ጽዱውና ሰፊው መንደር በበርካታ ቪላ ቤቶች ተሞልቷል። በግቢው ያሉት ልጆች ቡድን ቡድን ሠርተው በለምለሙ መስክ ላይ ይጫወታሉ። ለህፃናት መዝናኛ በተከለለውና የተለያዩ መጫዎቻዎች በሞሉት ሜዳ ላይ ደግሞ ዥዋ ዥዌ፣ ሸርተቴ፣ እሽክርክሮሽ፣ ወዘተ የሚጫወቱት ህፃናት ቀልብ ይስባሉ። በአንድ ወገን ደግሞ ወጣቶቹ በሞቀ የኳስ ጨዋታ ተጠምደው ሲታዩ ግቢውን አንዳች በዓል የሚከበርበት አስመስለውታል። ገና ከትምህርት ቤት እየመጡ ያሉት ደግሞ የደንብ ልብሳቸውን እንደለበሱ ቦርሳቸውን አንግተው የምሳ ዕቃቸውን አንጠልጥለው ወደየቤታቸው ያዘግማሉ። ግቢው ነፋሻማ አየር ያለው ከመሆኑ በተጨማሪ በአንድ ወገን የተተከሉት ኮባ፤ ሸንኮራ አገዳና ትናንሽ የጓሮ አትክልቶች ለግቢው ውበት አላብሰው ለተመልካች ጥሩ የዓይን ማረፊያ ሆነዋል።
እኔም በአስጎብኚዬ መሪነት ከግቢው አጠገብ ካለው ብስራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የሚወጣውን ዝማሬ እያዳመጥኩ ወደ አንደኛው ቪላ አመራሁ። ከቤቱ በረንዳ ላይ ደርሰን በሩን ስናንኳኳ በፈገግታ የተሞሉ እናት በሩን ከፈቱልን። አረጋሽ እባለለሁ ግቡ ብለውም ያቀረቡልንን ግብዣ ተቀብለን ወደ ውስጥ ዘለቅን። ቤቱ ሰፊ ሳሎን፤ ምግብ ማብሰያና የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ሲሆን ሳሎኑ ሙሉ ዕቃዎች የተሟሉለት ነው። በግድግዳው፤ በኮምፒዩተርና ቴሊቪዠኑ ላይ በርካታ ፎቶዎች ተሰቅለዋል፤ የቤቱ ጽዳትና የዕቃዎቹ አቀማመጥ በጥሩ የቤት እመቤት የተያዘ መሆኑን አፍ አውጥቶ ይናገራል።
እንድንቀመጥ ተጋብዘን አረፍ ከማለታችን አንዲት ህፃን ተከትላን ገባችና እየሮጠች እናቷን እቅፍ አድርጋ ከሳመች በኋላ ቀልጠፍ ብላ የፈተና ውጤቷን ማሳየት ጀመረች። ጥሩ ውጤት ስላመጣች የተሰማት ደስታ የእኛን መኖር እንኳ እንዳታስተውል አድርጓቷል። ላመጣችው ውጤት ከእናቷ ምስጋና ከተቸራት በኋላ የጥናት ሰዓት እስኪደርስ ድረስ ልብሷን ቀይራ፤ መክሰስ በልታ መጫወት እንድምትችል ተፈቅዶላት ወደ መኝታ ክፍሏ አመራች። እኛም ከኤስ. ኦ. ኤስ ቤተሰቦች ውስጥ የአንዱ ቤተሰብ መሪ ለሆኑት እናት አረጋሽ ህይወት እንዴት ናት? ስንል ጠይቀናቻው በፍፁም ፈገግታ የአስራ ስድስት ዓመት ቆይታቸውን በትዝታ ተመልሰው እንዲህ አጫወቱን።
“ትክክለኛ ጊዜውን ባላስታውሰውም ኤስ. ኦ. ኤስን የማውቀው ከልጅነቴ ጀምሮ ነው። ሐረር የድርጅቱ ቅርንጫፍ አለ፣ እዛ ውስጥ የሚያድጉ ልጆች ደግሞ ከእኛ ጋር አብረውን ይማሩ ነበር። በአንድ ወቅት የተቋሙ መስራች ፕሮፌሰር ኧርማን ገማይነር ህይወታቸው ማለፉን ስለሰማን ጓደኞቻችንን ለማስተዛዘን ሄደን ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የሐረር ኤስ ኦ ኤስን ቤተሰብ በአካል ለማየት አኗኗራቸውንም ለመገንዘብ የታደልኩትም የዛን ጊዜ ነበር። ከልጆቹ ጋር በደንብ እንቀራረብ ስለነበር ለቅሶውንም ደጋግመን ስለደረስን እግረ መንገዴንም ብዙ ነገር ለመገንዘብ ዕድሉን አገኘሁ።
አስራ ሁለተኛ ክፍል ከጨረስኩ በኋላ ሐረር መምህራን ማሰልጠኛ (ቲ. ቲ. አይ) ገብቼ ለቅድመ መደበኛ ትምህርት መምህርነት ስልጠና ወስጄ ለሁለት ዓመት ያህል እዛው ሳስተምር ቆየሁ። ታዲያ በአንዲት ዕድለኛ ቀን ጋዜጣ ሳገላብጥ ያ በልጅነቴ ያየሁት ድርጅት ያወጣውን ማስታወቂያ ተመለከትኩ ምንም አላመነታሁም ወዲያውኑ ተመዝግቤ ለፈተና ራሴን ማዘጋጀት ጀመርኩ ፈተናውንም ተወዳድሬ አለፍኩ። እስከዛ ድረስ ግን አስብ የነበረው እዛው በልጅነቴ ያየሁት ሐረር ያለው ግቢ ሥራ እጀምራለሁ ብዪ ነበር፤ ነገር ግን ክፍት ቦታ የነበረው አዲስ አበባ ብቻ ስለነበር ወደ ሸገር መምጣቱ የግድ ሆነ።
ሸገር ስመጣ የኤስ.ኦ.ኤስ ቤተሰብን ከመልመድ ይልቅ የሐረር አኗኗርን ትቼ የአዲስ አበባን ኑሮ መልመዱ አስቸግሮኝ ነበር። ያም ሆኖ ብዙም ሳልቆይ በዘመድም በጓደኛም ከአዲስ አበባ ጋር ያለኝን ግንኙነት ማጠናከር ቻልኩ። ለአራት ተከታተይ ወራት ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመጡ መምህራን ጭምር ስለህፃናት አስተዳደግና አንዳንድ መሰረታዊ ጉዳዮች የተሰጠው ስልጠናና ትምህርት ብዙ ግንዛቤ እንድጨብጥና ግቢውንም ሆነ የሚጠብቀኝን ቤት ሳልገባ እንዳውቀው ስላስቻለኝ ሥራውን ስጀምረው አልተደናገርኩም ነበር። በተጨማሪ ሥራ ጀምሬ ቤተሰብ ስረከብም የእያንዳንዱ ልጅ ታሪክ በወረቀት የተቀመጠ ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከኔ ቀድመው የነበሩትና ለ24 ዓመታት ያገለገሉት እናት ጡረታ ሲወጡ አብረውኝ ለአንድ ወር ተቀምጠው ጥሩ አቀባበልና ድጋፍ እንዲሁም ለዓመታት የነበረ ልምዳቸውን አካፍለውኝ፤ ከልጆቻቸውም ጋር አላምደውኝ ነበር የወጡት። በዚህም ትንንሾቹንና ትልልቆቹን ልጆች እንዴት ማቅረብና መያዝ እንዳለብኝ በቂ ግንዛቤ አግኝቺያለሁ። ይህም ሆኖ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አይሆንም። የልጆችን ባህሪ ለምዶ እነሱን እየተንከባከቡ ራስንም እያሳደጉ መኖር ትንሽ ይከብዳል። እናም አንዳንዴ ግር የሚል ነገር ሲገጥም የማህበራዊ ጉዳይ ሠራተኞች፤ የቅርብ አለቆቼና ዳይሬክተሩ የምፈልገውን ድጋፍ ያድርጉልኝ ስለነበር ያን ያህል የጎላ የማስታውሰው ችግር ገጥሞኝ አያውቅም። ዛሬም ድረስ አንዳንድ ጠንካራ ጥያቄዎችና ጉዳዮች ሲኖሩ የተቋሙ ባለሙያዎች ድጋፍና ምላሽ ፈጣን ነው።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ልጆቹ የቀደመች እናታቸውን ለመለየት የነበረባቸውን ችግር ስመለከት ምን ያህል ይፋቀሩ እንደነበርና እኔም ጥሩ መሥራት ብዙም መቆየት እንደምችል ተገንዝቢያለሁ። ፍቅራቸው ደግሞ ጊዜያዊ አልነበረም። አሁንም ድረስ የቀድሞዋ እናት ከእኔም ከልጆቹም ጋር ግንኙነታችን እንደተጠበቀ ነው ልጆቹ ለበዓል አየር ጤና መኖሪያ ቤቷ ድረስ እየሄዱ ይጠይቋታል። አንዳንዴ እሁድ እሁድም ይሄዳሉ እሷም ደጋግማ ትመጣለች፤ ስልክም ይደዋወላሉ። የመጀመሪያ ሰሞን አንዳንድ ጉዳዮች ገጥሞዋቸው ለእኔ ለመንገር ቢያፍሩ እንኳ እሷን ያናግሯት እሷም ከእኔ ጋር ትነጋገር ነበር። በባህሪዬ ከማንም ጋር ተቀራርቤ የመኖር ልምድ ስለነበረኝ አልተቸገርኩም፤ ነገር ግን ከሐረር ይዤ ያመጣኋቸው “አቦ ምናንም” የምላቸው አነጋገሮች ልጆቼን ያደናግራቸው ጀመር። ውለን ስናድር ግን እኔም እየቀነስኩ መጣሁ፤ ከእነሱም አንዳንዶቹ የኔን አነጋገር እየደገሙ ያስቁኝ ነበር።
ከሁለት ዓመት በኋላም ለአንድ ወር ያሳለፍነውን ጊዜ ተግዳሮቶች መነሻ በማድረግ በጥያቄ ተነስተው እኛም የጎደለንን የምንፈልገውን ግራ የገባንን ሁሉ እንድንጠይቅ አድርገው ሌላ ስልጠና ሰጡን። በዚህ ላይ በተፈጥሮ ሴትነታችን በራሱ የሚሰጠን የእናትነት ፍቅርም አለ። ልጆች ደግሞ የሚያዳምጣቸው ፍቅር የሚሰጣቸው ይፈልጋሉ። እንግዲህ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ይመስለኛል እስካሁን በባህሪው አስቸጋሪ የሆነ ልጅ ገጥሞኝ አስቀይሜም ተቀይሜም አላውቅም። ከዚህ በኋላ ሥራው ውስጥ በደንብ ስገባ ነገሮች ይበልጥ እየቀለሉኝ እየለመድኳቸው መጣሁ።
የቀን ውሏችን በፕሮግራም የተከፋፈለና በሥራ የተያዘ ነው፤ ሁላችንም እናቶች ጠዋት ተነስተን ልጆች ወደ ትምህርት ቤት መሸኘት አለ። ልጆቹ አዲስ አበባ ውስጥ በጣም በተለያየ ቦታ ነው የሚማሩት ልብስ በደንብ መልበሳቸውን፤ ደብተር ምሳ ዕቃ ምናምን መሟላቱን ስንከታተል እስከ ሁለት ሰዓት የስልክ ማንሻ ሰዓት እስክናጣ በሥራ እንወጠራለን። ከዛ በኋላ ከሁለት ሰዓት በኋላ ደግሞ የመዋዕለ ህፃናት ተማሪዎች የሆኑትን ከአልጋቸው አስነስቶ ገላ አጥቦ እንደዛው መሸኘት ይጠበቃል።
ከዛ መልስ ደግሞ አንዲት እናት በቤት የሚጠብቃትን መኝታ ቤት ማዘጋጀት፣ ልብሳቸውን ማስተካከል፣ ስንሠራ ሰዓቱ ይሄዳል። ቢሮ መረጃ መለዋወጥም አለ፤ የትምህርት ጉዳይ የቁሳቁስም ሆነ የቁጥጥርና የድጋፍ አገልግሎት ለመስጠት በየቀኑ ተሰብስቦ መነጋገር ይጠበቃል። በዚህ ውስጥ ሆኖ ከቤት የቀሩ ልጆችን መጠበቅና መንከባከብም አንዱ ሥራችን ነው። አንድ አስፈላጊ ነገር ተፈጥሮ ትምህርት ቤት ወላጅ መገኘት ካለበት የሚደወለው ለእናቶች በመሆኑ ከቤት ያለውን ልጅ ለአክስቱ ሰጥተን እንሄዳለን። የጎረቤት እናት አክስት ነው የምትባለው። ለሁሉም ልጆች ሞዴል መሆን ያለብን እኛ መሆናችንን እናውቃለን። ጎረቤት መላክ ካለብን አክስትሽን ሄደሽ እንዲህ በይ ብለን ነው የምንልካቸው። በስምንት ቀን አንድ ቀን እረፍት አለ። የሳምንቱንም ሆነ የዓመት እረፍት ስንወጣ ልጆችን የሚይዟቸውም የሚንከባከቧቸውም አክስቶች ናቸው። የሚገርመኝ በተለየኋቸው ቁጥር ይናፍቁኛል።
አንዳንዴ እንደ አስፈላጊነቱ ከልጆቹ ጋር በመሆንም ለቤት የሚያስፈልገንን ዕቅድ እናወጣለን። ገበያ ስንወጣም ልጆቹ ልምድ እንዲኖራቸው አካባቢያቸውንም እንዲገነዘቡ አንዳንድ ገበያዎችን በተለይ ልብስ ጫማ ሲገዛ ከልጆቹ ጋር ነው። ህክምናም እንደዛው ነው ታክመን ደረሰኝ አስገብተን ብሩ ተመላሽ ይደረግልናል።
ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም ማታ ማታ ሁሌም ቤተሰቡ ይሰባሰባል። እንደማንኛውም ቤት ቡና ይፈላል። በህብረት ተቀምጠን ቴሌቪዠን እናያለን። በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ ጠዋት ጠዋትም ሁሉም ወደየእምነት ተቋማቶቻቻው ይሄዳሉ። ስፖርት፤ ሙዚቃ፤ ሰርከስ፤ ቴኳንዶና ሌሎች ክበባቶችም አሉ የእነዚህም፤ የክበባት ቀናት ይከበራል።
ግቢው ለእኔ ትንሿ ኢትዮጵያ ነው። ስኬታማ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፤ ባሰለፍኩት አስራ ስድስት ዓመት አንዲት ልጄ በመሞቷ ብቻ በጣም አዝኛለሁ። ትልቅ ሐዘንም ነበር የገጠመኝ። ሐዘኑ የነበረኝንም ቀረቤታ እንድገምት ያደረገኝ ነበር። በፍፁም አላሰብኩትም አልተዘጋጀሁም ነበር። ስለሷ ሳስብ አሁን ድረስ የሚረብሽ ስሜት ይሰማኛል።
በጣም የተደሰትኩበት ቀን ደግሞ አንዷ ልጄ ስታገባ ነው። ከሁሉም ልጆች ጋር ያለኝ ቀረቤታ ጥሩ ነበር። ጓደኛ ሲይዙ ይነግሩኛል። የኔንም የወጣትነት ታሪኬን ጨምሮ ብዙ ነገር አጫውታቸዋለሁ። ይቺ ልጄ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ነበር የምትማረው። ስንደዋወል ተዘጋጅ የተመረቅኩ ዓመት አገባለሁ ትለኝ ነበር። ስለምንቃለድ ቀልዷን መስሎኝ ብዙም ትኩረት አልሰጠኋትም። ቀኑ ደርሶ ልናስመርቃት ስንሄድ ስቀልድ መስሎሽ ነው እንዴ? እውነቴን ነው አለችኝ። እኔ ማስተርስሽን እንድትሰሪ እፈልጋለሁ አልኳት፤ “ባክሽ አታካብጂ! አግብቼ እማራለሁ”፤ አለችኝ እኔ ግን እውነት እውነት አልመሰለኝም ነበር። ከቀናት በኋላ እህቶቿ ሽማግሌ እንደሚመጣ ሲነግሩኝ ቁርጥ መሆኑን አወቅሁ።
በአሁኑ ወቅት ስምንት ልጆች አሉኝ ሰባቱ ትምህርት ቤት የሚውሉ ሲሆን አንዱ እኔው ጋር እቤት የሚውል ህፃን ነው። እስካሁን ሃያ አንድ ልጆች አሳድጊያለሁ፤ አሁን አንዱ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ላይ ይገኛል። በዚህ ዓመት የሚመረቅም አለ። ስድስቱ ተመርቀው በሥራ ዓለም ናቸው፤ ሁለት አስራ ሁለተኛ ክፍል የደረሱም አሉኝ። ከቤት ካሉት አንዱ ልጅ ገና በእቅፍ ያለ ሲሆን ቀሪዎቹ ከኬጂ ጀምረው በትምህርት ላይ ናቸው።
ልጆቹ ራሳቸውን ችለው ከቤተሰቡ ከወጡም በኋላ ከእኛም ሆነ ከጓደኞቻቸው አጠቃላይ ከተቋሙ ጋር ያላቸው ግንኙነት አይላላም። እየመጡ ይከታተላሉ፤ ያሳለፉትን ህይወት መሠረት አድርገው ቀሪዎቹን ልጆች ይመክራሉ፤ ያሰለጠናሉ፤ ይንከባከባሉ። አንድ ሳምንት ቢያልፋቸው በሚቀጥለው አይቀሩም፤ ማታ ማታም ስልክ እንደዋወላለን። ዓመት በዓል ሲመጣ ግቢው በጣም ይደምቃል። ሁሉም ነገር አለ። የወጡ እናቶች ይመጣሉ፤ ልጆችም ከያሉበት ይሰባሰባሉ፤ የእንኳን አደረሳችሁ ዝግጅቶችም አሉ። በተለይ “የኤስ ኦ ኤስ ፋሚሊ ደይ” ተብሎ በሚከበረው ቀን ግቢው ልዩ ድምቀት አለው። ከውጭም ከውስጥም የሚቀር የለም። ትዳር የመሰረቱትም ይመጣሉ። ደግሞ እንደ እንግዳ ሳይሆን አንድ ቀን ቀድመው መጥተው ቤት አጽድተው ዕቃ አዘጋጅተው የሚሄዱም አሉ”።
ከእናት አረጋሽ በየነ ጋር የነበረንን ቆይታ ከማጠናቀቃችን በፊት በሴንት ጆሴፍ ትምህርት ቤት የአምስተኛና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የሆኑት ቢኒያም ኩምሳና ተማሪ ተስፋዬ ዳኜ ተከታትለው ገቡ። በክሩዝ አካዳሚ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ልዕልት ዳኜ ደግሞ ከመኝታ ቤት መጥታ ተቀላቀለችን። እናም ትምህርት እንዴት ነው? ወደፊትስ ምን ለመሆን ታስባላችሁ አልኳቸው። መልሳቸው አንድ አይነት ነበር፤ “ሁሌ እናጠናለን ጥሩ ውጤትም አለን፤ ዶክተርና መሪ መሆን እንፈልጋለን” አሉኝ። እንደኔ ያሉበትን ሁኔታ ያየ አላማቸውን ከማሳካት የሚያግዳቸው አንዳች ነገር እንደሌለ በቀላሉ ለመገመት ይችላል።
ቤተሰቡን ከመሰናበታችን በፊት በኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር በኢትዮጵያ የአዲስ አበባ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ልጅ ዓለም ባይለየኝ ደግሞ ስለ ኤስ ኦ ኤስ ህፃናት መንደር በአዲስ አበባ የሚከተለውን ብለው ሸኙን። “የኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር በአዲስ አበባ የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ1981 ሲሆን ዋናው ሥራ የቤተሰብ እንክብካቤ ያጡትንና የማጣት አደጋ የተደቀነባቸውን ህፃናትና ልጆች በቤተሰብ እንክብካቤ ውስጥ በአግባቡ እንዲያድጉ ማስቻል ነው። በአዲስ አበባ ፕሮግራም በተለያዩ ፕሮግራሞች ታቅፈው አገልግሎቱን በማግኘት ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉት ልጆችና ቤተሰቦች ከአራት ሺ 500 በላይ ናቸው። አገልግሎት ከሚሰጥባቸው ፕሮግራሞች መካከልም የኤስ ኦ ኤስ ቤተሰብ ክብካቤ፤ የተቋጥሮ ቤተሰብ፤ የአደራ ቤተሰብ፣ የቤተሰብ ማጠናከሪያ ፕሮጀክቶች፤ ህፃናት ማቆያ፤ መዋዕለ ህፃናት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ይጠቀሳሉ። እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያስችል ፕሮጀክት በመተግበር ላይ ነው። ህፃናት ወደ ኤስ ኦ ኤስ ቤተሰብ የሚቀላቀሉት ከመንግሥት ጋር በመተባበር ሲሆን ከተወለዱ እስከ ስድስት ዓመት ያሉት ብቻ።
ልጆቹን የሚንከባከቡትን የኤስ ኦ ኤስ እናቶችና አክስቶች ለመለየትም ህፃናትን ለማሳደግ ያላቸው ፍላጎት እንዲሁም በቂ ዝግጅት እንዳላቸው ከታወቀ በኋላ ለሦስት ወር ተኩል የመጀመሪያ ዙር የተግባርና የፅንሰሃሳብ ስልጠና ይሰጣል። በተጨማሪ ባላቸው የቆይታ ዘመን ልጆችን በማሳደግ የልጆችን እንክብካቤና ጥበቃ በተመለከተ ሁለንተናዊ ልጆች ዕድገትን እንዴት አድርገው እንደሚይዙ የሚሰጡ ተከታታይ ስልጠናዎች አሉ። በአሁኑ ወቅትም ለ103 ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠርም ተችሏል።
ለቀጣይም በአዲስ አበባ ከፍተኛ የህፃናት ለችግር ተጋላጭነት ስላለ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የቤተሰብ የማጠናከሪያ ፕሮጀክት እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ሌሎች አማራጭ የልጆች ክብካቤ ዘዴዎች በክፍለ ከተማና በወረዳ ድረስ የማስፋት ዕቅድ አለ። የወጣቶችን አቅም የሚያጎለብቱ ፕሮጀክቶችም ይኖራሉ” ሲሉ አጫውተውናል። እኛም በዚሁ ተሰናበትን፣ ቸር እንሰንብት።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 10/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ