ዛሬ ዛሬ የቴክኖሎጂና የዕውቀት መስፋፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የሰው ልጅ ለእያንዳንዱ ሥራ ቅልጥፍናና ውጤታማነት ቴክኖሎጂን መጠቀም መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ታዲያ በዚህ ፀጋ የታደሉ የዓለም ክፍሎች በዘመናዊ የሥልጣኔ ደረጃ ገስግሰው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች በሚተርፉበት በአሁነ ወቅት ኢትዮጵያ ዛሬም ከባህላዊ አስተራረስ መላቀቅ አልቻለችም። ራሷን መግባ ለሌሎች መትረፍ ተስኗታል።
በዚህም ህብረተሰቡ ኑሮው ከመሻሻል ይልቅ፤ መሠረታዊ የሆኑና ዕለታዊ ፍላጎቶቹን እንኳ ማሟላት እየተሳነው ይገኛል። ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ምቹ የአየር ንብረት ተጠቅማ ህዝቦቿን ከማጥገብ ባለፈ ለሌሎች መትረፍ እንድትችል በሳይንሳዊ እውቀት የተደገፈ የግብርና ልማት ማካሄድ ቢኖርባትም ዛሬም በበሬ ከማረስ መላቀቅ አለመቻሏ ያስቆጫል። እስከ አሁን የዘርፉ ውጤታማነት የአገር ውስጥ ፍላጎትን ካለማርካቱ ባሻገር፤ ቀድሞ የነበረ ከወጪ ምርት ሽያጭ የሚገኘው ገቢ መጓዳል እና የአቅርቦት አለመጨመር የዘመኑ ራስ ምታት ሆኗል።
ለኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት የሆነውና 90 በመቶ የወጪ ምርትን የሚሸፍነው ግብርና በ21ኛው ክፍለ ዘመን የዘልማድ አስተራረስን የሙጥኝ ማለቱ የወጪ ንግዱ እንዳያድግ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ ዋነኛው ነው። የወጪ ንግዱ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም መሰረት 14 ቢሊዮን መድረስ ቢኖርበትም፤ ጭራሽ ማሽቆልቆሉ ይታወቃል።
በ2003 ዓ.ም ከነበረበት አራት ቢሊዮን ዶላር ባለፈው በጀት ዓመት እጅግ ቀንሶ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ለዚህም ዋነኛውና ቁልፍ ችግሩ ምርት አለመጨመሩ ሲሆን፤ በተቃራኒው የላኪዎች ቁጥርም እጅግ እያሻቀበ ይገኛል። ለአብነትም 350 ሺ ቶን ያህል የሰሊጥ የወጪ ንግድ በሃያ ላኪዎች ብቻ ይፈፀም የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን በሰሊጥ ላኪነት ብቻ ተመዝግበው ያሉት የላኪዎች ቁጥር ከአንድ ሺ 300 በላይ ሆነዋል።
ይህ ማለት ሥራው “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንደሚባለው፤ ምርት ሳይጨምር አገሪቷ ያጋጠማትን የምርት እጥረት መቅረፍ ቀዳሚው ጉዳይ አድርጎ ዘመናዊ የግብርና ዘዴ ተግባራዊ ማድረግ ላይ መረባረብ የሚገባው ባለሀብት ፊቱን ያለችዋን ምርት መቀራመት ላይ አዙሯል። ይህ አካሄድ መስተካከል አለበት። ባለሀብቱ አምራች የሚሆንበት መንገድም ማመቻቸት ያስፈልጋል።
ባለሀብቶች ብቻ አይደሉም። ግብርናው እንዳይዘምንና ምርትና ምርታማነት እንዳይጨምር አንቀው የያዙትን ችግሮች ለመፍታት በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራንና መንግሥት የማይተካ ሚና አላቸው። ስለሆነም ዘርፉን ከመምራት ጀምሮ እስከታች ያለውን የግብርና ባለሙያ በማብቃት፣ በመደገፍና በማገዙ በኩል በሚገባውና በሚፈለገው ደረጃ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።
ይሁንና አሁን ባለንበት ዘመን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በጥራትም ሆነ በብዛት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ጉዳይ እጅግ ወሳኝና አማራጭ የሌለው ነው። ተወዳዳሪነትንና ተመራጭነትን ማምጣት ካልተቻለ አሁን ያለው ችግር የምርት መጠን አለማደግ በዚሁ ከቀጠለ ለገቢ ንግድ ምርትን ወደ አገር ውስጥ ማስገቢያ የውጭ ምንዛሬ ከመጥፋቱ ባሻገር የአገሪቷ አጠቃላይ ኢኮኖሚ አደጋ ላይ የሚወድቅ በመሆኑ፤ ከወዲሁ መንግሥትም ሆነ ባለሀብቱ እንዲሁም የዘርፉ ተመራማሪዎች ለምርት ዕድገት ሰፊ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል።
በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ግብርና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይደር የሚባል ጉዳይ አይደለም። ዘርፉን በሳይንሳዊ ዕውቀት በመምራት አገሪቷ፤ እስካሁን ባቀደችውና ወደ ፊትም በምታቀደው ልክ ምርትና ምርታማነት አድጎ በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ መሆን እንዲቻል ዘመናዊ ግብርናን ተግባራዊ ማድረግ፤ የነበረውን በበሬ የማረስ ልምድ በመቀነስ ኩታ ገጠም የግብርና ዘዴዎችን በማስፋፋት ትራክተርን የመሳሰሉ ዘመናዊ ከፍተኛ የሰው ጉልበትና ጊዜ የማይጠይቁ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምን የግድ ይላል። በዚህም ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል። ስለሆነም አሁን ያለውን የምርት መጠን እየተቀራመቱ በወጪ ንግድ ከመሰማራት አምራች ሆኖ ምርታማነትን ማሳደግ ላይም ሊሠራ ይገባል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2012