አግኝተው ደረጃውን እና ኃላፊነቱን የሚገልፅ ማዕረግ እና ምልክት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው፡፡
በተጨማሪም ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች ሰብአዊ መብት በማክበር እንዲሁም የታራሚዎች ግላዊ ሁኔታ በሚጠይቀው የፍርድ አፈጻጸም እና እርማት ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ እውቀትና ክህሎትን አዳብረው ከህብረተሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበትን ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችል አስገዳጅ ሆኖ ሊተገበር ይገባል፡፡ በመሆኑም የህግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ከጥፋታቸው ታርመው እንዲወጡ በማድረግ ሰላማዊ ህይወት እንዲኖሩ ለማድረግ አዋጁ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡
የህግ ታራሚዎች በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸውና አንዳንድ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መብቶቻቸው ለጊዜው ከሚገደቡ በስተቀር ሰብአዊ ክብራቸውና ሌሎች መብቶቻቸው የህግ ጥበቃ ያላቸው መሆኑ ሊሠመርበት የሚገባ ነው፡፡
የህግ ታራሚዎች ከመታሰራቸው በፊት ለሀገራቸው አገልግሎት ያበረከቱ፣ በማረሚያ ቤት ሆነውና ከማረሚያ ቤት ከተፈቱ በኋላም ወደቀደመ ክብራቸው በመመለስ፤ እንዲሁም ወንጀል መፈጸማቸው ተረጋግጦ የተቀጡትም ቢሆኑም ከጥፋታቸው ታርመው ለሀገራቸው የራሳቸውን አስተዋጽኦ የማበርከት ዕድሉና አቅሙ ያላቸውም ሊሆኑ እንደሚችሉ ሊታሰብ ይገባል፡፡
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ለታሠሩ ሰዎች ሰብዓዊ መብቶች መከበርና ተግባራዊነት ሁሉም ባለድርሻ አካል ግዴታውን ሊወጣ ይገባል፡፡ ይህን በማድረግ የህግ ታራሚዎችን ሰብዓዊ መብትና ክብርን በፅኑ መሰረት ላይ መጣል ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2012