( ክፍል ሁለት )
ደማሙ “ወገኛ“ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን (በቅፅል ያጀብሁት ከወግ ጸሐፊነቱ ጋር አያይዤ ስለሆነ ይቅርታ ይደረግልኝ።) በለውጡ ሰሞን ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር አዘውትረን በቴሊቪዥን መስኮት የምናየውን ያህል እያየነው አይደለም። አልፎ አልፎ ብቅ ማለቱ ግን አልቀረም። መቼም በአቋም ተለይቶ ወይም ከውህደቱ አፈንግጦ ይሆናል የጠፋው አትሉኝም። ዛሬ ዘመኑ ተቀይሯል። ዘመነ ትህነግ አይደለም። አፈንግጦም የፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር፣ ሚኒስትር ለዛውም የጦር መሆን ይቻላል። እንኳን አማካሪ። ከብዙ መናፈቅ (‘ ና ‘ ጠብቆ ይነበብ) በኋላ በዚያ ሰሞን በእስካይላይት ሆቴል “ የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በ2032 ዓ .ም “ በሚል በተዘጋጀ አዲስ አይነት መድረክ ላይ የተከሰተው ምን አልባት ስለሀገሩ እንዲገለጥለት ለዓመታት ይቃትተው የነበረ ራእይ አበክሮ ተገልጦለት ይሆን ብዬ አሰብሁ።
ከለውጡ ወዲህ ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ .ም ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ በዓለ ሲመት ንግግር ጋር የሚስተካከል ታላቅ ክስተት ማክሰኞ ሕዳር 23 ቀን 2012 ዓ.ም ብዙዎቻችንን በአግራሞት እጃችንን በአፋችን ያስጫነ ልዩ ታሪካዊ ሁነት በእስካይላይት ሆቴል ተከውኗል። ምን አልባት በአግባቡ ከተጠቀምንበት የሀገራችንን መፃኢ እጣ ፈንታ እስከ ወዲያኛው በበጎ መልኩ የሚወስን ይሆናል። “ዴስቲኒ ኢትዮጵያ“ ከ2004 ዓ .ም ጀምሮ ላይ ታች ሲል ሲደክምለት የኖረው“ የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በ2032 ዓ. ም “ን ከ“ንጋት“ ጋር ሊሞሽር ታዳሚው በእስካይ ላይት ሆቴል በስአቱ ተገኝቷል። ከጉምቱ ፖለቲከኞች እስከ የፌስ ቡክ አርበኞች፤ ከሚኒስትር እስከ ክልል ርዕሳነ መስተዳድር እንዲሁም ከሊቅ እስከ ደቂቅ የታደሙበት የተስፋ፣ የሕልም “ሰርግ“። ኢትዮጵያን ከራእይዋ የሚሞሽር ድል ያለ ድግስ። ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም ከታዳሚዎች አንዱ ነበር። ተመስጦ ስመለከተው አንድ ወጉን አስታወሰኝ። ካልዘነጋሁ 2003 ዓ.ም በተባ ብዕሩ ያወጋን “ጠጠሮቹ እና ሌሎቹ“ ከተሰኘው የጉዞ ማስታወሻ ቅዱስ ዩሐንስ ራእዩን የጻፈበትን ዋሻ ግሪክ “ባለራእይዋን ደሴት“ እየጎበኘ በሀሳቡ “…እኔም ምናለ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ራእይ ባየሁ ብዬ ተመኘሁ። የመጣና የሄደ ሁሉ እንዲህ ትሆናለች እያለ በሌለ ተስፋ ከሚሞላን ቁርጥ ያለውን የነገ ዕጣ ፈንታዋን አውቀን በጊዜ ብንገላገል ምናለ። ከዚህ ጥቁር ዐለት በነጭ ሰሌዳ ተጽፎ አንዳች ራእይ ቢታየኝ ምናለ።…” በማለት በሄደበት ሁሉ ይዟት ስለሚዞረው ሀገሩ ይቃትታል። ዛሬ ግን ሊገለጥለት ይመኘው የነበረውን ራእይ በእነ “ቲም ንጉሡ “ የተገለጠለት ይመስለኛል።
እንደ ነብይ ራእይ ባገሩ አይከበርም ካላልን በስተቀር እልፍ አእላፍ ባለ ራእዮች በዚች ምድር ተመላልሰዋል። ራእያቸውን የሚተረጉም ተቀብሎ የሚፈፅም አላገኙም እንጂ። ወይም እንደ ዲያቆን ዳንኤል እያንዳንዳችን በአድራሻችን ራእይ ካልታየን ካላልን በስተቀር ባለራእዮችን ከአንድም ሁለት፣ ሶስቴ አስነስቶልን ያውቃል። የራእይ ቡዳዎች መሆናችን እንዳለ ሆኖ። እንደ ቅዱስ ዩሐንስ በጥቁሩ ዐለት በነጩ ሰሌዳ ተጽፎ ባይሆንም በእነ ”ዴስቲኒ ኢትዮጵያ“ ተገልጦ በ50ዎቹ ወካይ ኢትዮጵያውያን ተተርጉሞ ምን አልባት በሀገራችን ታሪክ ስትወሳ በምትኖረው በዛች ታሪካዊ ዕለት የዚች ሀገር ዕጣ ፈንታዋ በእስካይ ላይት ሆቴል “ የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በ2032 ዓ.ም “ በሚል ርዕስ ራእይዋ ተገልጧል። ኢትዮጵያውያንን ከሁሉም ማዕዘን ሙሉ በሙሉ ሊወክሉ ይችላሉ በተባሉ ዜጎቿ አማካኝነት የተፈጠረ መደማመጥ፣ የልብ ለልብ መገናኘት እና መቀባበል ምን አልባት ከአድዋ በኋላ የመጀመሪያ ነው ማለት ይቻላል። በቅንነት እና በየዋህነት አምነን ከተቀበልነው የሀገራችንን ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስን ራእይ ተገልጧል። ድርሻ ድርሻችንን ወስደን የመፈፀሙ የዜግነት ግዴታ የሁላችን ነው። እነ ”ቲም ንጉሡ“ ከአመታት እልህ አስጨራሽ ጥረት እና መቃተት በኋላ የተገለጠላቸውን ራእይ ከእነትርጉሙ አስረክበውናል። ዘመኑንም ሆነ ትውልዱን ሊዋጅ የሚችል ራእይ ስለሆነ በጊዜ የለም ስሜት ወደ መሬት ልናወረደው ይገባል።
ታላቁ መፅሐፍ ራእይ የሌለው ትውልድ ይጠፋል ማለቱ ራእይ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያረጋግጣል። በአለማዊ ህይወትም ስለ ራሳችን፣ ቤተሰባችን፣ ማህበረሰባችን፣ ሀገራችን ከፍ ሲልም አለማችን ልናሳካው፣ ልንደርስበት የምንፈልገው ራእይ አለን። ዴስቲኒ ኢትዮጵያዎች ወይም “ቲም ንጉሡ“ የተገለጠላቸው ራእይ በ50ዎቹ ደቀ መዛሙርት ተተርጉሞ
“ ብሩህ ተስፋ ከፊታችን ነው !!!
እርሱን ዕውን ለማድረግ እንነሳ !!! “
በሚል ርዕስ ከወካይ ዜጎች ለመላው ኢትዮጵያውያን እንዲህ ቀርቧል።
- ተስፋ በሚጣልበት ለውጥ ውስጥ መሆናችንን ብናውቅም በተቃራኒው ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራችን መንታ መንገድ ላይ የምትገኝ በመሆኗ ሁላችንም ዛሬ ለመጓዝ የምንመርጠው የትኛውም መንገድ የሀገራችንን ዕጣ ፈንታ በእጅጉ የሚወስን መሆኑንና እንደሀገር ነገ የሚገጥመን ዕጣ ፈንታ በዋነኝነት በእጃችን ላይ እንደሆነ ተገንዝበናል።
- ከሁሉ አስቀድሞ በመጪዎቹ 20 ዓመታት ውስጥ ሀገራችንን ኢትዮጵያን ሊገጥሟት የሚችሉ፣ መንገዳቸውና መጨረሻቸውም የተለያየ አራት አማራጭ ዕጣ ፈንታዎች (ሴናሪዮዎች) ከፊታችን እንደተደቀኑ ተረድተናል። እነዚህን ንጋት፣ የፉክክር ቤት፣ አፄ በጉልበቱ እና ሠባራ ወንበር ብለን የሰየምናቸው ሲሆን ከነዚ።ህ ሴናሪዮዎች መካከል ሶስቱ በሁላችንም ዕይታ መልካም አማራጮች አለመሆናቸውን ተገንዝበናል። በሌላ በኩል ንጋት /dawn/ ብለን የሰየምነው ሴናሪዮ በአብዛኛው ሁላችንንም ሊያግባባ የሚችል በጎ አማራጭ መሆኑን አይተናል።
- ይህ ‘ ንጋት ’ ብለን የሰየምነው ሴናሪዮ ከሁሉም የተሻለ አማራጭ ቢሆንም ቁጭ ብሎ የሚጠብቀን ሳይሆን ከእያንዳንዳችን ከወዲሁ ትልቅ ኃላፊነት ያዘሉ ተግባራትን የሚጠብቅብን መሆኑን ተገንዝበናል። እነዚህን ተግባራት ለመፈጸም ደግሞ የሴናሪዮ ቡድኑ አባላት ቁርጠኞች መሆናችንንና ይህም የጋራ አቋማችን እንደሆነ ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን። ቁጭ ብለን በመጠባበቅ የማይገኘውን ‘ንጋት’ ዕውን ለማድረግ ታዲያ ፈጽሞ መተው ያሉብን ተግባራት መኖራቸውንና ከዚህ በተጨማሪም እያንዳንዳችን በጽንአት ልንወስዳቸው የሚገቡን እርምጃዎች መኖራቸውን ተገንዝበናል።
- ሁላችንም የምንፈልጋትን ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ፈጽሞ መተው ያለብን አንድ ዓቢይ ወቅታዊ ጉዳይ አለ። ይኸውም በሀገራችን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን ግጭትና ብጥብጥ፣ እርሱንም ተከትሎ የሚከሰተውን የዜጎች ህልፈተ-ህይወትና የህዝብ መፈናቀል ከግምት ውስጥ በማስገባት በሀገሪቱ ውስጥ በየትኛውም ደረጃ የምንገኝ የፖለቲካና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሪዎች የምንሰነዝራቸውን ጥያቄዎች፣ በመድረክ የምናደርጋቸውን ንግግሮችና እርስበርስ የምናካሂዳቸውን የሃሳብ ልውውጦች ኃላፊነት በተመላበትና በሰለጠነ መንገድ ለማራመድ እንድንችል እንመክራለን። እኛም ይህንኑ ለማድረግ ተስማምተናል።
- በዚህ ራዕያችን መሳካት ሁላችንም ተግተን መፈጸም ያሉብን ዓበይት ጉዳዮች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡-
5.1. በየጊዜው እያየነው ያለነው አላስፈላጊ ግጭትና እርሱን ተከትሎ የሚከሰተው እልቂትና የሀብት ውድመት ተመልሶ እንዳይመጣ፣ በሃሳብ አለመግባባቱም ፈጥኖ ወደ ጥቃትና ግጭት እንዳያመራ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለዚህም እንደፖለቲካ መሪነታችን ወይም ኃላፊነት እንደሚሰማው ኢትዮጵያዊ ዜግነታችን ግጭት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ሃሳቦች ወደ ሕዝብ ከመውረዳቸው በፊት በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት እልባት እንዲያገኙ ሁላችንም አጥብቀን እንድንሰራ እንጠይቃለን።
5.2. በሀገራችን ሲንከባለሉ የቆዩ አወዛጋቢ ጉዳዮች በዴሞክራሲያዊ ምርጫ በህዝብ ተመርጦ የሚመጣ መንግሥት እንዲፈታቸው የሚጠበቁ ቢሆኑም አንዳንድ ጉዳዮች ግን ጊዜ የማይሰጣቸውና በቅድሚያ መከወን የሚገባቸው ናቸው። ለምሳሌ በመላ ሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን፤ የወጣቶች ሥራ አጥነት እንዲቀንስ ጥረት ማድረግ፣ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት ሊጠቀሱ ይችላሉ። እኛ የሴናሪዮ ቡድኑ አባላት እነዚህና መሰል አጣዳፊና ፈታኝ ጉዳዮች የግጭት መንስኤዎች እንዳይሆኑና በነዚህና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ይቻል ዘንድ ተከታታይነት ያላቸው ውይይቶች እንዲካሄዱ እንመክራለን።
5.3. እኛ የሴናሪዮ ቡድኑ አባላት ለሀገራዊ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ሲባል በጊዜ ሂደት የሚፈቱና ከምርጫ በኋላ ሊሻገሩ የሚችሉትን ማናቸውንም ጉዳዮች ግለሰቦች፣ ቡድኖችም ሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲያቀርቡ እንመክራለን። እኛም ብንሆን እነዚህን ጉዳዮች በምንም አይነት አመክንዮ ቢሆን ለግጭት መጫሪያነትና መቀስቀሻነት ላለመጠቀም ተስማምተናል።
5.4. እኛ የሴናሪዮ ቡድኑ አባላት ሀገራዊ ውሳኔ የሚያሻቸው ማናቸውም ጉዳዮች ሁሉም በአንድ ጊዜ ሊተገበሩ እንደማይችሉና በሂደት እንደሚፈቱ አውቀን ሁላችንም ለጉዳዮቹ የመፍትሔ አካል በመሆን ጉዳዮቹ ቅደም ተከተል በሚይዙበት ሁኔታ ላይ የጋራ መግባባት ላይ እንዲደረስ ጥሪ እናቀርባለን። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ባለፉት ዘመናት በሀገራችን ታሪክ ላይ የሚታየውን አለመግባባት ጊዜ ወስዶ ለማየትና ከሁሉም የአተያይ ጎራዎች የተውጣጡ ምሑራንን በማሳተፍ እስክንግባባ ድረስ ለግጭት በማይዳርግና የቆየውን ህብረ ብሄራዊ ትስስራችንን በማያላላ መንገድ እንድንጠቀምበት እናሳስባለን።
- እኛ የሴናሪዮ ቡድኑ አባላት በዚህ የሴናሪዮ ቀረፃ ሂደት እንደተረዳነው ከሆነ የተለያየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ያላቸው ወገኖች የውይይት መድረክ ቢያገኙ ወዳጅነትን መፍጠርና ወንድማማችነትን ማጎልበት እንደሚቻል፣ በሰከነ መንፈስ በመወያየት ከባድና አይነኬ የሚባሉ የፖለቲካ ጉዳዮች ሊዳሰሱ እንደሚችሉና ከዚህ መሠል ሂደት መግባባት፣ መተማመንና መፍትሔ ሊመጣ እንደሚችል ተምረናል። ስለሆነም የፖለቲካ መሪዎች፣ አክቲቪስቶችና ሌሎች ዜጎች ከመደበኛ መድረኮች ባሻገር በሌሎች መንገዶች እየተገናኙ ቢወያዩና የጋራ መፍትሔዎችን ቢያፈላልጉ የተራራቁ አቋሞቻቸውን ለማቀራረብና ልዩነቶቻቸውን ለማቻቻል እንደሚያግዛቸው ከልባችን የምናምን መሆኑን ከወዲሁ እየገለጽን በሀገራችን የጋራ ጉዳዮች ላይ በመደበኛና ሌሎች መንገዶች ውይይቶች እንዲስፋፉ ጥሪ እናስተላልፋለን።
- እነሆ እኛ የዴስቲኒ ኢትዮጵያ የሴናሪዮ ቡድን አባላት አሁን የፈጠርነውን እህትማማችነት እና ወንድማማችነት እንደ መልካም ስንቅ በመውሰድና ደግሞም ለሀገራችን መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል ጠቃሚ መሣሪያ እንደሆነ በማመን የእርስበርስ ግንኙነታችንን ይበልጥ አጠናክረን ለመቀጠል የወሰንን መሆናችንን እየገለጽን አንዲት ውድ ሀገራችንን ለማዳንና ወደ ‘ንጋት’ እንድንደርስ በፍጹም መሰጠት እንደምናግዝ ቃል እንገባለን። …”
ሀገራዊ ጥሪ
መላው የሀገራችን ማህበረሰቦች በብዙ ማስተዋል የጥንቃቄ ጉዞ እንዲያደርጉና ሁሉም በየፊናው የሚጠበቅበትን ግዴታ እየተወጣ ሠላምን እንዲያስጠብቅ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ይህንን ብናደርግ እንደሀገር ‘ንጋት’ ላይ የምንደርስበትን ጊዜ ማፋጠን ይቻላል ብለን በፅኑ እናምናለን። ሀገራችን ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ አላት። ተስፋውን እኛና ልጆቻችን እርግጠኝነት መጨበጥ እንችላለን። ሁላችንም በይቅርታና በወንድማማችነት መንፈስ እንነሳ። በትእግስትና በማስተዋል እንራመድ። በትጋት ለሠላም እንሥራ !!!
ፈጣሪ ሀገራችንና ኢትዮጵያውያንን አብዝቶ ይባርክ !!!
አሜን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )
fenote1971@gmail.com