በማለዳው
የጥዋቱ ቅዝቃዜ ለሣምንታት ማቀዝቀዣ ክፍል የገባ ሥጋ ይመስል ጭምትርትር ያደርጋል። የቁሩ ግሪፊያ ከጨካኞች እርግጫ ባልተናነሳ መልኩ አቅልን ያስታል። ከተራራው ግርጌ ግራ ቀኝ ሽው እልም እያለ የሚነፍሰው ንፋስ ቁም! ተከበሃል ብሎ በጣላት ቀጣና ስትወድቅ የሚፈጥረውን ስሜት ያስተጋባል።
በአራቱም አቅጣጫ የነፋሱ ድምጽ እየተንሾካሾከ እረፍት ይነሳል። ከዛፉ አናት ደጋግመው ዱብ! ዱብ! የሚሉ የባህር ዛፍ ፍሬዎች ከአንዳች የማይታወቅ ስፍራ ባዕድ ነገር የተወረወረ ይመስል ፍርሃትን ያነግሳሉ። በዚህ ስፍራ የቅጠል ኮሽታ፣ የበረከቱ ድምፆች ቱማታ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ቢያሰኙና እግሬ አውጪኝ ብሎ መበርገግ ቢከሰት ላያስገርም ይችላል። የአካባቢው እውነታ ለዚህ የታደለ ነውና።
ወዲህ ደግሞ የማለዳ ወፎች ዝማሬ፣ የቁራ ማንቋረር፣ የትንንሽ ተሳቢዎች ሽውታ ቀልብ ይገዛል። የዛፎቹ ቁመት፣ ውፍርትና ውበት፣ አልፎ አልፎም ቸምቸሞ ጎፈሬውን አበጥሮ እንደሚንገዋለል ጎረምሳ የዛፎቹ ጥቅጥቅ ማለት እይታን ይስባል። የሁኔታዎቹ ጉራማይሌነት አካባቢውን ላልተላመደ እይታውን ሰቅዘው መያዛቸው አይቀሬ ነው። በዛፎቹ መሃል ለመሃል የተንጣለጠሉና የተጠመጠሙ ሐረጎች ተደጋግፈው ከዛፉ አናት ላይ ለመውጣት የሚያደረጉት ፍልሚያም ተፈጥሮንና የህይወት ውጣ ውረድን ለማሳየት መልካም ምሳሌ ይሆናል።
በዚህ የማለዳ ሁነት ማልደው በመውጣት ማንም የማይቀድማቸው በርካታ አትሌቶች ደግሞ በተለመደው ሰዓት ከስፍራው ይገኛሉ። አትሌቶቹ ምንም እንኳን ደኑ መሃል ደፍረው ባይገቡ ጫካውን ተተግነውና መስመር ሠርተው ላይ ታች ሲሯሯጡ ማየት የተለመደ ነው። አትሌቶቹ ሁሌም ማለዳ ከዚህ ስፍራ አይታጡም። የነገው አገር ተረካቢዎች ጥረትና ድካም በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ስም አድምቆ ማስጠራት ነውና ብርቱዎቹ በማለዳው ቁር በጥንካሬ ተጉዘው ፣በየቋጥኙ ሲተሙ ይስተዋላል።
በዚሁ ማለዳ ሌላም ትዕይንት አለ። የነጋባቸው አውሬዎችን ከፊት ለፊታቸው አስቀድመውና እግሮቻቸውን ተከትለው የእራሳቸውን እግር የሚተክሉ የአንዳንድ ውሾች ጉዳይ።
ከእነዚህ ውሾች አብዛኞቹ ከአዲስ አበባ ዳርቻ ተጠራርተው በህብረት የተጣመሩ ናቸው። ማለዳ ላይ አውሬ በማባረርና ቀበሮዎችን በማስደንበርም በተራቸው ጀብደኞች ይሆናሉ። የእነዚህን ውሾች ዱካ ተከትለው ወደ ጫካው ዘው ብለው የሚገቡ በርካታ ጭራሮ ለቃሚ ሴቶችም የዚሁ ማለዳ አንድ አካል ናቸው። ሴቶቹ የእንጀራ ጉዳይ ሆኖ ከአካባቢው አይጠፉም። በርካቶቹ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ከእንቅልፍ ነቅተው በእግራቸው ወደ ጫካው ያቀናሉ። ይህን ህይወት ለዓመታት የተላመዱት ነውና ለሌሎች ግርምታ እምብዛም የተለየ ስሜት የላቸውም። የቁሩን ጥዝጣዜ፣ የቅጠሉን ኮሽታ፣ የአውሬው ድምፅና የሌሎችንም ፈታኝ ችግሮች ተቋቁመው ዓመታትን በጽናት ተሻግረዋል።
እናቶች በጫካ ውስጥ
እማማ ውድነሽ ዳብሎ ይባላሉ። ውልደታቸው አርባ ምንጭ አካባቢ ነው። ከወጣትነት ዘመናቸው ጀምረው ወደ እንጦጦ ጫካ እየሄዱ ቅጠል ጠራርገው፤ የወደቀ ጭራሮ ለቃቅመው ቤተሰባቸውን ሲመሩ ቆይተዋል ።ከማገዶው ሽያጭ ከሚያገኙት ጥቂት ገቢም ጎጆ አቅንተው ልጆች አሳድገዋል። ባለቤታቸው በውትድርና ዓለም የቆዩ ናቸው። የጦርነት አሻራ አንድ እጃቸውን አሳጥቶ ዓይናቸውን አጥፍቷል።
የወታደሩ ሚስት እማማ ውድነሽ ሁሌም እግራቸውን ያማቸዋል፤ አንድ ዓይናቸውም ብትሆን በቂ ብርሃን የላትም። በስራ የደከመው አካላቸው እየደከመና እርጅና እየተጫናቸው ነው። አሁን ላይ ባለቤታቸው ወደ ትውልድ አገራቸው በመመለሳቸው ብቻቸውን ኑሮ እየገፉ ነው። ዛሬም ከትናንቱ የተለየ ለውጥ ባለመኖሩ ጭራሮ እየለቀሙ ኑሯቸውን ይመራሉ።
እማማ ውድነሻ አንድ ኩንታል ሙሉ ጥራጊ ቅጠል እስከ 20 ብር ይሸጣሉ። ሁለት ልጆች ቢኖራቸው ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ እናታቸውን ለመደገፍ አልታደሉም። ውድነሽ ዘወትር እንዲህ ከመልፋት ውጭ ተስፋ እንደሌላቸው ይናገራሉ። ቤተሰብና ዘመድ ዘንድ አዝማድ የመጠጋት ዕድል የላቸውምና። ፈታኝ በሆነ ኑሮ ውስጥ አልፈው፤ ዛሬም ፈተና በበዛበት ዓለም ውስጥ ይኖራሉ።
ሌላኛዋና ስማቸውን መናገር የማይፈልጉት እናት ደግሞ ከሌላ አካባቢ ሽንቁሩ ሚካኤል ለፀበል መጥተው የሚደግፋቸው ያጡ ናቸው። በቅርበት ካለው ጫካ እየለቃቀሙም እስከ 10 ኪሎ ሜትር ድረስ በእግራቸው ተጉዘውና ጭራሮ ለቃቀቅመው 20 እና 30 ብር ይሸጣሉ።
እኚህ እናት በዚሁ ሥራ የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈንና ወዲህ ደግሞ ጤናቸው እንዲያገግም ፀበል እየተጠመቁ በቤተክርስቲያኑ ተጠግተው ይኖራሉ። እናት አባታቸው በህይወት አለመኖራቸው፤ ወንድምና እህቶቻቸው ደግሞ ለማገዝ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ተስፋ አስቆርጧቸዋል። እናም ውሏቸው ከእንጦጦ ተራራ ላይ ካለው ጫካ ውስጥ ሆኗል።
ፈተና
የአካባቢው ሁኔታ የሚረዱ አንዳንዶች እነዚህ እናቶች ጨለማውን ደፍረውና ሌሊት እንቅላፋቸውን አጥተው ማገዶ ለቀማ ሲዘዋወሩ ጫካውን ተገን አድርገው እነርሱን ለመድፈር የሚያስቡ በርካቶች መኖራቸውን ይናጋራሉ። ለቤተሰቦቻቸው ብርሃን እንዲ ወጣ ላይ ታች ሲሯሯጡ፤ ኑሯቸውንና ሕይወታቸውን ለማጨለም የሚለፉ ጥቂቶች አይደሉም።
እነርሱ እንደሚሉት የማይነጋ ሌሊት የሌለ ይመስል እነርሱም ጫካ ተደብቀው ሲነጋ ብርሃን ያጋልጣቸዋል ። ጤነኛ መስለው ይሂዱ እንጂ ጤናን የሚያሰናክሉ ሰዎች መሆናቸውን ስናስብ ልባችን ክፉኛ ይጎዳል። ለመሆኑ ሰው እናት፣ እህት፣ አክስትና አያት እያለው በሴት ልጅ ላይ እንዲህ የደነደነ ልብ የሰጠው ምን ነክቶት ይሆን? ሲሉም ይጠይቃሉ። የዛኔ በየጫካው ሲሄዱ ጅቡ እንኳን እየፈራ ይሸሻቸው ነበር። አንዳንዶች ደግሞ እነርሱን ለመድፈር ማድባታቸውን ሲያስቡት አሳዛኝ እንደሚሆንባቸው ይናገራሉ።
ብዙዎቹ በጣም የከፋ ችግር እንደሚደርስ ባቸው ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ ቀደም ሲል ደን ጠባቂ የሚባሉ በነበሩ ጊዜ ችግሩ እጅግ የከፋ እንደነበር ያስታውሳሉ። እነዛ ክፉ አጋጣሚዎች መፈጠራቸውን እንጂ መቼ እና በማን እንደተፈጠሩ ለማወቅም ውስብስብ ሆኖ መቆየቱን በትዝታ ያወሱታል። የወዳደቀ ደረቅ ቅጠልና ጭራሮ ለመልቀምም ለደን ጥበቃ ሠራተኞች 10 ብር ይከፍላሉ። ግን ይህንን ችግር ቢናገሩ በሌላ ቀን ወደዚህ ስፍራ ሄደው ጭራሮ መልቀም ስለማይችሉ ሁሉንም በዝምታ ለማለፍ ይገደዳሉ። ለመሆኑ ችግሩን ቢናገሩ ማን ይስማቸዋል፤ ማንስ ይታደጋቸዋል ሲሉ የእናቶችንና የልጃገረዶችን ህመም ይጋራሉ።
ከልካይ የበዛበት
ልክ እንደ ዝንጀሮ ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ ዝላይና ልፋት በበዛት የጫካ ጭራሮ ለቀማ አያሌ ችግሮች እንደበዙበት ይናገራሉ። በተለይም ጫካውን የሚጠብቁ ሰዎች አይሆንም እያሏቸው በተደጋጋሚ ይከለክሏቸዋል። ለምን ብለው ሲጠይቁ ደግሞ የቆመው ዛፍ ምግብ ይልጋል። ምግቡን የሚያገኘው ደግሞ ከዚህ ዛፍ ላይ ከወዳደቁ ቅጠሎችና ጭራሮ ብስባሽ እንጂ ማንም ውሃ አያጠጣቸውም፤ ምግብ አይሰጣቸውም። በመሆኑም ምግባቸውን አትሻሙ ሲሉ ይከለክሏቸዋል። ወዲህ ደግሞ አውሬውና አስፈሪው ጨለማ በራሱ በጣም ስለሚያስፈራቸው እንደ ከልካይ ይቆጥሩታል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ግን የተቻላቸውን ለማድረግ ይታትራሉ። ምንም እንኳን ከልካይ የበዛበት ቢሆንም ሕይወታቸው፣ ህልውናቸው በዚህ ላይ የተመሰረተ ነውና እንደምንም ተለማምጠው ቀኑን ለማለፍ ይገደዳሉ። አንዳንዴም ከፋ ሲልባቸው ትተውት ለመመለስ ይገደዳሉ። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ነገሮች እየተስተካከሉ ሲሆን ችግሩን የሚገነዘቡ ወጣቶች በጥበቃ መመደባቸውን ይናገራሉ።
ተጠቃሚዎቹ
አዲስ አበባ ውስጥ ዛሬም ማገዶ ለቃሚዎች በብዛት ስለመኖራቸው የሚያሳ ብቀው ማገዶና ቅጠል የሚረከባቸው ሰው መበርከቱ ነው። በመሃል አዲስ አበባ በኩበት ጢስ እየታፋኑ፣ በቅጠል ወላፈን የሚለበለቡ እጆች በችግር የሚጋረጡ ፊቶችና በጭስ ብዛት የሚጠቁሩ ጣሪያዎች የትዬ ሌሌዎች ናቸው። አሁንም በርካታ ጣሪያዎች በእሳትና ጭስ ታፍነው ይኖራሉ። እናም ተጠቃሚዎቹ ከእንጦጦ ተራራ የሚለቀሙ ቅጠልና ጭራ ሮችን እየማገዱ ለልጆቻቸው ምግብ ያበስላሉ። በተለይም ደግሞ ቆጣሪ የሌላቸውና በተለምዶ የቀበሌ ቤት የሚባሉት አካባቢ ያሉ ሰዎች ይህን ይጠቀማሉ። ይህም ብቻ አይደለም የመብራት ቆጣሪ ለማስገባት አቅም የሌላቸው ሰዎችም ቋሚ ደንበኞች ናቸው። በተለይ ደግሞ ቀጨኔ በሚባለው የሰሜናዊ ክፍል አካባቢ በርካቶች ቅጠልና ጭራሮን በብዛት ይጠቀማሉ።
ከዚህ በዘለለ በባህላዊ መንገድ አረቄ የሚያወጡ ሰዎች የመጀመሪያ ምርጫቸው ይህን ማገዶ መጠቀም ነው። ካልሆነ ግን በኤሌክትሪክ ምድጃ አረቄ ለማውጣት አይቻላቸውም። ከዚህም በተጨማሪ ጠላ እና የመሳሰሉትን ባህላዊ መጠጦች ለማዘጋጀት፣ እንኩሮ ለማነኮር፣ ማገዶውን ይጠቀማሉ።
ስለነገ
በዚህ ሁኔታ ኑሯቸውን እየደጎሙ ከዛሬ ላይ ቢደርሱም የነገ ሕይወት ያሳስባቸዋል። ኑሮ ጣሪያ እየነካ እንድምን አድርገው እነዚህን ቀናት እንደሚሻገሩ ሲያስቡ ሁሉ ነገር ጭንቅ ጥብብ ይላቸዋል። ህይወታችን መምራት እንጂ የተለየ እቅድ ሆነ ዓላማ የለንም የሚሉት እነዚህ እናቶች ‹‹ከዛሬ ነገ የተሻለ ኑሮ ይኖራል ብለን ዓመታትን ብንለፋም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ዓመታት ተቆጠሩ›› ይላሉ።
ምናልባትም እነዚህ እንስቶች የነገ ሕይወታቸው ሊመሩ የቤተሰባቸውን ሕይወት ሊያቃኑ ደፋ ቀና እያሉ ነው። ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ወይ በሚያስብሉ ክስተቶች ውስጥ አልፈው ከዛሬ ላይ ቢደርሱም የነገው ነገር ያሳስባቸዋል። ታዲያ ይህ ኑሮ በርካቶች እስከ ዛሬ የዘለቁበት ቢሆንም ነገ ግን አስተማማኝ ዋስትና የሚሆናቸው አይደለም።
በአገሪቱ ዋና ከተማ ውስጥ እየኖሩና ዜጎችም ወደ ብልጽና ማማ እያማተሩ ባለበት ዘመን እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ዘመኑ የሚፈቅደውን ስልጣኔ ሳይጋሩ በድህነት የመኖራቸው እውነት አሳሳቢ ይሆናል። እነሱም ቢሆኑ ደጋግመው መንግስት ትኩረት ሊሰጠን ይገባል ባይ ናቸው። በተለይ ደግሞ በሴቶች መብት ላይ እንሠራለን የሚሉ ግብረሰናይ ድርጅቶችና የሚመለከታቸው አካላት በእነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ አበክረው ሊሠሩ ይገባል። የእኛም መልዕክት ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር