በሃገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች በተለይም በዋና ዋና ከተሞች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ ይገኛል ።አሁን ላይ ከምግብ እስከ መድኃኒት ያልጨመረ ነገርን ማግኘት ከባድ ነው።መቶ ሃምሳ ግራም የማይሞላ ዳቦ ሦስት ብር መግዛትም እየተለመደ መጥቷል ።ምክንያቱም ለምን የሚል ገዥ ስለሌለ።
በተዓምር ካልሆነ በስተቀር ከምጣዱ ላይ እንዴት እንደተላቀቀ ለማወቅ የሚያዳግት እንጀራንም ሰባት አልያም ስምንት ብር መግዛት ዋል አደር ያለ ሆኗል።እርሱም ባእድ ነገር ያልተቀላቀለበት ከሆነ ጥሩ ነው።የሥጋ ዋጋማ የማይቀመስ ከመሆኑ የተነሳ ለብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን የቅንጦት ምግብ እየሆነ ነው።
ይህን በመሰለው የሸቀጦች ዋጋ መናር ሳቢያ በህብረተሰቡ ላይ ለተፈጠረው የኑሮ ውድነት በርካታ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ቢሆንም ምክንያት አልባ የዋጋ ጭማሬ የሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎች መበራከታቸው ግን ዋናው ነው።
በዚህ ስነ ምግባር የጎደለው የንግድ እንቅስቃሴ ያልተገባ የኑሮ ውድነትን እየፈጠረ ብዙሀኑንም እያማረሩ ይገኛሉ። “መንግስት በህገ ወጦች ላይ ተገቢውን እርምጃ እየወሰደ አይደለም” የሚል ከፍተኛ ቅሬታና ወቀሳ ህብረተሰቡ እንዲሰነዝር እያደረገ ነው።
መንግስት በበኩሉ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ የእርምት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ሲገልጽ ይሰማል።ለአብነትም ከሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች የባሰ የኑሮ ውድነቱ እየከፋ በመጣበት በአዲስ አበባ ከተማ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ችግሩን አባብሰዋል ያላቸውን ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ መስመር ለማምጣት፣ ፈቃደኛ ያልሆኑት ላይ ደግሞ ግብረ ኃይል በማቋቋም እርምጃ መውሰዱም በተደጋጋሚ ይገለጻል ።
አሁን ደግሞ በግብይት ወቅት በመስፈሪያ መሳሪያዎች አማካኝነት የሚፈጸመውን ቅሸባ ለመከላከል ባለፉት አራት ወራት ሰባት ሺ 500 የመስፈሪያ መሳሪያዎችን በመፈተሽ በ186 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማሸግ ለአራት ሺ 527ቱ ደግሞ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውቋል።
ይህ የቢሮው እርምጃ ይበል የሚያሰኝና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ህገ ወጦችንም አደብ የሚያስገዛ በመስፈሪያ ሚዛን ጉድለት ተደራራቢ ችግር ውስጥ የገባውንም ሸማች እፎይ የሚያሰኝ ተግባር ነው።
ከቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በመዲናዋ ከሚስተዋለው የኑሮ ውድነትና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባሻገር ሸማቹ እንደ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ስጋና ዳቦ የመሳሰሉትን ሲገዛ ለከፈለበት ዋጋ በትክክለኛው የመስፈሪያ መሳሪያ ተመዝኖ አይሰጠውም ፤ በዚህ ሁኔታ የሚፈጸመው ቅሸባ ከፍተኛ በመሆኑ ቢሮው ባለፉት አራት ወራት ችግሩን ለመከላከል በሰባት ሺ 500 የመስፈሪያ መሳሪያዎች ላይ ፍተሻ ማድረጉን ነው። ይህ ደግሞ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር ነው።
ቢሮው ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም በመዲናዋ በስፋት በዳቦ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ስጋ ቤቶች ላይ በቴክኖሎጂ የዘመኑ ዲጂታል ሚዛኖችን በጀት አመቱ መጨረሻ በግብይት ስርዓት ላይ ተግባራዊ አደርጋለሁም ብሏል።
ይህ እርምጃ የሚበረታታና የሚያስመሰግነው ቢሆንም ዋነኛው የችግሩ ሰለባ የሆነው ህብረተሰቡ ግን የበኩሉን መወጣት በሚዛን ተጭበርብሬያለሁ ብሎ ሲጠራጠር ለሚመለከተው አካል ማመልከትና እርምጃ ማስወሰድ እንዲሁም ከዋጋ በላይ የተጋነነ ጭማሪ ሲጠየቅ አልገዛም ብሎ መወሰንን መልመድ ይኖርበታል።
ይህ ሁኔታ ለእኛ አገር አዲስ ቢሆንም በሌሎች የዓለም አገራት ግን የተለመደ ነው። አንድ ኩባንያ ወይም የንግድ ድርጅት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርግበት ወቅት ገዥው በአንድነት ሆኖ የመቃወም አልገዛም የማለትና ሌሎችም እንዳይገዙ የማድረግ ልምድ አለ። ይህ እንደ እኛ አገር የግል ጥቅማቸውን ብቻ ለሚያስቀድሙ ነጋዴዎች ጥሩ መላ በመሆኑ ብንቀስመው ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አያደርገንም።
የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን በአዋጅ ከተቋቋመባቸው ዋና ዋና አላማዎች መካከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማጎልበት የገበያ ግልጽነትን በማሳደግ ጸረ – ውድድር የሆኑ የንግድ አሰራሮችንና ተገቢ ያልሆኑና አሳሳች የንግድ ተግባራትን በመከላከልና ፍትሃዊ ውሳኔ በመስጠት የሸማቹንና የንግዱን ማህበረሰብ መብትና ጥቅም ማረጋገጥ እንደመሆኑ እሱም ስራውንና ሀላፊነቱን በአግባቡ ይወጣ እንላለን።
የሸማቹን ችግር ይፈታሉ በተመጣጣኝ ዋጋ ሸቀጦችን ያቀርባሉ ተብለው በመንግስት ታምኖባቸው በየአካባቢው የተቋቋሙ የሸማች ማህበራትም ይህንን የኑሮ ውድነት በማረጋጋት ኃላፊነት አለባቸው። ሥለሆነም የኑሮ ውድነቱን ሆነ የሚዛን ማጭበርበር ለመቀነስ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።አስተዳደሩ የወሰደው እርምጃም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2012