በዚች ምድር የሚገኝ ሕይወት ያለው አካል ጉርሱም ልብሱም የሚመነጨው ከተፈጥሮ ነው፡፡ በእርሷ ላይ የሚያርፈው ክንድ በበረታ ቁጥር ምላሿ የከፋ ይሆናል፡፡ የሰው ልጅ ዘግይቶም ቢሆን ይህን የተረዳ ይመስላል፡፡ በእጁ ያዛባውን የተፈጥሮ ሚዛን ለማስተካከል እየኳተነ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም የዚሁ አካል ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ያለ ስስት ፀጋዎቿን ከለገሰቻቸው አገሮች ተቀዳሚዋ ናት ማለት ይቻላል፡፡ ፀጋዋን አሣይታ እንቁልልጭ በሚል ዓይነት ከነሣቻቸውም እንዲሁ ቀዳሚ ናት፡፡ ከማየት በዘለለ ከተፈጥሮ ሃብቷ ተቋድሶ ጎኑ ያልደነደነ ሕዝብ መኖሪያ፡፡
የኢትዮጵያ አርሶ አደር ለረጅም ዘመናት የተፈጥሮ ሃብት የሆኑትን አፈር፣ ዛፍ፣ ውሃ እና መሰል ስጦታዎች በወጉ አልተጠቀመባቸውም፡፡ ይልቁንም የግንዛቤ እጥረቱን የሚሞላ፣ የሚሰማው፣ እምነት የሚያሣድርበት እና አሻግሮ የነገ ሕይወቱን የሚያሣይ መሪ በማጣቱ ከእጁ ያሉ ዕድሎቹን በዋዛ ተነጥቋል፡፡ ባለማወቅ በሰራቸው ስህተቶች በተፈጥሮ አለንጋ ተገርፏል፡፡ አሁንም የረሃብ አለንጋ የሚያርፍባቸው ወገኖቻችን ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ተፈጥሮ ስትንከባከባትና ስታከብራት ወርቋን ከጉያዋ ያለ ስስት ታዝቅሃለች፡፡ ስትጋፋት፣ ስታጎሳቁላት እና ስታጠፋት ቂሟ ‹‹ከግመል የከፋ ነው›› ለትውልድ ይተርፋል፡፡
አርሶ አደሩ በቀዬው ከዝናብና ከፀሐይ የሚያስጠልል የዛፍ ቅጠል እያጣ በመምጣቱ ተከፍቷል፡፡ በማሣው ላይ በትንሽዬ ማረሻ የሚዝቀው አፈር ዛሬ በአንድ ክንድ የሰጠ ማረሻም አልቀመስ ማለቱ ይብሱን አንገብግቦታል፡፡ የምርት ነገርማ ከመቀናጆ የማያልፍ ሆኖበታል፡፡
በመሆኑም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የአገሪቱ ሕዝብ በልጅነቱ የሚያስታውሳትን ያችን ለምለም ቀዬውን በእጅጉ ናፍቋል፡፡ ሞረሽ በሚል ተጠራርቶና ቀን ቆርጦ በተራቆቱ ዳገታማ፣ ተራራማ፣ ተዳፋታማ እና ሸለቋማ የመሬት ክፍሎች ላይ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች በየዓይነቱ በርብርብ ይሠራል፡፡ በፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተፈራ ታደሰ እንደገለጹት፤ የተፈጥሮ ሃብት ሥራው ዘንድሮም በተቀመጠለት ጊዜ ይሰራል፤ ከፌዴራል ጀምሮ በተዋረድ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ በመላው አገሪቱ የሚገኘው ፈጻሚ አካል ዝግጅት አድርጓል፡፡ የአፈጻጸሙ ሁኔታ እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ሊለያይ የሚችል ቢሆንም ባለሙያው ዝግጁ ሆኗል፡፡ 300 ሺ ቀያሽ አርሶ አደሮች ሰልጥነዋል፡፡ በሚቀጥለው ሣምንት መጀመሪያ ላይ ዋና ተዋናይ የሆነው አርሶ አደሩ የሚነቃቃበት መድረክ በሀገር ደረጃ ይካሄዳል፡፡ በመድረኩም በግብርና ሥራ ላይ ካለው ባለሙያ ከ80 በመቶ በላይ ተሳታፊ ይሆናል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ተፈራ ታደሰ ገለጻ፤ ተፋሰስ ተለይቷል፣ ለየአካባቢው የሚስማሙ ቴክኖሎጂዎች የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት አሰራር መመሪያን መሰረት አድርገው ተለይተው የልማት እቅድ ተዘጋጅቶላቸዋል፤ ባለሙያም ይህን ቦታው ድረስ ተልኮ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በግለሰቦች የእጅ የሥራ መሣሪያዎች ፣ 260 ሺ የቅየሣ መሣሪያዎች እና 13 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ተሳታፊ የሰው ኃይል ተዘጋጅቷል፡፡
ሥራው በአካባቢው የአየር ፀባይና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መሰረት አድርጎ የሚጀመር መሆኑን የተናገሩት አቶ ተፈራ፤ በቆላማ የአገሪቱ ክፍሎች ቀድሞ የሚጀመር ሲሆን፣ በደጋማው አካባቢ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ይዘገያል ብለዋል፡፡
ለአቶ ተፈራ አልፎ አልፎ በሀገሪቱ የሚስተዋሉት ግጭቶችና መፈናቀሎች በተፈጥሮ ሃብት ሥራው ላይ የሚያሣድሩት አሉታዊ ተጽዕና ይኖር ይሆን? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ‹‹ዘንድሮ ይህን ታሳቢ በማድረግ በቂ ዝግጅት ተደርጓል፤መዋቅሮች ተሻሽለው የተዋቀሩባቸው አካባቢዎች አሉ፤ሰፊ የግንዛቤ ማጎልበቻ ሥራዎች ተሰርተዋል፣ሀገራዊ ለውጡም ልዩ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ በመሆኑም ካለፉት ዓመታት የተሻሉ ሥራዎች ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል፤ የዝግጅቱ ምዕራፍ መቋጫ ግምገማ ያሳየው ይሄን ነው›› ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ተስፋ እንደተናገሩት፣ በመጀመሪያ አመራሩ በተለወጠ አስተሣሰብ መምራት እንዲችል ግንዛቤ ተፈጥሮለታል፡፡ ቀጥሎም እስከ ወረዳ ላሉ ባለሙያዎች ተግባር ተኮር የሆነ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ አሁን ላይ በየቀበሌው ለልማት ጣቢያ ባለሙያዎች እና ለቀያሽ አርሶ አደሮች ሥልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል አርብቶ አደር በሆነው አካባቢ 42 ወረዳዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሃያዎቹ ከታኀሣሥ ወር እኩሌታ ጀምሮ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ጀምረዋል፡፡ በአጠቃላይ ሥራ ያልጀመሩ በ 286 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደር አካባቢዎች ደግሞ ከጥር አምስት ጀምሮ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ይጀምራሉ፡፡
አቶ እንዳልካቸው በዘንድሮው ዓመት ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሰው ኃይል፣ 10 ሺ 770 ተፋሰስና ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት በመላው ኦሮሚያ ለተፈጥሮ ሃብት ሥራ ተለይቷል ብለዋል፡፡
በተፋሰሶቹ የተለያዩ የእርከን ፣ የውሃ ዕቀባ እና ሌሎች 208 ያህል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሣይንሳዊ ሥራዎች እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም 24 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ ስትራክቸሮች ይሰራሉ፤አምስት ሺ 365 ሄክታር መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ሆነው ይከለላሉ ብለዋል፡፡ በእግረ መንገዱ የሥነ ሕይወታዊ (ባዮሎጂካል) ሥራዎች የሚሰሩ ሲሆን ሁለት ሺ አሥራ አምስት ኩንታል የተለያዩ ችግኞች ዘር በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ እንዳልካቸው እንዳሉት፤ ካለፉት ጊዜያቶች የዘንድሮው የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ለየት ያለ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የተበታተነ አደረጃጀት ነበር፡፡ በአርብቶ አደር እና በአርሶ አደር አካባቢዎች በመስኖ ሥራም ሆነ በተፈጥሮ ሃብት ሥራ ልዩነት ነበር፡፡ ይህ መሆኑ ሥራዎች በተበታተነ መንገድ ወደ ታች እንዲወርዱ ያደርግ ነበር፡፡ ዘንድሮ ከላይ እስከ ታች ድረስ አደረጃጀቱ በአንድ እንዲቀናጅ ተደርጓል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ወንዴ፤ በበኩላቸው ክልሉ ወጣገባ የሚበዛበት ከመሆኑም በላይ ሰፊ የተፈጥሮ ሃብቱ ሥነ አካላዊ እና ሥነ ሕይወታዊ ሥራ ያስፈልገዋል፡፡ በመሆኑም የአፈርና ውሃ ጥበቃ እና የደን ተከላ ሥራዎች በሕብረተሰቡ ተሣትፎ ይሰራሉ ብለዋል፡፡ በዘመቻ ብቻ ሣይሆን ማህበረሰቡ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራው የሕልውናው መሰረት መሆኑን አምኖ ለዘለቄታው መስራት ከጀመረ ረጅም ጊዜ እንደቆየ አመልክተዋል፡፡
ሥራው በ2003 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ዘንድሮ በነባር ስድስት ሺ 482 እና በአዲስ ደግሞ 340 ተፋሰሶች ላይ ሥራው ይከናወናል ብለዋል፡፡ የተፋሰሱ ሥራ በራሱ እንዲመራ 118 የወረዳ ባለሙያዎችና ሌሎች 18 ባለሙያዎች እንዲሰለጥኑ ተደርጓል፡፡ ወረዳና ቀበሌ ላይ በሚገኙ ባለሙያዎች 108 ሺ 228 ቀያሽ አርሶ አደሮች ሰልጥነዋል፡፡ የእቅዱ 42 በመቶ ተፈጽሟል፡፡ ተጠናክሮም ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ከክልሉ የቆዳ ስፋት፣ከሚያስፈልጋቸው ቴክኖሎጂ እና መሰል ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ምዕራብ አማራ እና ምስራቅ አማራ በሚል ለሁለት ተከፍሎ 505 የዞንና የወረዳ ባለሙያዎች የተፈጥሮ ሃብት ልማት የተፋሰስ ሥራዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ የቦረቦር ልማት፣ የቴክኖሎጂ አመራረት፣የተፈጥሮ ሃብት አጠባበቅና የአፈር ለምነትን መመለስና መጠበቅ የሚያስችሉ ጉዳዮችን ሥልጠናው ዳሷል ብለዋል ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ማርቆስ፡፡
ዘንድሮ ከሌላው ጊዜ በተለየ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ እንዴት ይመራ የሚለውን የሚመልስ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡ ሥልጠናም በተዋረድ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ በክልሉ ከጥር አንድ እስከ ሦስት ባለው ጊዜ ውስጥ ሁሉም የተፈጥሮ ሃብት ሥራ የሚጀምሩ ሲሆን መራቆቱ አሳሳቢ በሆነባቸው አካባቢዎች ቀድመው የሚጀምሩ አሉ፡፡ ተፈጥሮ ሃብትን ለመስራት ሕብረተሰቡ ተደራጅቷል፡፡ አራት ሚሊዮን 887 ሺ 945 (የእቅዱን 89 በመቶ) የሰው ኃይል ተለይቷል፡፡ በአቅራቢያው በሚገኝ ተፋሰስም ለሥራ እንደሚሰማራ አቶ ማርቆስ ገልጸዋል ፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በበጀት ዓመቱ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ በህብረተሰቡ ተሳትፎ በ2,267,000 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ አንድ ሚሊዮን 463 ሺ ሄክታር መሬት ከንክኪ ነፃ ተደርጓል፡፡ በ343 ሺህ ሄክታር የሚሸፍኑ ቦታዎች የፊዚካልና ስነ ህይወታዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ጥገናና እድሳት ተደርጓል፡፡ የተፈጥሮ ሀብት መመናመንና መራቆትን መቀነስ፣ ምርታማነትን ከማሳደግ፣ የዕፅዋት ሽፋንን ከማሻሻል ባሻገር ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ያገገመ መሬትን በማልማት 256 ሺህ 408 ሴቶች፣ ወጣቶች እና መሬት አልባ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ 8ሺህ 691 ሄክታር መሬት ለነዚሁ አካላት ዝግጁ ሆነዋል፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ለግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ምቹ ሥነ ምህዳርን ይፈጥራል፡፡ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ሥርዓትን ማስፈን የአየር ሚዛንን በመጠበቅ ዘላቂ የግብርና ልማት ማጎልበትም ያስችላል፣ በተለያየ ምክንያት ለሚጎዳው ተፈጥሮም ወጌሻ ነውና ተጠናክሮ ይቀጥል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011
ሙሀመድ ሁሴን
Hey! Do you know if they make any plugins to
help with Search Engine Optimization? I’m trying to
get my site to rank for some targeted keywords but I’m not seeing very good results.
If you know of any please share. Thanks! You can read similar art here: Eco wool