
እኩለ ቀን ነው ፤ አማራጭ ስለሌለኝ አናት በምትበሳ ፀሐይ መሀል አንድ ወዳጄን ለማግኘት እየተጓዝኩ ነው። እኔ የምለው? ለጸሐይ ቀርበን ነው ወይስ እሷ ወደ እኛ ቀርባ ? ሀይሏ ከመክበዱ የተነሳ ሰውነት የሚያዝል ፣ሃሳብ የሚያስረሳ ነው ብል ማጋነን አይሆንም ብቻ ይህን ሁሉ ውርጅብኝ ተቋቁሜ አይደርሱ የለ የቀጠርኩትን ሰው ወደማገኝበት ቦታ ደረስኩ። በአካባቢው ወደሚገኝ ካፌ ገብቼ አረፍ አልኩ። ብዙም ሳልቆይ አንዲት መልከ መልካም ወጣት ወደ እኔ ቀርባ ምን እንደምፈልግ ጠየቀችኝ። ብዙም ማሰብ ሳያስፈልገኝ ‹‹ውሃ ታመጭልኝ›› እርሷም ቃጠሎዬ ገብቷታል መሰል ለዛውም የቀዘቀዘ አቀረበችልኝ። ጠጣሁት፤ ነብሴ ተመለሰች።
ዋናው ነገሬ እንኳን ስለ ፀሐይዋ ማውጋት አልነበረም። እግረ መንገዴን ያስተዋልኩትን እንዲሁ ለመንገር ያክል እንጂ! የዛሬው ቁምነገሬ ይህን ይመስላል… ለረጅም ጊዜ ተለያይተን ከነበረው ወዳጄ ጋር በቀጠሮ ሰዓት ተገናኝተናል። ከአጭር ሰላምታ በኋላም ሊያማክረኝ ወደ መጣበት ጉዳይ … እንዲያው ሊያማክረኝ አልኩ እንጂ ያጋጠመውን ሊነግረኝ ወደፈለገው ሃሳብ በቀጥታ ገብተን መጨዋወት ጀመርን፡፡
‹‹እኔ የምልህ›› ብሎ ወጉን ሲጀምር በአይኔ ተከትልኩት፤ ቀጠለና ‹‹ውሸት ለካ የእውነት ድምቀቷ ናት!›› የሚል ጭውውቱን ሲጀምር፤ በተዝናኖት ከተቀመጥኩበት እግሬን፣ እjyንና ቀልቤን እየሰበሰብኩ የወዳጄ አፍ አቅራቢያ ተጠጋሁ፤ ቀጠል አድርጎ ‹‹ባለፈው የሽርክና ስራ ለመስራት አብሬያቸው ጥምረት የመሰረትነውን ልጆች ታወቃቸዋለህ አይደል?›› ሲል ጥያቄውን አስከተለ። አንገቴን በአዎንታ እየነቀነኩ እንደማውቃቸው ገለፅኩለት። ‹‹ታዲያ ከሶስታችን መካከል አንዱ ይህንን የስራ ጥምረት አልወደደው ነበር›› በማለት በዚህም ምክንያት ሊበትናቸው ፣ ጠቅላላ የስራ ግንኙነታቸውን ሊያጠፋው ያላደረው ነገር ያልፈነቀለው ድንጋይ እንዳልነበር አረዳኝ…።
‹‹ይህንን ሰይጣናዊ ምግባሩን ለመከወን ያልተፈጠረ የሃሰት ስንቁን ይዞ ወጣ›› ወጉን እየሰማሁ መሆኔን ለማስረዳት ‹‹እሺ›› ብዬ ቀጣዩን በጉጉት እየጠበኩ… ‹‹የማህበራችንን ስም ለማጥፋት ዕቃ የምናቀርብላቸውም የተለያዩ ድርጅቶች እና ከዚህ በኋላ ይሄዳሉ ብሎ ወደሚያስባቸው ድርጅቶች ጋር በመሄድ የሚሰሩት እንዲያ ነው… እንዲህ ነው … የእነሱ ስራ ችግር አለበት›› እያለ ብቻ ብዙ ስማቸውን እንዳጠፋ በንዴት አጫወተኝ። በዚህ ሁሉ የልጁን ወሬ የሚሰሙ ድርጅቶች ለማጣራት በሚል ወደ ምርት ማምረቻችን መምጣታቸውን ገለፀልኝ። ታዲያ የሰሙት እና ያዩት ነገር የተቃረነ በመሆኑ ከዚህ በፊት አይተውት በማያውቁት ሁኔታ በደንበኛ ብዛት እንደተጨናነቁ ነገረኝ። ታዘው የማያውቁትን ያክል ከአቅማችን በላይ ትዕዛዝ መቀበላቸውን በሃሴት ነገረኝ። ብቻ ምን አለፋችሁ ሊያዋርዳቸው አስቦ ቆንጆ ማስታወቂያ ሰርቶ እንዳከበራቸው ነገረኝ። የሚገርመው በቅርቡ መኪና ሊገዙ ነው ! በውሸት ሊያጠፋቸው አስቦ መጥቶ ይልቁን አበለጸጋቸው፡፡
በዚህ የወዳጄ ጨዋታ መሃል ነው ያነበብኩትን የማስቀመጥበትን አድባር ቦርሳዬን (ፎልደር) ውስጥ ያለ አንድ ጽሑፍ ትዝ ያለኝ።የህዝብ ስነ ቃሎችን በማደራጀት እንደመማሪያ የሚያቀርብ “ተረት ተረት” በሚል ስሙ የሚጠራው የማህበራዊ የትስስር ገጽ ያገኘሁትን ነው፤ አወጣሁት፤ ተረቱ ሳነበው ወዳጄ ከነገረኝ ጉዳይ ጋር ተዛምዶ አየሁት ፤ ስነ ቃሉ እንዲህ ነው… እሳት፣ ውሃ፣ እውነትና ሃሰት ጓደኞች ነበሩ።ነገር ግን ሃሰት በዚህ ጥምረት ደስተኛ ስላልነበረ አንድነታቸውን ማበላሸት ፈልጎ እንዲህ አለ “ለምን ወደ አንድ ስፍራ ተጉዘን እያንዳንዳችን የራሳችንን ግዛት አንመሰርትም? ስለዚህ ተነስተን አብረን እንጓዝ፡፡”
ሁሉም በሃሳቡ ተስማምተው ሲሄዱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሀሰት ወደ ውሃ ጠጋ ብሎ “እሳት ሣሩን፣ ደኑንና ቁጥቋጦውን የሚያቃጥል ቀንደኛ ጠላታችን ስለሆነ ለምንድነው ከእርሱ ጋር ግዛት ፍለጋ የምንሄደው?” አለው።ውሃም “ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አለ።ሃሰትም ቀበል አድርጎ “ልንገድለው እንደሚገባ ግልፅ ነው።እሳትን የማጥፋት ብቸኛ ኃይል ያለህ ደግሞ አንተ ነህ።እናም ቁጭ ሲል ጠብቀህ እላዩ ላይ ራስህን በመርጨት አጥፋው፡፡” አለው።ውሃም “ራሴን መሬቱ ላይ ከረጨሁ ተመልሼ ውሃ መሆን አልችልም፡፡” አለ፡፡
ሀሰትም “ችግር የለውም፤ ተረጭተህ እንዳትበታተን የተወሰኑ ድንጋዮች በዙሪያህ አኖርና በኋላ እሰበስብሃለሁ።” አለው።በዚህ ጊዜ ያልጠረጠረው እሳት መጥቶ ቁጭ ሲል ውሃው አንድ ጊዜ በላዩ ላይ ሲረጭ ሃሰት ድንጋዮች ዙሪያውን አድርጎ ውሃውን ከሰበሰበውና እሳትን ካስወገዱ በኋላ አብረው መጓዝ ጀመሩ።ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሃሰት ውሃውን “ለምን እዚህ ገደል አፋፍ ላይ ቁጭ ብለህ በተፈጥሮ ውበት አትዝናናም?” አለው፡፡
ውሃም አፋፉ ላይ ቁጭ ሲል ሃሰት ቀስ ብሎ ተነስቶ ውሃ የተቀመጠባቸውን ድንጋዮች ከስሩ ሲለቅማቸው ውሃው በመፍሰስ ተበታትኖ ጠፋ።በመጨረሻም ሃሰት እውነትን ማጥፋት ነበረበትና ወደ አንድ ትልቅ ተራራ በተቃረቡ ጊዜ ሃሰት እውነትን ከተራራው ግርጌ ቁጭ በል ብሎት ከተራራው አናት ላይ ትልቅ አለት ቁልቁል በመልቀቅ እውነትን ሊጨፈልቀው ሲል እውነት ቀልጠፍ ብሎ ማምለጥ በመቻሉ አለቱ ተንከባሎ ሲፈረካከስ ከውስጡ አልማዝ፣ ወርቅና ልዩ ልዩ የከበሩ ማዕድናት ወጡ።ሃሰትም የእውነትን አስከሬን ሊመለከት በመጣ ጊዜ እነዚህን ሁሉ የከበሩ ድንጋዮችን አየ፡፡
እናም “እነዚህ ሁሉ ከየት መጡ?” ብሎ ጠየቀ። እውነትም “ እላዬ ላይ እንዲወድቅ ከላከው አለት ነው የወጡት፡፡” አለው።በዚህ ጊዜ ሃሰት “አሁን ደግሞ እኔ ከተራራው ግርጌ ልቀመጥና አንተ አለቱን በላዬ ላይ ልቀቅብኝ፡፡” አለው፡፡
እናም እውነት ወደ ተራራው ጫፍ ወጥቶ ትልቅ አለት ወደታች በለቀቀ ጊዜ የሃሰት አናት ላይ አርፎ ጨፈላልቆ ገደለው፡፡
አየህ ወዳጄ !ምን እንኳ ሃሰት ቀን የወጣላት፣ የአሸነፈች፣ የተሳካላት ብትመስልም ለጊዜው የተወሰነ ጥፋት ታደርሳለች እንጂ እውነት አትጠፋም። ይልቅ እውነት በሃሰት የጥፋት መሳሪያ ትለመልማለች ብሎም የመበልጸጊያ መንገዶች ከሃሰት ታገኛለች።
ይህ የማህበረሰብ ስነ ቃል ቀድሞ ከወዳጄ ጋር ካነሳሁት ጉዳይ ጋር እንዴት ይገናኛል? ብለህ ከጠየከኝ፤ ስነ ቃሉም ሆነ ገጠመኜ የሚያሳየው እውነት ፈተና ቢገጥመውም በመጨረሻ አሸናፊ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ እነግርሀለሁ። ሰላም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2012
አብርሃም ተወልደ