የአካል ጉዳቷ እየተፈታተናትም ቢሆን ተምራ ለውጤት በቅታለች፡፡ በአካውንቲንግ ዲፕሎማ፣ በማኔጅመንት ዲግሪዋን ይዛ በሙያዋ ወገንና አገሯን እያገለገለች ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ጽህፈት ቤት ከባለሙያነት እስከ ኃላፊነት ደረጃ ተመድባ ሠርታለች፡፡ አሁን ደግሞ በቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 15 ወሳኝ ሁነቶች የሥራ ሂደት አስተባባሪ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያ ሴት አካልጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆንም ትሠራለች፡፡ የዛሬዋ የ”ህይወት እንዲህ ናት” አምድ እንግዳችን ወይዘሪት ዘነበች ጌታነህ፡፡ ከእሷ ጋር የነበረንን ቆይታ እነሆ ለንባብ አልን፡፡
ልጅነት
በትክክል የተወለደችበትን ዓመተ ምህረት አታውቀውም። የተወለደችው ገጠራማ አካባቢ በመሆኑ የልደት ቀኗን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላገኘችም። ትውልዷ ጎሃጺዮን አካባቢ ፍልቅልቅ ተብላ በምትጠራ ስፍራ ነው። ያደገችው ደግሞ ደጋ ቦርሱ በተባለች የገጠር መንደር ውስጥ። ቤተሰቦቿ ከአካባቢው የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው በእንክብካቤ ማደጓን ትናገራለች።
አባቷ በአካባቢው የተከበሩ፣ተደማጭ እንዲ ሁም የተጣላን አስታራቂ ሽማግሌ ናቸው። በቤተሰ ባቸውም ተወዳጅ ደስተኛ ቤተሰብ የሚመሩ ናቸው። ልጆችም የቤተሰባቸው ነጸብራቅ ናቸውና ሁሌም በደስታ ያሳልፋሉ። አንድ ቀን ግን ቤት ውስጥ የተከሰተው ነገር ሁሉንም በጠበጣቸው። ልጃቸው ባልተጠበቀ ሁኔታ አካል ጉዳተኛ ሆነች። ምክንያቱ ሲጠና ሕፃኗ ከታላቅ እህቷ እጅ ላይ ወድቃ ነበር። ሕፃኗ የወደቀችባት እህት ደግሞ ለቤተሰብ አልተናገ ረችም። ህክምና ምስላልተደረገላት በተኛችበት የአልጋ ቁራኛ ሆነች።
በቤት ውስጥ እየቦረቀች ለቤተሰቡ የደስታ ምንጭ የነበረችው ልጅ ጨዋታ ተቋረጠ። አባትም እጅግ አዘኑ። ‹‹ለእኔ የመጣ ቅጣት ነው። አምላኬን የሆነ ነገር በድየዋለሁ። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ልጅ እንዲኖረኝ አልፈልግም›› አሉናም መኝታ ለይተው መኖርም ጀመሩ። ስቃያቸው ግን በዚህ አላበቃም። መቋቋም አቃታቸውና ህይወታቸውን ቀጠፈው።
እናት ደግሞ ሁሉን ነገር ያጣሁባት ናትና ለማንም አልሰጥም ብለው እስከ ስድስት ዓመቷ ተንከባከቧት። ከዚያም ስቃይዋን ላለማየትና የተሻለ ዕድል እንዲኖራት ለማድረግ እህታቸው መካን ነበረችና ወደ አክስቷ ዘንድ ወሰዷት። በእርግጥ በቋሚነት አክስቷ ቤት አልኖረችም። “ ምቹ ሁኔታዎች እንዲኖረኝ በማሰብ አክስቴ በተለያዩ የአዳሪ ቤቶች እንድኖር አድርጋለች። የአክስቴ እገዛ ሳይርቀኝ።” ትላለች።
ዘነበች እስከ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ድረስ ፈጣን ፣ ለጎረቤት የምትታዘዝና ሁሉም ሰው የሚመርቃት ልጅ ነበረች። ሳቂታና ጣፋጭ አንደበት ያላት እንደነበረች ታስታውሳለች። በዚያው ልክ ደግሞ ረባሽና ተደባዳቢም ነበረች። በተለይ የሦስት ዓመት ሕፃን እያለች እህቷን ተከትላ ትምህርት ቤት በመሄድ የተማሪዎችን እስክሪብቶ ትቀማ እንደነበር አትረሳውም። በዚህም ቤተሰብ ድረስ አማላጅ ይመጣ ነበር። የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ብዙ ጊዜ አማላጅ በመሆን ወላጆች እንዳይሰሙ አድርገው በአንድ እስክሪብቶ 10 ሳንቲም በመክፈል ይሸኙ እንደነበርም ታስታውሳለች።
ዘነበች አካል ጉዳተኛ ብትሆንም የምትፈልገውን ከማድረግ ወደኋላ የምትል አልነበረችም። ለአካል ጉዳቷ የሚመጥን ጨዋታ ተጫውታ ነው ያደገችው። በተለይም ዕቃ ዕቃ መጫወትና ሙሽራ መሆን በጣም ያስደስታት ነበር። በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ደግሞ የተሟላ መጫወቻ በመኖሩ ብዙ ዓይነት ጨዋታዎችን ተጫውታለች። በተለይ የምታስታውሰው ሞግዚቶቻቸው ዞር ሲሉ እንጀራ እየሰረቁ እንግዳ የሚጫወቱትን ነው።
ዘነበች የተወለደችበት ስፍራ ተራራማና ስርጥ የበዛበት ቦታ ቢሆንም እርሷ በእዚያ አለማሳለፏ ያስደስታታል። እንደውም ‹‹በእዚያ መንደር ውስጥ ብኖር ኖሮ ህይወቴ መቃብር ውስጥ ይሆን ነበር። ተስፋና ዛሬ ላይ መድረስም ይናፍቁኝ ነበር›› ትላለች ወደኋላ የነበረችበትን ሁኔታ ስታስታውስ።
ሌላው የዘነበች ዕድለኝነት በአክስቷ ቤት ማደጓ ሲሆን፤ በእነርሱ ጊዜ አዋቂ ቤት ከመጣ ሁሉም ልጅ ወደ ጓዳ ይገባል። ዘነበች ግን ከዚያ ይልቅ ሙሉነት እንዲሰማት ለማድረግ ከአዋቂዎች ጋር እንድትጫወት ይፈቀድላታል። አካል ጉዳተኛ ልጅ እንዳለኝ ሁሉም ይወቀው በማለት እንዳትደበቅ ትደረጋለች።
ይህ ደግሞ በራሷ የምትተማመን አንድትሆን አድርጓታል። እናም የአክስቷ ቤት ለእርሷ ትምህርት ቤት፤ እንደ ልጅ የተጫወተችበት፣ ነፃነት ያገኘችበት ሆኖላታል። ይሄም ጥንካሬዋ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር ስትገባ ጎለበተ እንጂ አልቀነሰምና ሙሉ ሰው አድርጎ ሠርቷታል። እናም ልጅነቴ ለዛሬ ሙሉነቴ መሰረት ነበር ትላለች።
ወይዘሪት ዘነበች በልጅነቷ የምተመኘው መጀመሪያ ጋዜጠኛ መሆን፤ ይህ ካልተሳካ ደግሞ አርቲስት መሆንን ታስባለች። ግን ሁለቱም አልተሳካላትም። ምክንያቱም ተንቀሳቅሳ ይህንን ሁሉ ማድረግ የምትችልበት ሁኔታ ላይ አይደለችም። እናም ስጦታው ቢኖራትም ማድረግ አለመቻሏ ያበሳጫታል።
ትምህርት
ጅጌሳ ሚሽን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው አንደኛ እና ሁለተኛ ክፍልን የተማረችው። በጣም ጎበዝ ልጅ ነበረች። በዚህም አንደኛ ወጣች። በጊዜው ግን ይህ ጥሩ ውጤት መሆኑን አላወቀችም ነበርና ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። ክፍሏ ገብታም ለሞግዚቷ ካርዷን ሳታሳይ ቆየች። ሁሉም ካሳዩ በኋላ መጨረሻ ካርዱን ሰጠቻት። እርሷም እቅፍ አድርጋ ሳመቻት። ምክንያቱም ውጤቷ በጣም ጥሩ ነው። በዚሁ መቀጠል እንዳለባት አስረድታት ሽልማት ሰጠቻት።
ሽልማቱ አንድ ፓኬት ደስታ ከረሜላና መንፈሳዊ ስዕል ነበር። እናም በሽልማቱ ተነቃቅታ ሁሌም ለመሸለም መትጋት ጀመረች። በድርጅቱ የቆየችው ሁለት ዓመት ብቻ በመሆኑ ደረጃዋን አስጠብቃ ወደ ቀጣዩ ክፍል ተዛወረች።
ዘነበች ሦስተኛ ክፍል ለመማር ስጋ ሜዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስትገባ ግማሽ መንፈቅ ዓመት አልፎ ነበር። ስለዚህ ደረጃዋ እንደጠበቀችው አልሆነላትም። ምክንያቱም የገባችበት ጊዜ ጫና አሳርፎባት ነበር። በቀጣዩ የትምህርት ጊዜ ውጤቷን ማስተካከል እንዳለባት አምና ስለተንቀሳቀሰች እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ ስትማር የደረጃ ተማሪ ሆና ነቀጠለች።
ስምንተኛ ክፍልን ለመማር አቡነባስሊዮስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደገባች የምትናገረው ዘነበች፤ የነበሩ ሁኔታዎች ምቹ ባለመ ሆናቸው ውጤታማነቷ እንደቀነሰ አጫውታናለች። ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ክፍልም በአየርጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስትማር ምቹ ሁኔታ አልነበራትምና ጉብዝናዋ ቀንሷል። ወደከፍተኛ ትምህርት ለመግባት ውጤት የመጣላት ለመምህርነት የሚያበቃ በመሆኑ በውጤቷ ደብረብረሃን መምህራን ኮሌጅ መመደቧን ትናገራለች።
አካል ጉዳተኝነት ያሰቡት ቦታ ሄዶ ለመማር አያስችልም የምትለው ባለታሪኳ፤ የነበረችበት ድርጅት ጥያቄ አቅርቦላት ባገኘችው የትምህርት ዕድል ምቹ የሆነውን ኪዊንስ ኮሌጅ መርጣ መከታተል እንደጀመረች ታስረዳለች። በትራንስፖርት ችግር እየተሰቃየችም ቢሆን በአካውንቲንግም ዲፕሎማዋን ይዛ ለመመረቅ በቅታለች። ከዚያም መማሯን ሳታቆም ዲግሪዋን በአድማስ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ተመረቀች።
በነበረባት ተደራራቢ ችግር ምክንያት ትምህርቷን መቀጠል እንዳልቻለች ያጫወተችን ዘነበች፤ ተንቀሳቅሶ፣ ወጪ ችሎ መማር ከባድ መሆኑን በማንሳት ከእውቀት ላለመራቅ ግን የተለያዩ ስልጠናዎችን እንደወሰደች ነግራናለች። ማንኛውም ትምህርት ቤት ለአካል ጉዳተኛ ምቹ የሆነ ቤተመጽሐፍት፣ ቤተሙከራውና ክፍል አለመኖሩም ፈተናዋን አክብዶት ስለነበር ኑሮዋን ለመምራት የሚያስችል ትምህርት ከወሰደች በኋላ ይብቃኝ ብላ ማቆሟን አጫውታናለች።
ዘነበች ቴሌ ለ21 ቀን የሰጠውን የኦፕሬተርነት ስልጠና ወስዳ መቀጠር አለመቻሏ፣ ዲግሪዋን ስትጀምር በህግ ተምራ መሥራት እንደማትችል መነገሯ ተስፋ እንዳስቆረጣትም ትገልጻለች። በተለይ ግን ከሁሉም ላለመማር ያስወሰናት የትራንስፖርት ጉዳይ መሆኑን ነግራናለች።
ሥራና ፈተናው
ከኮሌጅ እንደወጣች ሥራን የተለማመደችው አካል ጉዳተኞች ማህበር ውስጥ በማገልገል ነበር። ለሁለት ዓመታት በሂሳብ ሹምነትና ፀሐፊነት ሠርታለች። ከዚያ ዴልታ ኮምፒውተር ማሰልጠኛ በመግባት ስልጠና ወስዳ ቂርቆስ ወረዳ 7 ንግድ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ገባች። ለነጋዴዎች ፈቃድ መስጠትና መሰረዝ ላይ ትሠራም ጀመር። ሥራዋ ያስደሰታቸው አለቃዋ ያበረታቷት ጀመር። ወደሌላ ጽሕፈትቤት ልዛወር ስትላቸውም ለቤቷ አቅራቢያ በሆነው ቦሌ ወረዳ 10 ንግድ ጽህፈት ቤት ገባች።
የወረዳው አስተዳዳሪ ደግሞ በተቃራኒው ‹‹እንዲህ ዓይነት ሰው ለምን ተቀበላችሁ›› ብላ የጽህፈት ቤቱን ኃላፊ ላይ ቅሬታዋን ታሰማለች።ይሄ የረበሻት ዘነበችም ከቅርብ አለቆቿና የሥራ ባልደረቦቿ ጋር ተስማምታ ብትሠራም ሁኔታው ስላልተመቻት እንዲቀይሯት አመለከተች። ዕድል ቀናትናም ከወረዳው ስፋት አንጻር መስሪያቤቱ ለሁለት ተከፍሎ ስለነበር ወደ ቦሌ ወረዳ 15 ተዛወረች። እዚያም ቢሆን የተለየ ሁኔታ አልገጠማትም። አለቃዋ ሁልጊዜ ልብ ሰባሪ ንግግር ይናገራት ነበር። እርሷ የንግድ ጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስተባባሪ ሆና መስክ የሚበዛበት ሥራ ላይ ለምን ተመደበች በሚል ነው። ቅንነት ካለ ሥራው በውክልና መሠራት ይችላል። የቢሮ ኃላፊነቱን ደግሞ እርሷ መሥራት ትችላለች። ይህ ግን አልሆነምና አዕምሮዋን ላለመጉዳት ዳግመኛ ቦታ ለመቀየር ጥያቄ አቀረበች።
የወረዳው ካቢኔም ችግሯን አዳምጦ ከወረዳው ሳትወጣ ወሳኝ ሁነት ውስጥ አስተባባሪ ሆና እንድትሠራ አደረጋት። ዛሬ በሥራዋም በአለቃዋም ደስተኛ ነች። በዚያ ላይ ቤቷ ለመሄድም ብዙ አይርቃትም። እናም ውጤታማ ሥራ እየሠራች በመሆኑ ያስደስታታል።
ዘነበች የአካል ጉዳተኞች ማህበር ውስጥ የቦርድ አባል በመሆን አገልግላለች። ከዚያ ደግሞ ቦታ ቀይራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ሆና ሠርታለች። ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ ሴት አካልጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን አባል ነበረችና ወደ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ከፍ አለች። እናም አሁን በዚህ ደረጃ ላይ እያገለገለች ትገኛለች።
አካል ጉዳተኝነትና የአካባቢ ሁኔታ
‹‹በሁሉም ቦታ አካል ጉዳተኛ የመሥራትና ለሰው ልጅ የተሰጠው መብት ሁሉ እንደሚገባው ቢታወቅም በበጎ ፈቃድ እንዲደረግለት መሆኑ በጣም ያበሳጫኛል›› የምትለው እንግዳችን፤ የአካል ጉዳተኞች መብት የበጎ ፈቃደኞች ችሮታ ሊሆን አይገባም። መብታቸው እንደሆነ ታስቦ በእውቀታቸው ተለክተው ወደፈለጉበት ቦታ መሄድና የፈለጉትን ማግኘት ወይም ማድረግ እንዳለባቸው ታሳስባለች። ከባዱ የፈተና ጊዜዋ የነበረው በሥራ ቦታና በኪራይ ቤት ያሳለፈችው ጊዜ መሆኑን ትነጋራለች። ዲፕሎማና ዲግሪ ብትይዝም የሚቀጥራት አለመኖሩ ያናድዳታል።
በመጨረሻ የነበረችበት ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ተነጋግሮ ባያስቀጥሯት ኖሮ የዛሬ ህይወቷን እንደማትኖረውም ትናገራለች። ይህም ቢሆን በወቅቱ ቤት ተከራይቶ ለመኖር የሚከፈለው ገንዘብ በቂ እንዳልነበረ፣ ቢሮም በምንም መልኩ አካል ጉዳተኛን ታሳቢ ያደረገ እንዳልሆነ ታነሳለች። ይህ ደግሞ “መኖር ምን ይሠራል” የሚል ተስፋ ያስቆርጣት እንደነበር አትረሳውም።
አካልጉዳተኝነት ከመሥራት እንደማያግድ ለማሳየት 1፡30 ቢሮ ትገባ እንደነበር የምታነሳው ዘነበች፤ ምቹነት ባለመኖሩ ስቃይዋ ቢበረታም ያንን እየታገሰች እንደምትሠራ ትናገራለች። በተለይም በመጸዳጃው ምክንያት ውሃ ልክ ላይ ለዓመታት ስትጸዳዳ መቆየቷን አትዘነጋውም። የተከራየችበት ቤትም ቢሆን ይህ የመጸዳጃ ቤት ጉዳይ ፈተና ነበር። ምክንያቱም የሚከፈላት ደመወዝ 1ሺህ 100 ሲሆን፤ ለቤት ኪራይ 750 ታወጣለች።
ኪራዩ ዝቅ ያለበት ቦታ ገብታም ከዚህ የባሰ ገጥሟታል። መጸዳጃቤቱ ለአካል ጉዳተኛ ብቻ ሳይሆን ሙሉ አካል ላለውም የሚያስፈራና ሰፊ ነበር። በዚያ ላይ ይህንን ሳትፈራ ለመጠቀም ብትሞክር ደረጃ ስላለው አትችልም። መኖሪያ ቤቷ በጣም ድንጋያማ በመሆኑ ደግሞ የአካል ድጋፏ(ክራንቹ) በድንጋዩ ውስጥ እየገባ ወድቃ እየተነሳች እንደኖረችም ታስታውሳለች። ይህንን ጊዜ ‹‹መናገር ከሚቻለው በላይ ነው›› ትለዋለች። ግን ‹‹ሳይደግስ አይጣላም›› ነውና ነገሩ አለቃዋ አኗኗሯን አይቶ ኖሮ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተነጋግሮ ቂርቆስ ወረድ ብሎ ወረዳ 7 አካባቢ የቀበሌ ቤት እንዲሰጣት አድርጎ ነበርና በዚያ ዓመት ቆየች። በልማት ምክንያት ሲፈርስ ደግሞ ዓመታትን በኪራይ ስታሳልፍ ብትቆይም መልሳ በምትኩ በተሰጣት የጋራ መኖሪያ ቤት ገብታለች።
“ዛሬ ያንን ሁሉ ስቃይ አልፌ ቤቴን የአካል ጉዳተኛ ቤት አስመስየዋለሁ። አሁንም ቢሆን የእኔ መሰሎች በየመስሪያቤቱ እንደሚኖሩ አምናለሁ። እናም ድረሱላቸው ከማለት ውጪ የምለው አይኖረኝም። የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ስቃይ በእኔ ይብቃ›› ስትል ትማጸናለች። የሁኔታዎች አለመመቻቸት ፈተና እንዳይሆንባቸው አግዟቸው ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።
የአካል ጉዳተኛ ፈተና
ትምህርት ለመማር ከአየር ጤና ግንፍሌ ኪዊንስ ኮሌጅ ለመድረስ ሦስት ትራንስፖርት አቆራርጣ ትጠቀማለች። ይህ ግን የሚሆነው እንደ መኪኖቹ አሽከርካሪዎች መልካም ፈቃድ ነው። ገንዘብ ብትከፍልም እርሷ እንደማንኛውም ሰው መብቷ ሆኖ አትጫንም። ምክንያቱም ጠጋ በይ ብትባለ አይመቻትም። ስለዚህም ተሽከርካሪው ባዶ ሲሆን ብቻ ትሳፈራለች። ይህ ደግሞ የፈለገችበት ቦታና ኮሌጅ ገብታ ለመማር ለምትፈልገው ዘነበች ችግር ሆኖባታል።
‹‹የትራንስፖርት ላይ ጉዞ ረጅምና አድካሚ ነው። በሰዓት ገብቶ ለማንበብ አይቻልም። በባሶችም ሆነ በታክሲዎች ትቶ መሄድ ብርቅ ስላይደለ ሁልጊዜ ይፈጸማል።›› የምትለው ዘነበች፤ ፊት በር ላይ ካልሆነ አትሳፈርም። ቶሎ ውረጂ መባሉ ስለሚያሳቅቃት። እናም ይህንን ላለመባል ሁልጊዜ ጠዋት ለ12 ሩብ ጉዳይ ትወጣለች። ስትመለስ ደግሞ ቶሎ ካልተለቀቀች ሠራተኛው ሁሉ እቤቱ ከገባ በኋላ ነው ትራንስፖርት አግኝታ ወደ ቤቷ የምትገባው።
በትራንስፖርት ችግር ሁልጊዜ አርፍዳ የምትገባና የምትወጣው ዘነበች የትራንስፖርት ችግሬን አይቶ የሚያግዘኝ ካለ ለመማር ወደኋ አልልም ብላናለች። ምክንያቱም ያለመማሯ ዋና ምክንያት እንደልቧ መንቀሳቀስ አለመቻሏ ነውና።
የአክስት ውለታ
ከገጠር እንደመጣች አክስቷ ጤነኛ እንድት ሆንላት በማሰብ ‹‹ቼሻሪ ሆም›› የሚባል የሕፃናት አካልጉዳተኞች የሚታከሙበት፣ የሚያገ ግሙበት፣ ፊደል የሚቆጥሩበት ድርጅት ውስጥ መናገሻ አካባቢ አስገባቻት። ሀሙስና ዕሁድም የሚያስፈልጋትን በመያዝ ትጠይቃታለች። ይህ ደግሞ ተንፏቃ የምትሄደውን ዘነበችን አበርትቷት ወደ ክራንች ተዛወረች።
‹‹ አክስቴ የምትመጣበት ጊዜ ለእኔ ዓመት በዓል ነበር›› የምትለው እንግዳችን፤ የምታመጣላት ምግብ፣ የምታጫውታት፣ የምትነግራት ተረትና ታሪክ ሙሉነቷን ይነግራት እንደነበር ታወሳለች። ሁለት ዓመት በድርጅቱ ውስጥ ቆይታ ስትወጣም የተቀበለቻትና የተንከባከበቻት እርሷ እንደሆነች ትናገራለች። ግን ብዙ በአክስቷ ቤት የምትቆይበት ሁኔታ ስላልነበረ ማለትም ቤቷ አስፓልት ዳር፣ እርሷ ደግሞ ነጋዴ በመሆኗ ትምህርት ቤት እያደረሰ የሚያመጣት አይኖርም። እናም ይህንን ሁሉ ስቃይ በእኔ ምክንያት ማየት የለባትም በማለት ወደ ሻሸመኔ ‹‹ጅጌሳ›› ተብሎ ወደሚጠራ የካቶሊኮች ድርጅት አስገባቻት። በዚያም እየተመላለሰች ትጠይቃት ነበር። ሁለት ዓመት ሲሞላት ደግሞ መልሳ አዲስ አበባ አመጣቻትና ለተወሰነ ጊዜ ከእርሷ ጋር አቆየቻት።
እንቁ ታሪኮችን እየነገረቻት ደስተኛ እንድ ትሆንም ታደርጋት ነበር። ከእነዚህ መካከል እስከ አሁን ከአዕምሮዬ አልጠፋም የምትለው የአካልጉዳተኛዋ የቴሌ ሠራተኛ ታሪክ ነው። ይህ ታሪክ ሁልጊዜ ትልቅ ቢሮ ውስጥ የመሥራት ራዕይ እንዲኖራት፣ አርአያ መሆን እንደምትችል አስተምሯታል።
ዘነበች ‹‹በአክስቴ ቤት አንድም ቀን የበታችነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም። እንደውም እኔ ብቻ ልጇ እንደሆንኩ ይመስለኛል። አክስቴ ሳትሆን እናቴ ብቻ ነች የሚል እምነትም አለኝ። በተለያየ ጊዜ አካልጉዳተኛ ልጅ እንዳለኝ ይወቁ በማለት የማታፍርብኝ፤ ከአዋቂዎች ጋር እንድጫወት የምትፈቅድልኝ፤ የማልችለው ነገር እንደሌለ የምትነግረኝ እርሷ ብቻ ነች›› ትላለች ስለአክስቷ ስታወሳ።
‹‹የሞት ክብደቱ የገባኝ በእርሷ ነው። የሌለሁ ያህል ተሰምቶኛል። ግን ሌላም ጎንም እንዳለ አሳውቆኛል።›› የምትለው ዘነበች፤ እርሷ ባትሞት ኖሮ ራሴን ማስተዳደር አልችልም፤ በብቸኝነት መኖር እንዴት እንደሚቻልም አልረዳም ነበር። እናም ሞት መልካም ባይሆንም በእርሷ ሞት ብዙ ነገሮችን እንደተማረች ታነሳለች። መማርና ራሴን መለወጥ እንዳለባት ያወቀችው፣ በተለይም የማህበረሰቡ አሉታዊ ምልከታ ምን እንደሚመስል የተረዳችው ከዚያ በኋላ እንደነበር አጫውታናለች።
የአዳሪ ቤቶች ትዝታ
‹‹ትምህርትን ሀ ያልኩበት፣ የሕፃንነት ወጉን የልጅነት ቡረቃውን በሚገባ የተገበርኩበት፣ በሙሉነት የተገነባውን ህይወቴን ያሳደግኩበት፣ ሁልጊዜ እችላለሁ የሚል ስሜትን የፈጠረልኝ ነው። ማንነቴን እንድቀበለውና ከሌላው ማህበረሰብ ልዩነቴ እስከማይታየኝ ድረስ ያደረሰኝም ነው። ቦታው ላይ ያለው የስነልቦና ግንባታ ዘላለም በእኔ ችግር ውስጥ ያሉትን እንድረዳ አስችሎኛል›› ትላለች የአዳሪ ቤቷን ቆይታ ስታስታውስ ።
በዚህ ቦታ ጠዋት ተነስቶ በተቻለ መጠን የሚሠራ ሥራ አለ። አልጋ ማንጠፍ፤ ክፍላችንን ማፅዳት ግዴታ ነው። ይህ ደግሞ ስለራሳችን ኃላፊነት እንዲሰማን፣ ራሳችንን እንዴት መንከባከብ እንደምንችል እንድንማርና ሰዓታችንን እንዴት መጠቀም እንዳለብን አስተምሮናል ትላለች። ለመብላት፣ ለመጫወት፣ ለመማርና ለማጥናት እቅድና ፕሮግራም እንዲኖራቸው ያደረገ መሆኑን ትገልጻለች።
አካልጉዳተኛ ሆኖ ዋና መዋኘት እንደሚቻለ ያየችው አዳሪ ቤት ነው። ምክንያቱም ቤተሰብ ጋር ሆኖ ይህንን ማድረግ እጅግ አዳጋች ነው። ነገር ግን ሽርሽር ወስደዋቸው የተለያዩ ቦታዎች ላይ በሞግዚቶች አማካኝነት ዋና እንዲለማመዱ ሆነዋል። ስለዚህ ብዙ ነገሮችን የተማረችበትና ያየችበት መሆኑን አጫውታናለች።
ገጠመኝ
10ኛ ክፍል እያለች የገጠማት ነው። ከትምህርት ቤት ወጥታ አክስቷ ጋር በምትሄድበት ጊዜ አካል ጉዳተኛ መሆኗን አይተው ያዘኑ አንድ አዛውንት ሊያሻግሯት ነይ አሏት። እርሷም ምንም ይላሉ ብላ ስላላሰበች እጇን ሰጥታቸው አሻገሯት። ግን ከማሻገሩ ጀርባ ሌላ ነገር ነበር። አመስግና ልትለያቸው ስትል ‹‹ነይ እስኪ መቼም በዚህ ብቻ አይደለም የምንገናኘው አይደል። ሌላቀንም እዚሁ አካባቢ ብንገናኝ ምን ይመስልሻል?›› ትልቅነታቸውን በማየቷ ደስ ይለኛል ብላ መለሰችላቸው። ቀጠሉና አንድ ብር እየሰጧት ያልጠበቀችውን ሃሳብ ሰነዘሩ። ለጊዜው ምንም ስላልመሰላት ተሰናብታቸው ወደአክስቷ ቤት አመራች። ከዚያ መልስ ግን ወደዶርሟ ተመልሳ ለጓደኞቿ ስታወራቸው በጣም ሳቁባት። ማለት የፈለጉትንም አስረዷት። ይህ ደግሞ በዚያን ወቅት ማህበረሰቡ ስለእነርሱ የሚያስበውን እንድትረዳ አስችሏት እንደነበር አስረድቷታል። ጾታዊ ጥያቄም ቢሆን እንዴት እንደሚቀርብ ተምራበት ነበር። ይህ ገጠመኟ ብዙ ነገሮችን ግራና ቀኝ ያስተማራት እንደነበር አጫውታናለች።
የትዳር አጋር ጉዳይ
‹‹ህብረተሰቡ ማግባት አትችልም መውለድ አትችልም›› የሚል መሆኑን ያየሁት በሚቀርቡት የጓደኝነት ጥያቄዎች ነው። በተለያየ ምክንያት ቆራጥነታቸውን ሲያሳዩ አልተመለከትኩም። በተለይም የሚገጥሙኝ ጓደኞች በቤተሰቦቻቸው እጅግ ተወዳጅ በመሆናቸው ለቤተሰባቸው ሲሉ ግንኙነታቸውን ያቆማሉ።
ጓደኝነት ሲጀመር በመለኪያ መስፈርት አይደለም። ይልቁንም በፍቅርና በመተሳሰብ ነው። አንዱ ለአንዱ መኖርና ጎዶሎን የሚሞላ ለመሆንም ነው። ግን ብዙዎች ለጥቅምና ለስም ሲሉ እንዲሁም ራስና ቤተሰብ ወዳድነታቸው ተሳስቦ የመቀጠሉን ዕድል እያስቀረው ይገኛል። እናም ሴት አካልጉዳተኛ መሆን እጥፍ መገለልን ይዞ የሚጓዝበት ሁኔታ በመኖሩ የትዳር ሁኔታ እንዳይሳካ አድርጎታል ትላለች።
ተፈጥሮም ሆነ የተዛባው የማህበረሰቡ አመለካከት እኔንና መሰሎቼን ከዚህ ውጪ አድርጎናል የምትለው ዘነበች፤ ‹‹ሁልጊዜ ሰዎች የትዳር አጋር እንድሆናቸው የሚጠይቁኝ ለምንድነው የሚለው ጥያቄ ዘወትር በአዕምሮዬ ያቃጭላል። መልሱ ደግሞ ጥቅም ፍለጋ የሚለው እየሆነብኝ መጥቷል።›› ትላለች ያሳለፈችውን የትዳር ጥያቄ ጉዞ ስታስታውስ። እናም ጓደኞቿ ለእርሷ ዋጋ የሚከፍሉላት ካልሆኑ፤ ልብ ሰባሪ ክስተቶች ከበዙ የጓደኛ መኖር ለምኔ ትላለች። እናም በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደማትፈልግም አጫውታናለች።
መልዕክት
‹‹እኛ የራሳችን ህይወት አለን። በሌሎች ውስጥ መንቀሳቀስ የለብንም። ስለዚህ በራሳችን የህይወት ኡደት ህይወታችንን መቃኘት አለብን። ማህበረሰቡም ቢሆን የአካል ጉዳተኝነት እርግማን ነው ብሎ ማመኑን ማስቀረት አለበት። ሊያበረቱትና ኃይሉን ተጠቅሞ እንዲሠራ ሊያደርጉት ይገባል። አካል ጉዳተኛ ዕድል እንጂ እውቀት አላጣምና።›› የምትለው ዘነበች፤ እኔ ስለታገስኩኝ እዚህ እንደደረስኩ ሁሉ ቤተሰብ ያላቸውና አይዞህ የሚላቸው ያገኙ ከእኔ እንደሚልቁ መገንዘብ ይገባል ትላለች።
ተፈጥሮን መጋፈጥ ባይቻልም ምቹ ማድረግ ይቻላል። እናም ማህበረሰቡ ይህንን በማድረግ የአካል ጉዳተኞችን ስነልቦና ማነቃቃት ይገባል። አካል ጉዳተኞች የየዕለት ህይወት የሚታወሱበትን መንገድ መቀየስም አለባቸው ምክሯ ነው።
አካል ጉዳተኛ መሆን ቀይ ጥቁር፣ ወንድ ሴት እንደመሆን የሚፈጠር መልካም ልዩነት መሆኑን በማመን፤ አካል ጉዳተኛውም ግንዛቤው የሌለውን ማህበረሰብ ተደራጅቶ በማንቃት መሥራት አለብን ትላለች።
ሴትነትና አካል ጉዳተኝነት በጥምረትም በነጠላም የሚታይ ጉዳይ መሆኑን ትናገራለች። ማህበረሰቡ ሴትን ልጅ የሚወዳት ከምትሰጠው ጠቀሜታ አንጻር መሆኑን ማቆም አለበት። ሰው መሆኗን ብቻ ተቀብሎ ሊያግዛት ያስፈልጋል ስትል ጥብቅ መልዕክቷን በማስተላለፍ ተሰነባበትን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው